Saturday, 15 October 2022 11:17

“ክብር” የስነ-ፅሁፍና የጋዜጠኝነት ሽልማት ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ሽልማቱ 18 ዘርፎች አሉት ተብሏል

       በቃል መልቲ ሚዲያ አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው “ክብር” የስነ-ፅሁፍና የጋዜጠኝነት ሽልማት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥር ወር መጨረሻ ላይ ይካሄዳል።
የሽልማቱ አዘጋጅ የቃል መልቲ ሚዲያ መስራችና ዋና ስራ አስፈፀሚ ደራሲና ጋዜጠኛ ቃልኪዳን ሐይሉ ከሽልማቱ የቦርድ አባላት ጋር ከትላንት በስቲያ ጥቅምት 3 ቀን ረፋድ ላይ በቤልቪው ሆቴል ሽልማቱን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት በሽልማቱ መሳተፍ የሚችሉት ከመስከረም ወር 2014 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓ.ም የታመሙ የታሪክ፣ የግለታሪክ፣ የምርምር፣ የልጆች መፅሐፍት፣ የግጥም የረጅምና የአጭር ልቦለድ መፅሐፍት፣ ፊልምና የቴአትር ስክሪፕቶች፣ የሬዲዮና የተሌቪዥን የዓመቱ ምርጥ ፕሮግራሞች፣ የህትመት ውጤቶች እና ሌሎችም ዘርፎች ሲሆኑ ጋዜጣዊ መግለጫው ከተሰጠበት ሰዓት ጀምሮ ማህበረሰቡ ለየዘርፉ ይመጥናሉ የሚላቸውን ሰዎችና ስራዎች http://kibershilemat.com ላይ እየገባ እንዲጠቁም አቶ ቃል ኪዳን ጥሪ አቅርበዋል።
ሽልማቱ ተዓማኒና ቀጣይት እንዲኖረው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ “አለ የስነ-ጥበብና የዲዛይን ት/ቤት” ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን እና አቶ አገኘሁ አዳነ ድልነሳው፣ ከጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር)፣ ከአርቲስቶች ሰለሞን አለሙ ፈለቀ፣ ከደራሲያን ማህበር የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙና ሌሎችም በቦርድ አባልነት ተካትተውበታል። የመጀመሪያው ጥቆማ መቶ በመቶ በህዝብ የሚካሄድ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ላይ ምርጥ አምስቶቹ በዳኞችና በህዝብ ይመረጣሉ ተብሏል። ለሽልማቱ የተዘጋጀው አዋርድ ሙሉ ለሙሉ ከነሀስ የተሰራና ለአይን ማራኪ ሲሆን ዲዛይኑ በአለ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት መሰራቱም ተገልጿል።
ለሽልማቱ ጥቆማ የተሰራው ድረ-ገጽ በኩራዝ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለሙያዎች በጥንቃቄ የተዘጋጀ ሲሆን ተዓማኒና ትክክለኛ ምርጫ መካሄዱን በግልፅ የሚያሳይ እንደሆነ የኩራዝ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባልደረባ ወጣት ብሩክ ማሞ የድረ-ገፁን ዲዛይን እያሳዩ አብራርተዋል። ሽልማቱ ሂደቶቹን ጨርሶ ጥር ወር መጨረሻ ላይ እንደሚካሄድም ተብራርቷል።

Read 31583 times