Saturday, 15 October 2022 11:17

“ጠላቴ በጸጉሬ ልክ ነው!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በአንድ ሚኒ ባስ የጀርባ መስታወት ላይ የተለጠፈች... “ለጠላቴም ስጠው!” አሪፍ አይደለች! በዚህ ክፋት በዛ፣ ተንኮል በዛ፣ መጠላለፍ በዛ... ምናምን በምንልበት ወቅት እንዲህ አይነት ዘና የሚያደርግ ጥቅስ ማየቱ...አለ አይደል...በሰው ላይ ያላችሁ እምነትና ተስፋ ሙሉ ለሙሉ እንዳይሟጠጥ ያደርጋል፡፡ 
ሀሳብ አለን...መቼም ዘንድሮ የማይደረግ አይነት ውድድር የለም አይደል! እኛም ሀሳብ አለን...ለምን “የወሩ ምርጥ የሚኒባስ ጥቅስ...” ምናምን የሚባል አይነት ውድድር አይዘጋጅምሳ! አሀ...ልክ ነዋ... aሚኒባስ ላይ የምታዩዋቸው አንዳንዶቹ ጥቅሶች እኮ...አለ አይደል... ከዕለታት አንድ ቀን “የምንጊዜም ታላላቅ ዓለም አቀፍ ጥቅሶች...” አይነት ርዕስ የሚኖራቸው መጽሐፍት ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ ናቸው፡፡
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አሁን “ለመሆኑ ጠላት አለኝ ትላለህ?” አይነት ጥያቄ ‘የመመለስ ግዴታ’ የሚጣልበት ጥያቄ ቢኖር፣ የዓለም ታላላቅ ልቦለዶችን የሚያስንቁ ‘ክሬቲቭ’ ታሪኮች ባይቀርቡ ነው!
“ለመሆኑ ጠላት አለኝ ትላለህ?”
“አለኝ ትላለህ ወይ! አሁን ይሄ እንዲህ ተቃሎ የሚጠየቅ ጥያቄ ነው!”
“አልገባኝም፣ ብታስረዳኝ፡፡”
“አሁን ጸጉሬን ቁጠርልኝ ብልህ ትችላለህ?”
“በጭራሽ...”
“አሁንም አንተ እየጠየቅኸኝ ያለው ጥያቄ ‘ጸጉርህን ቁጠርልኝ!’ ከማለት አይለይም፡፡”
“ጠላቶችህ ይህን ያህል ብዙ ሆነው!”
“እየነገርኩህ እኮ ነው፡፡ ጠላቴ በጸጉሬ ልክ ነው፡፡” ይቺን ‘ጠላቴ በጸጉሬ ልክ ነው’ የምንላትን ነገር ብዙዎቻችን የምንደጋግማት ነች፡፡ አለ አይደል...የጠላት መብዛት የእኛን በጎ ወገን እንደሚያሳይ አይነት ነገር፡፡
እናላችሁ... አንድ ሰው “ጠላቴ በጸጉሬ ልክ ነው፣” ካለ በኋላ መቻል ነው፡፡ እህ ብላችሁ ብትሰሙት...አለ አይደል....ከዩክሬይንና ከሩስያ ጦርነት ጀርባ ያለው እውነተኛ ምክንያት አንደኛው ክፍል በእሱ ላይ ያለው ጠላትነት እንደሆነ ሊነግራችሁ ይችላል። (እዚህ ሀገር እኮ ግርም የሚላችሁ ነገር ‘የነገር ኤ.ቲ.ኤም.’ ካርዳቸው ‘ኤክስፓየር’ ያደረጉ የከረሙ አራዶች “ቀደዳ...” የሚሉት አይነት ነገር የሁላችንም የማይገሰስ መብት የሆነ ነው የሚመስለው፡፡
ይቺን ታሪክ ስሙኝማ... ሰውየው የሆነ ጉልበተኛ ደበደበኝ ብሎ ፍርድ ቤት ቀርቧል። እና ጠበቃ ሆዬ በጥያቄ ሊያፋጥጠው እየሞከረ ነው፡፡
“ደንበኛዬን ጨካኝ ነው፡፡ አካላዊ ጉዳት አድርሶብኛል ብለህ ነው የከሰስከው?”
“አዎ፤ አካላዊ ጉዳት አድርሶብኛል፡፡”
“ምን አደረግህ?”
“መትቶኛል፣ ደግሞም ነክሶኛል፡፡”
“በምንድነው የመታህ?”
“በቡጢ...”
“በምንድነው የነከሰህ?”
“በጥርሱ ነዋ!”
እና በምን ሊነክሰው ፈለገ! መራቀቅ እኮ ሁልጊዜ አሪፍ አይደለም፡፡
“ለመሆኑ ሙዚቃ ዓለም ውስጥ እገባለሁ ብለሽ የወሰንሽው መቼ ነው?”
እሷ ደግሞ መራቀቅ ፈልጋ “ጥያቄውን ከመመለሴ በፊት መጀመሪያ ሙዚቃ ባልነው አተረጓጎም ላይ እንስማማ፣” ብትል ይታያችሁ! ጠያቂው አሁን በሆዱ “አቦ አትነጅሽኝ! እኔ ለራሴ ምሳ የሚጋብዝ ጠፍቶ ቁልጭ፣ ቁልጭ እላለሁ ትራቀቅብኛለች እንዴ!” ይፈረድባታል? እሜቴ ተጠያቂ መጀመሪያስ ትርጉሙ ምንድነው ብለሽ ነው የገባሽበት!
ይቺኝዋን ታሪክ ስሙኝማ.... እናም በጠዋት አንድ ሰው በሌላ ሰው እጅ ይገደላል። አስከሬኑም ቀኑን ሙሉ ቆይቶ አመሻሽ ላይ ሆስፒታል ይወሰዳል፤ ለአስከሬን መርማሪ ሐኪሙ ይቀርባል፡፡ ይኸው ሐኪም ስለ ምርመራው ሂደት እንዲያስረዳ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡ አንድ ሌላ መራቀቅ የሚፈልግ ጠበቃ እየጠየቀው ነበር፡፡
“የሟችን አስከሬን የመረመርክበትን ትክክለኛ ሰዓቱን ታስታውሰዋለህ?”
“አዎ፣ ምሽት ላይ ነበር፡፡”
“ምሽት ስንት ሰዓት ላይ?”
 “ምርመራው በሁለት ሰዓት ነው የተጀመረው፡፡”
“ምርመራውን እያደረግህ በነበርክበት ጊዜ ሰውየው ሞቶ ነበር፡፡ ልክ ነኝ፣ አይደል?”
“ልክ አይደለህም፡፡”
ይህኔ ጠበቃ ሆዬ አመዱ ቡን ይላል። በምንም አይነት የጠበቀው መልስ አልነበረም። ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል አንዳንድ ጊዜ እኮ እኛው ራሳችን ሊመለስልን ይችላል የምንለውን ምላሽ ወስነን ስናበቃ፣ የምናቀርባቸው የይምሰል ጥያቄዎች ወይም በነሲብ የምንናገራቸው ነገሮች ጉድ ሊያደርጉን ይችላሉዋ፡፡ እንበልና ከሆነ ወዳጃችሁ ጋር ድንገት ትገናኙና ጥቂት ካወራችሁ በኋላ አስቸኳይ ወሳኝ የህይወት ጉዳይ ቀጠሮ እንዳለበትና ሰዓቱም ሊያልፍበት እንደሆነ ነግሯችሁ ብድግ ይላል፡፡ ይሄኔ...አለ አይደል...ብዙም ያልለመደባችሁ ደግነት አይሰፍርባችሁ መሰላችሁ!
“በመሄድህ አዝናለሁ፡፡ እኔ ደግሞ ልክ ሳገኝህ ከአንተ ጋር ምሳ አብረን ልንበላ ወስኜ ነበር፡፡ ክትፎ ወይም የምትወደውን ጥሬ ሥጋ ብጋብዝህ ደስ ይለኝ ነበር። መቼ እንዲህ የተጣደፈ ሰው አይደለም ለአንድ ክትፎ፣ ዓመቱን ሙሉ ነጻ ክትፎ መመገብ እንደሚችል ቢነገረው ከሚሄድበት አይቀርም፡፡ አሀ...ወሳኝ የህይወት ጉዳይ ቀጠሮ ነዋ! እናላችሁ ምን ቢል ጥሩ ነው...
“የአንተን ግብዣማ ተራምጄ ልሄድ አልችልም፡፡ ቀጠሮው ነገም፣ ከነገ ወዲያም ሊሆን ይችላል፡፡” እርፍ! እና የሚሰጣችሁ መልስ ምን እንደሚሆን አስቀድማችሁ ወስናችሁ ጥያቄ መጠየቅ ሁልጊዜም አሪፍ ላይሆን ይችላል ለማለት ያህል ነው።  ልክ ነዋ...ለምሳሌ ከቢሮ ውጪ ሦስት ቀን አብራው ማኪያቶ የጠጣች የሥራ ባልደረባውን “በቃ በእጄ ገብታለች...” ብሎ ለሚያስብ ሰው፤ ሊጨበጨብለት ሳይሆን ሊታዘንለት ነው የሚገባው፡፡ እናላችሁ ቀጥሎ፣ ማለት ለአራተኛ ጊዜ ሲገናኙ ጥያቄውን ዱብ ያደርገዋል፡፡ በቃ...አለ አይደል... በዛ ሁሉ ሰው መሀል ተስፈንጥራ ተነስታ በደስታ ስትጠመጠምበት የሚፈጠረውን ትዕይንት እያሰበ፣ ፈገግ ብሎ፣ ለእሱ የጥያቄዎች ሁሉ እናት የሆነውን ጥያቄ ያቀርባል፡፡
“እኔና አንቺ ጠበቅ ያለ ጓደኝነት ብንጀምር ምን ይመስልሻል? ማለቴ እንደ ቦይፍሬንድና ገርልፍሬንድ...” “ምን!” ይህን ያህል ግድግዳ የሚያነቃንቅ  ድምጽ ለመጨረሻ ጊዜ የሰማው ድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ቦላሌ ሱሪ የለበሰ ዕለት ሊሆን ይችላል፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...
“...እኔ የሥራ ባልደረባዬ ነህ ብዬ አብሬህ ሻይ ብጠጣ ምን መሰልኩህ! ድሮም ወንዶች ስትባሉ...” ብላ በድንጋጤ ሁሉም ነገሩ እንደፈጠጠ ጥላው ልትሄድ ትችላለች!
እናላችሁ... ብሽቅ ያለው የአስከሬን መርማሪ ዶክተር ጠበቃውን “እስቲ ጥያቄውን ድገምልኝ፣”  ይለዋል፡፡ ጠበቃውም ይደግምለታል፡፡
“ምርመራውን እያደረግህ በነበርክበት ጊዜ ሰውየው ሞቶ ነበር፡፡ ልክ ነኝ፣ አይደል?”
“ልክ አይደለህም፡፡ አልጋው ላይ ቀና ብሎ ለምን የአስከሬን ምርመራ እያደረግሁ እንደሆነ ገርሞት ያየኝ ነበር!” አለና አረፈላችሁ፡፡
ከጸጉር ልክ ጠላት ይሰውራችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 1401 times