Saturday, 29 October 2022 11:42

የጠሉትን ሊሸሹ ወይስ ወደ ወደዱት ሊሄዱ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

“የሃይማኖታው መፅሐፍ ዋና ማጠንጠኛ ነው” የተባለለት የኦሪት ዘፀአት ትረካ፣ ምን ይነግረናል? ምንስ እንማርበታለን?
ብዙ ሰዎች፣ የዛሬ ሃሳባቸውና ተግባራቸው ነገ ምን ዓይነት መዘዝ እንደሚያመጣባቸው ከወዲሁ ለማወቅ አይጥሩም። እንዲያውም እንደ ክህደት ይቆጥሩታል። እለታዊ የእልህና ጥላቻ ስሜቶችን በጭፍን ያራግባሉ።
ወደ ተመኙት ቦታ ወደ ስኬት ከፍታ የሚያደርስ “የሃሳብ፣ የአካልና የመንፈስ ስንቅ” ሳያዘጋጁ፣ ለጉዞ ይነሳሉ - ብዙ ሰዎች። ከነባሩ ችግር በማምለጥ ብቻ ወደ ሚመኙት ቦታ የሚያደርሱ ይመስላቸዋል።
ከነባሩ ኑሮና ከእለት መተዳደሪያ፣ ከነባሩ የስምግባር መርህና ባሕል፣ ከነባሩ ሕግና ስርዓት ለማምለጥ ሲሮጡ፣… የቀድሞውን አፍርሰው የለውጥ መፈክር ሲጮሁ፤… የተሻለ ሃሳብና መርህ አዘጋጅተው ነው?

በሃይማኖታዊው መጽሐፍ፣ ኦሪት ዘፀአት በተሰኘው ክፍል ውስጥ ከምናገኛቸው ትረካዎችና አገላለጾች መካከል አንዳንዶቹ፣ በጣም በጥበብ የተዋቡ በምስጢር የበለጸጉ ናቸው። ግራ የሚያጋቡ አባባሎችም አሉ። የትረካው ዋና አስኳል ግን እንዲህ ሲል ይጀምራል።
“የእስራኤል ልጆች ከባርነት የተነሳ አለቀሱ። ጮሁ።… እግዚሄርም ጩኸታቸውን ሰማ።… ከአብርሃም፣ ከይስሐቅ፣ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ። እግዚሄርም እስራኤላውያንን አየ። እግዚሄርም አወቀ”
ምን አወቀ?... የእስራኤላውያንን መከራ? እንደዚያ ብለው የተረጎሙ አሉ። ደግሞም ይመስላል። ነገር ግን፣ የወቅቱን ሁኔታ ከማየት በተጨማሪ የጥንቱን ቃልኪዳን እንዳስታወሰም ጠቅሷል።
የስደትና የባርነት ኑሮ አይደለም ቃልኪዳን። ማርና ወተት በምታፈልቅ የተስፋ ምድር፣ በሰላምና በነፃነት፣ የተደላደለ ኑሮ እንደሚገነቡና መልካም የሕይወት ጣዕም እንደሚፈጥሩ ነበር የተነገራቸው። በተለይ ለያዕቆብ (ለእስራኤል)። ብዙ ዘመን አለፈ። 400 ዓመት ገደማ።
በድርቅና በረሃብ ሳቢያ ወደ ግብፅ የመጡት የእስራኤል ቤተሰቦች፣… መልካም አቀባበል ቢገጥማቸውም፤ ከጊዜ በኋላ ግን ኑሯቸው ተበላሽቷል። ብዙ ትውልድ አልፏል። የእስራኤል ልጆች ኑሮም፣ የበደልና የባርነት መከራ፣ ሕይወትም መራራ ሆነዋል።
ከብዙ ዘመን ስቃይ በኋላ፣ አሁን ጩኸታቸው ተሰምቷል። መከራቸው ታይቷል። የጥንቱ ቃልኪዳን፣ የወደፊት ተስፋና ራዕይ እንደገና ታስቧል። ከዛሬ መከራ ማምለጥና ወደ ጥንቱ የቃልኪዳን ምድር መሄድ ነው የነገ ተስፋቸው። በአጭሩ፣ የለውጥ ጊዜ መድረሱ ታውቋል።
“እግዚሄርም አወቀ” የሚለው ትረካ፤ ይህን ሁሉ የሚገልፅ ሊሆን ይችላል።
በዚያ ላይ፤ “ምን አወቀ?” የሚል ጥያቄ በአንባቢና በአድማጭ ዘንድ ለመፍጠርም ያገለግላል። ትኩረትን ይስባል። ትረካው፣ ጥያቄ ቢፈጥርብን፣ ትኩረታችንን ቢማርክ፣ በባዶ አይደለም። ልዩ ትረካ ይዞ ሊመጣ ነው፡፡
በሃይማኖታዊው መጽሐፍ ውስጥ በርካታ ተዓምረኛ ትረካዎች መኖራቸው አያከራክርም። ነገር ግን፣ ይህ በሙሴ ዘመን ከተከሰተው የስደትና የዘመቻ ትረካ ጋር የሚስተካከል ሌላ ትረካ የለም ማለት ይቻላል። የትና የት!
የሙሴ ትረካዎች፣ ከዚያ በፊት ከነበሩት ጋር በእጅጉ የተለዩ ናቸው።
በሃይማኖታዊው ትረካ ውስጥ፣… ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ ከአዳምና ሔዋን አንስቶ፣ በነሄኖክ በኖህ ተሻግሮ፣ በአብርሃምና በይስሐቅ፣ በያዕቆብና በዮሴፍ ዘመን ብቻ ሳይሆን፣ ከሙሴ በኋላም፣ በኦሪት ትረካ ውስጥ ተካተቱትን ነገስታትና ነብያት በሙሉ፣ ከዳዊትና ከሰለሞን፣ ከኢሳያስ እስከ ዳንኤል ድረስ… ሁሉንም ማነፃፀር ይቻላል።
እግዚሄር እንዲህ አለ፤ እግዚሄር እንዲህ አደረገ… የሚሉ ትካዎች እጅግ ብዙ ናቸው። የኦሪት ዘፀአት የተሰኘው ትረካ ግን፣… ይለያል። የሃይማኖታዊው መፅሐፍ ዋና ማጠንጠኛ፣ የሌሎች ትረካዎች ሁሉ እምብርት ነው ይባላል- “ኦሪት ዘፀአት”።
ሙሴና እግዚአብሔር ጎረቤታሞች ይመስላሉ። የሰውና የእግዚአብሔር ውሎ እንደሰማይና ምድር በርቀት አይደለም። በሕይወት ዘመን ውስጥ ሦስቴ ወይም አራቴ ብቻ አይደለም። ቅርብ ለቅርብ የሚታይና የሚደመጥ፣ እለት ተእለት የሚከናወን ክስተት ነው።
እስራኤላዊያን በሙሴ መሪነት ከግብፅና ከባርነት የሚወጡበት ትረካ፣ የእግዚሄር ንግግርና ተግባር እጅግ በብዛትና በቅርበት፣ ቀንና ሌሊት ያለማቋረጥ የተዘረዘረበት ልዩ ትረካ ነው።
ቀን እንደ ደመና አምድ ሆኖ መንገድ እያሳያቸው፣ ሌሊት እንደ እሳት አምድ ሆኖ ጨለማውን እያበራላቸው ስደተኞቹን እንደመራ ከጎናቸውም እንዳልተለየ ይገልጻል ትረካው።
በዚያ ላይ፣ በፈርዖን እብሪት ሳቢያ የተከሰቱ መከራዎችና እልቂቶች፣ የሚያስፈሩና የሚዘገንኑ የመዓት ዓይነቶች፣… እንደ ጦርነት ዘመቻዎች እየተከታሉና እየተደራረቡ፣ እየሰፉና እየከፉ የሚመጡ ጥፋቶች፣ በዝርዝር አንድ በአንድ የተተረኩበት መንገድ፣… ከዚህ በፊትና ከዚህ በኋላ አልታየም። በእያንዳንዱ ትዕዛዝና ማስጠንቀቂያ፣ በእያንዳንዱ የቅጣት ውሳኔና የጥቃት ተግባር ላይ፣… እግዚሔር ተናገረ፤ እግዚሄር አደረገ… ብሎ ነው የሚተርክልን።
ሙሴ በብዛት የሚገናኘው ከእግዚአብሔር ጋር ነው። እግዚአብሔር ይናገራል። ሙሴ የተነገረውን ወደ እስራኤላውያን ያደርሳል። ለፈርዖን ይናገራል። ተመልሶ ለእግዚሄር ጥያቄ ይሰነዝራል፤ አቤቱታ ያሰማል። የፈርዖንን ምላሽ ያቀርባል።
እግዚሄር በፈርዖን እምቢተኝነት ይቆጣል። ቁጣውን ያወርድበታል።
አገሬው በዝንብ በእንቁራሪት ይወርራል።
በሰውና በእንስሳት በሽታ የግብፅ ምድር ይታመሳል።
እርሻው በውሽንፍር ይጠፋል።
የአባይ ውሃ በሞቱ አሳዎች ይሸፈናል። ከቆሻሻው ሽታው።
አገሬውን የማታ ጨለማ ብቻ ሳይሆን የቀን ጨለማ ይውጠዋል።
በዚያ ላይ የሰው እልቂት! ልጅ ያልሞተበት ቤተሰብ የለም።
ከሰውም ከእንስሳትም ሁሉ፤ የመጀመሪያ ልጅ በሙሉ እንደ ሞተ የሚገልጽ ትረካ ምን ማለት ሊሆን ይችላል? ኑሮም ሲዖል ሆኗል፤ ሕይወትም ገሃነም ገብቷል። አሳርና መከራ ያልደረሰበት፣ ሞትና ሃዘን ያልገባበት ቤት የለም።
የመከራ ዙሮችና የእልቂት ዘመቻዎች እንዲሁ በጥቅል አንድ ላይ ተዳብለው የተተረኩ አይደሉም። በዝርዝር አንድ በአንድ እየተጠቀሱ እንጅ። በእያንዳንዱም ውስጥ፣ የእግዚሄርና የሙሴ ንግግር ሰለ። በእያንዳንዱ ውስጥ ቁጣና ትዕዛዝ፣ ቅሬታና ክርክር፣ ጥያቄና መልስ አለ። እዝያው ቅርብ ለቅርብ፣ እዝያውና ወዲያው፣ እለት በእለት ነው። ቀን ከሌት በተከታታይ።
“በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ” ከግብፅ ያወጣኋችሁ፣… የሚለው አገላለጽ ተፈጠረው አለምክንያት አይደለም።
ከሙሴ ዘመን በፊትም ሆነ በኋላ፣ በእግዚሄርና በሰው መካከል እንደዚህ አይነት የእለት ተዕለት ግንኙነትና ንግግር፣… የዘወትር አመራርና የቅርብ ክትትል፣… በሃይማኖታዊው ትረካው ውስጥ በየትኛውም ቦታ የለም- ከሙሴ ጋር ብቻ ካልሆነ በቀር።
እንዲያም ሆኖ፣ “ኦሪት ዘፀአት” የሃማኖታዊው መፅሐፍ ዋና ማጠንጠኛ እምብርት ነው ተብሎ የሚነገርለት በዚህ ምክንያት አይደለም።
ሙሴ ዮቶር የሰጠውን ምክር ሰምቶ ከተቀበለ በኋላ ነው ተዓምረኛ ለውጦች መምጣት ጀመሩት። ዘመናትን የሚሻገሩ
- የሥነ ምግባርና የፍትሕ መርሆች መልክ ይይዛሉ።
- ሕግና ሥርዓት እግር ይተክላሉ።
- “እግዚሄርን መፍራት” የሚለው አገላለፅ፣ “መልካምነትን የሚያከብርና ለእውነታ የሚታመን” የሚል መንፈሳዊ ትርጉም ይላበሳል። ይህም በክብረ በዓላት ይገለጣል። ባህልን ይገነባል።
እነዚህ ሁሉ ነፍስ የዘሩት “በኦሪት ዘፀአት” ነው። የሃይማኖታዊው መፅሐፍ ዋና ማጠንጠኛ እንደሆነ የሚነገርለትም በዚህ ምክንያት ነው።
አሁን ወደ ትረካው መግቢያ እንመለስ።
“እስራኤውያን ከባርነት የተነሳ አለቀሱ፤ ጮኹም። እግዚሄርም የልቅሷቸውን ድምፅ ሰማ። እግዚሄር የቀድሞ ቃል ኪዳኑን አሰበ። እግዚሄር በባርነት ያሉትን እስራኤላውያን አየ። እግዚሄር አወቀ” ይላል።
ከዚያ በፊት ያልታየና ወደፊትም የማይደገም ልዩ የለውጥና የነውጥ ጊዜ መድረሱን አወቀ? ሊነገርና ሊደረግ የሚገባውን፣ ሊከሰትና ሊሆን የሚችለውን ሁሉ አወቀ? ወይስ ሌላ?
“እግዚሄርም አወቀ”… ያልተለመደና ያልተገለጠ አባባል ነው። “ምን አወቀ?” ብለን ለማወቅ እንድንጓጓ የትረካውን ዱካ እንድንከተል ሊገፋፋ እንደሚችል ግን አያጠራጥርም።
ትረካው እንዲህ ይላል፣ በምዕ12፡30-40።
ሞት ያልገባበት ቤት አልነበረምና፤ በግብፅ ምድር ታላቅ ለቅሶ ሆነ።
ፈርዖንም፣ ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ፣ እናንተ የእስራኤል ልጆች ተነሡ። ከሕዝቤ መካከል ውጡ። ሂዱም… አለ። ግብፃዊያንም ሁላችንም መሞታችን ነው ብለው ስለፈሩ የእስራኤልን ልጆች አጣደፏቸው በሌሊት።
…ፈጥነው ከምድሩ ይወጡ ዘንድ ያስቸኩሏቸው ነበር።… ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ። ቡሃቃውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት።…
የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው፣ ወደ ሱኮት ሄዱ። ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበር።… እጅግ ብዙ ከብቶችም ከእነሱ ጋር ወጡ።
ያመጡት ሊጥ አልቦካም ነበርና ቂጣ አደረጉት። ግብፃውያን ስላስቸኮሏቸው፣ ይቆዩ ዘንድ አልተቻላቸውም። ስንቅም አላዘጋጁም ነበር።… ይላል ትረካው።
ያ ሁሉ ስቃይና ሞት ሳይመጣ በፊት፣ በሰላም መነጋገር፣ መግባባትና መስማማት አይቻልም ነበር? አይሻልም ነበር? ይሻል ነበር። ይቻል ነበር ለማለት ግን ያስቸግራል።
ብዙ ሰው በአይኑ በእውን ካላየ፣ ቤቱን ካላንኳኳበት፣ በራሱ ላይ ካልደረሰበት በቀር፤ የነገን መዘዝ በቅጡ ለማሰላሰልና ለማገናዘብ አይጥርም። በቀውጢ የለውጥ ጊዜ ይቅርና በሰላም ጊዜም ብዙ ሰው፣ ጠንቅቆ የማሰብ ፍላጎት አይኖረውም። እንዲያውም፤ የማገናዘብ ሙከራ፣ የፈሪዎች ማምለጫ ነው፣ የክህደት ሙከራ ነው በማለት ያወግዛሉ፤ ያስፈራራሉ።
እናም አስተዋይና ጥበበኛ ሰዎች፣ ሃሳባቸውን ከመናገር ይታቀባሉ።
ጭፍን ስሜታዊ ሀሳቦች ይነግሳሉ።
በጎራ የተቧደኑ ጭፍን የስድብ ጩኸቶችና የጥላቻ ስሜቶች ይዛመታሉ።
ዛቻና ቅስቀሳ ይግለበለባሉ።
ጥቃትና አጸፋ፣ ወደ ጦርነትና እልቂት ያመራሉ።
 እነዚህን ክፉ መዘዞች ገና ከመነሻው አስቀድሞ በመገንዘብ፣ ጥፋትንና እልቂትን ከሩቁ ማስቀረት፣… የመግባባትና የመስማማት እድሎችን መፍጠር ይሻላል፤ ይቻላል።
ነገር ግን፣ ሰዎች ሁል ጊዜ የሚሻላቸውን ለማወቅ፣ ችሎታቸውንም ተጠቅመው መፍትሔ ለመፍጠር ላይመርጡ ይችላሉ።
መዘዝ አፍጥጦ ከመጣ በኋላም ግን ድንገተኛ አደጋ የደረሰባቸው ይመስል፤ ይደናበራሉ።
“አትሄዱም፤ አትወጡም” ሲል የነበረው ፈርዖን፣ በሌሊት፣ “ተነሡ ውጡ፤ ሂዱ” ብሎ እያጣደፈ ትዕዛዝ ይሰጣል።
ከግብፅ ለመውጣት ሲቸኩሉ የነበሩ የሙሴ ተከታዮች ደግሞ፣ ትንሽ ቢቆዩ በወደዱ። ስንቅ የላቸውም። ስንቅ አላዘጋጁም።
“ይቆዩ ዘንድ አልተቻላቸውም። ስንቅም አላዘጋጁም ነበር” ይላል ትረካው።
ስንቅ አለማሰናዳት፣ የመብል የመጠጥ ጉዳይ ነው። ግን ከዚያም ይብሳል። በአጠቃላይ ለጉዞ አለመዘጋጀትንም ያመለክታል። ከዚያም ይከፋል። በነፃነት ህይወታቸውን ለመምራት አለመዘጋጀታቸውን ያሳያል።
ሊጥ በቡሃቃ፣ በጨርቅ ጠቅልሎ፣ በትከሻና በጫንቃ ተሸክሞ፣ በውድቅት ሌሊት የመኖሪያ ቤቱንና ከተማውን ለመልቀቅ የሚጣደፍ ሰው፣… “መንገዱን በቅጡ የሚያውቅ፣ ለጉዞ በብቃት የተዘጋጀ አስተማማኝ ባለ ራዕይ ተጓዥ”… ይመስላል?
ማደሪያውንና መድረሻውን ያላወቀ፣ አቅጣጫውንና መንገዱን ለይቶ ያልወሰነ ተፈናቃይ አይመስልም?
“ምን ተይዞ፣ …ጉዞ!” ይባል የለ!
አዎ ግብፅ ውስጥ የእስራኤላዊያን ኑሮ፣ መራራ ነው። ለማምለጥ መመኘታቸው አይገርምም። ሕይወታቸው የችግር፣ የጥቃት፣ የፍርሃት፣ የውርደት፣ የባርነትና የሃዘን ኑሮ ሆኗል። ከመራራው ሸክም መላቀቅ፣ ነፃ መውጣት፣ ማርና ወተት ወደምታፈስ ወደ ተስፋይቱ ምድር መሄድ፣ በሰላም የተደላደለ ኑሮ መፍጠር…
ያው፣ የቅሬታና የምኞት፣ ከጨለማ የማምለጥና ወደ ብርሃን የመድረስ፣ የስጋትና የተስፋ ውሕደት ነው። ይህ መልካም እንጂ መጥፎ አይደለም። ታዲያ ችግሩ ምንድነው?
ምሉዕ አለመሆኑ ነው ችግሩ።
ቅሬታ፣… ምኞትን የሚያሳካ መሳሪያ አይደለም።
የማምለጫ መንገድህን በትክክል ካላወቅህና ካልመረጥክ ወደ ተስፋይቱ ምድር ላያደርስህ ይችላል። ወደ ባሰ ሲኦል የሚወስድ፣ አልያም አውላላ በርሃ ላይ የሚያስቀርህ ሊሆንም ይችላል።
በሌላ አነጋገር፣ የሃሳብህና የምግብ ስንቅህ፣ የአካልና የመንፈስ አቅምህ፣ ገና ብዙ ሳትራመድ ሊመናመን ይችላል።
ይሄም ነው ችግሩ። በአእምሮ፣ በአካልና በመንፈስ በቂ ስንቅ የላቸውም። አላዘጋጁም።
ግብፅ ውስጥ አነሰም በዛ፣ ቢከፋም ቢለማም፣… የሰከነና መሠረት የያዘ፣ ሥር የሰደደ የአኗኗር ዘይቤና የዘወትር ሕይወትን የሚቃኝ ነባር የግብፅ ባህል ውስጥ የነበሩ ሰዎች ናቸው።
አማረም አረረም፣ ጣፈጠም መረረም፣ በግብፅ ነባር ህግና ስርዓት ውስጥ ነበር የሚኖሩት። የግብፅ ህግና ሥርዓት፣ የዳኝነት መስመራቸውና ሚዛናቸው ነበር።
አሁን፣ ከነባር መኖሪያቸው ለቀቁ፤ ግን ስንቅ የላቸውም።
ከኖሩበት አገር ወጡ። የራሳቸው ሕግና ሥርዓት ግን የላቸውም።
አምነውበት፣ ወይም በዘልማድ፣ አልያም በይሉኝታና ለይምሰል ሲከተሉት የነበረ የስነ-ምግባር መርህ፣ እለታዊና መንፈሳዊ ባሕል፣ የስራ ቀንና ክብረ በዓል ሁሉስ?
ይህን ሁሉ ትተው ሲያመልጡ፣
ሌላ ትክክለኛ የስነ-ምግባር መርህ ይዘዋል? አልያዙም።
ለመኖርም ለማማርም፣ ለመግባባትም ለመዝናናትም፣ ለመስራትም ለመዝፈንም፣ ለእለት ጉርስም ለክብረ በአልም፣… በአጠቃላይ ሕይወታቸውን ለመምራት የሚያገለግል አዲስ ሃሳብ፣ አዲስ ስርዓትና ባህል የላቸውም።
በቅሬታ ስሜት ሁሉም ይቅርብን ሲሉና ሲያመልጡ፣… ያን ሁሉ የሚተካ የሃሳብና የባሕል፣ የምግብና የመንፈስ ስንቅ አዘጋጅተዋል? አላዘጋጁም።
የኦሪት ዘጸአት ትረካ፣ እነዚህ የአእምሮና የሃሳብ፣ የአካልና የኑሮ፣ የመንፈስና መልካምነት ጥያቄዎች፣… የሰው ልጅ በህልውና ጥያቄዎች መሆናቸውን የሚያሳይ፣ በርካታ መልሶችንና መፍትሄዎችንም ለማቅረብ የሚሞክር፣ እጅግ አስቸጋሪ የለውጥ ዘመንን የሚተርክ ፅሁፍ ነው።
ግን፣ የሃሳብ፣ የኑሮና የመንፈስ ስንቅ ሳይኖራቸው እንዴት? የትረካውን ምላሽ እናያለን። የምናገኘውን  ትምህርት እንመለከታለን።

Read 3317 times