Print this page
Saturday, 29 October 2022 11:36

የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ነገ ይጠናቀቃል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ፣ ዛሬን ለቀናት ሲካሄድ የዘለቀው የኢትዮጵያ መንግስትና የትግራይ ሃይሎች የመጀመሪያው መደበኛ የሰላም ንግግር፣ በነገው ዕለት እሁድ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የሰላም ንግግሩ ሂደቱ እስካሁን ምን ላይ እንደደረሰ ወይም በምን አጀንዳ ላይ እየተካሄደ እንደሚገኝ ያልታወቀ ሲሆን፤ ንግግሩ የሚደረገው ፕሪቶሪያ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መ/ቤት ውስጥ እንደሆነ ታውቋል።
የሰላም ንግግሩን የሚመሩት የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ተወካይና የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ ባለፈው ረቡዕ ወደ ስብሰባው ስፍራ ሲያመሩ በካሜራ ዓይን ውስጥ መግባታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአደራዳሪው ቡድን አባል የሆኑት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ስብሰባው ወደሚካሄበት ህንፃ ሲገቡ ታይተዋል።
የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ፉምዚሌ ምላምቦ እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ማይክ ሃመርም በሰላም ንግግሩ  ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተነግሯል።
 የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ ቪንሰንት ማግዌንያ እንደገለፁት፣ ባለፈው ማክሰኞ የተጀመረው የሰላም ንግግር በነገው ዕለት እሁድ ይጠናቀቃል።
እስካሁን ድረስ የሰላም ንግግሩ ለጋዜጠኞች ዝግ ሆኖ እየተካሄደ ሲሆን ከአደራዳሪዎችም ሆነ ከተደራዳሪዎች ሂደቱን አስመልክቶ የተሰጠ መረጃ እንደሌለ ታውቋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በመግለጫው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአሜሪካ መንግስትና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በሰላም ንግግሩ ላይ በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁሟል።
የሰላም ንግግሩ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የጥይት ድምፅን በማስቆም፣ የተረጋጋች የአፍሪካ አህጉርን ዕውን ማድረግ በሚለው የአፍሪካ ህብረት መርህ መሰረት እንደሚካሄድ የጠቆሙት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃመት፤ በዚህም መሰረት የአፍሪካ ህብረት፤ የተባበረች፣ የተረጋጋች፣ ሰላማዊና የማትበገር ኢትዮጵያን የመፍጠር ሂደትን በቁርጠኝነት እንደሚደግፍ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል፤ የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ከመጀመሩ በፊት የአሜሪካ ሴናተሮች ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በላኩት ደብዳቤ፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው እሁድ ሴናተሮቹ በላኩት ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ለመሳተፍ መወሰኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ ወደፊትም ሆነ በንግግር ሂደቱ ወቅት የተኩስ ማቆም እንዲደረግና ያልታገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲጀመር ጠይቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዋና ፀሃፊ አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው፤ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንዲጀመርና የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ ባለፉት ቀናት በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስትና የትግራይ ሃይሎች ተወካይ ተደራዳሪዎች በደቡብ አፍሪካ የሰላም ንግግር ላይ እየተሳተፉ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት፣ በትግራይ ጦርነቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ እየተነገረ ሲሆን የመንግስት ጥምር ሃይሎች የክልሉን ወሳኝ ከተሞች መቆጣጠራቸውን  ቀጥለዋል ተብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ መከላከያ በተቆጣጠራቸው የትግራይ አካባቢዎች የህዝብ አስተዳደር መመስረትን ጨምሮ የተቋረጡ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለመጀመር ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑን የፌደራል መንግስቱ አስታውቋል።
የአሜሪካ መንግስትና አውሮፓ ህብረት፣ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ የሚገኘው የሰላም ንግግር ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልፀዋል።

Read 11563 times
Administrator

Latest from Administrator