Saturday, 29 October 2022 11:14

ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌክላውድ አገልግሎት አቀረበ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮ ቴሌኮም፣ የደንበኞቹን የዕለት ተዕለት የቢዝነስ እንቅስቃሴ ለማዘመንና ለማሳለጥ (Empowering Businesses with Cloud Service) የሚያስችለውን የቴሌክላውድ አገልግሎቱን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል፡፡
የክላውድ ኮምፒውቲንግ አገልግሎት ተቋማት የራሳቸው የመረጃ ማዕከል እንዲሁም ለማዕከሉ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን መገንባት ሳያስፈልጋቸው ካሉበት ሆነው (virtually) የቴክኖሎጂና የዲጂታል ሶሉሽን አቅራቢዎች ዓለም የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መሠረት አድርገው በገነቧቸውና ደህንነታቸው በተጠበቁ የመረጃ ማዕከላት መረጃዎቻቸውን ማከማቸት፣ መቀመር ብሎም የተለያዩ አገልግሎቶች ማግኘት የሚያስችል የዲጂታል ሶሉሽን ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም፣ በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግልና የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ የመረጃ ክምችትና አጠቃቀም እንዲሁም ተዛማች የክላውድ አገልግሎት ፍላጎት መሠረት በማድረግ፣ እጅግ አስተማማኝ የክላውድ ማዕከላትን መሠረተ ልማትና አስፈላጊ ግብአቶችን ሁሉ በማሟላት ቴሌክላውድ አገልግሎትን በይፋ ለደንበኞቹ ማቅረብ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የክላውድ አገልግሎቶቹን በሶስት አማራጭ ያቀረበ ሲሆን፤
Infrastructure as a Service  (IaaS) ተጠቃሚዎች እንደ አስፈላጊነቱ ካሉበት ሆነው የግል መረጃዎቻቸውን ማስቀመጥ፣ መቀመር፣ ለደንበኞቻቸው የተለያዩ አገልግሎችን መስጠት የሚያስችል የክላውድ አገልግሎት
Platform as a Service (PaaS)- በዋነኛነት የሶፍትዌር አልሚዎች ካሉበት ሆነው ላበለፀጓቸው ሶፍትዌሮች የተሟላ የዳታቤዝ ማኔጅመንት ሲስተም (MySQL DB) መጠቀም ያስችላቸዋል፡፡
Software as a Service (SaaS)- ደንበኞች የተለያዩ በውጭ ምንዛሪ የላይሰንስ ክፍያ በመክፈል ያገኟቸው የነበሩ ሶፍትዌሮችን ከቴሌክላውድ በተመጣጣኝ ክፍያ በብር ማግኘት የሚችሉበት አገልግሎት ነው፡፡
ኩባንያው ለመነሻነት የሚከተሉትን ሶስት አገልግሎቶች ያቀረበ ሲሆን በቀጣይ የተለያዩ ተጨማሪ ሶፍትዌሮችን  የሚያቀርብ ይሆናል ተብሏል፡፡
One office productivity and collaboration solution ደንበኞች በቢሮዎቻችው የጽሁፍና ሌሎች የቢሮ አገልግሎቶች የሚያከናውኑበት የኦፊስ መተግበሪያ (Application) ነው፡፡
Video Management System (VMS) ደንበኞች ይህን አገልግሎት በመጠቀም የደህንነት የቪዲዮ ካሜራዎቻቸውን በማገናኘት የቪዲዮ ማስተዳደሪያ ሲስተም እና የሚፈልጉትን ያህል የዳታ ቋት ማግኘት ይችላሉ፡፡
Smart Education productivity /Ulearning የትምህርት ተቋማት በስማርት ትምህርት በመታገዝ የርቀት እና የገጽ-ለገጽ ትምህርትን በቪዲዮ ጭምር በመታገዝ በዘመናዊ መልኩ በመስጠት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚያገኙበት ሲሆን ለተማሪዎቻቸው የተሟላ ቤተ-ሙከራ፣ ማስታወሻ አያያዝ የትምሕርት ግብአቶችን ማጋራት፣ የትምህርት መርጃ እና ምዘና ማካሄድ ይችላሉ፡፡
የቴሌክላውድ አገልግሎትን በመጠቀም ድርጅቶችና ተቋማት ለቴክኖሎጂ መረጣ፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ስልጠና እና ጥገና የሚወስደውን ጊዜ እንዲሁም የውጪ ምንዛሪ ክፍያ በማስቀረት ተቋማት የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸው እና የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸው እና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በላይ ፍላጎትን ተከትሎ ሊስፋፋ የሚችል የሪሶርስ አጠቃቀም ተግባራዊ የሆነበት በመሆኑ አላስፈላጊ ወጪን እንደሚያስቀር ተጠቁሟል፡፡
“በዚህ አስተማማኝና ደሀንነቱ በተጠበቀ የክላውድ አገልግሎት ለመጠቀም የሚሹ ደንበኞቻችን በድረ ገጻችን cloud.ethiotelecom.et ተጠቅመው አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉና ክፍያቸውንም ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ በሆነው ቴሌብር ባሉበት በመክፈል ማግኘት የሚችሉ ሲሆን፤ ፍላጎታቸውን በኦንላይን ማከናወን በማይችሉበት ወቅት ወይም የቴክኒክ ድጋፍና ምክር በሚያስፈልጋቸው ጊዜ የአገልግሎት መስጫ ማዕከሎቻችንን በመጎብኘት ድጋፍ ማግኘት የሚችሉ መሆኑን በአክብሮት እየገለጽን፣ በቀጣይም ዓለማችን የደረሰበትን ዘመን-አፈራሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለውድ ደንበኞቻችን ተደራሽ በማድረግ ሕይወትን የማቅለል፣ ቢዝነስን የማሳለጥና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ተግባራችንን የምንቀጥል መሆኑን እንገልጻለን፡፡” ብሏል - ኢትዮ ቴሌኮም፡፡
በሌላ በኩል፤ በኢትዮ ቴሌኮም እና በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መካከል የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ስምምነት ባለፈው ሰኞ ተደርጓል፡፡
በዚህም ስምምነት፣የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለጉዳዮች፤ ከንግድ ምዝገባ፣ ከንግድ ፈቃድና ከንግድ ስያሜ ጋር ተያያዥነት ላላቸው የአገልግሎት ክፍያዎች  በኦንላይን አገልግሎት እንዲያገኙ እና ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ የሆነውን የዘመኑን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ቴሌብርን ተጠቅመው የአገልግሎት ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
“በተለይም የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለጉዳዮች ለአዲስ ንግድ ምዝገባ፣ ማሻሻያ፣ ምትክና የውል ማቋረጥ አገልግሎት ክፍያዎችን እንዲሁም አዲስ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት፣ ለማሳደስ፣ ምትክ ለመውሰድ፣ ውል ለማቋረጥ/ለመሰረዝ፣ ለአዲስ የንግድ ስም፣ የንግድ ስም ለማሻሻል፣ ለመቀየርና ለመሰረዝ የአገልግሎት ክፍያዎችን በቀላሉ በቴሌብር የክፍያ አማራጭ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል” ብሏል ኩባንያው፡፡
ባለጉዳዮች አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ www.etrade.gov.et በመግባትና የሚፈልጉትን የአገልግሎት አይነት በመምረጥ እንዲሁም የአገልግሎት ቅጹን በቀጥታ (online) በመሙላት ለአገልግሎቱ ክፍያ ለመፈጸም የሚሰጣቸውን የመክፈያ ቁጥር በመጠቀም በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በቴሌብር አጭር ቁጥር (*127#) የአገልግሎት ክፍያቸውን በቀላሉ መፈጸም እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

Read 7581 times