Saturday, 08 October 2022 09:46

ምሥራቅ አፍሪካን በትዊተር ያመሱት የሙሴቬኒ ልጅ

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(2 votes)

    • “እኔና ሠራዊቴ ናይሮቢን ለመያዝ 2 ሳምንት አይፈጅብንም”
         • ሙሉ የጄነራልነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው ከሥልጣን ተሰናብተዋል
               
        የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የበኩር ልጃቸውንና የአገሪቱ የምድር ጦር ዋና አዛዥ የነበሩትን ሌ/ጄነራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባን ባለፈው ማክሰኞ ከሥልጣን ያሰናበቷቸው ወደው አይደለም፡፡ ሙሴቬኒ ጄነራሉን ልጃቸውን ዝም ቢሏቸው ኖሮ፣ አገራቸውን ኡጋንዳን ያለ ጎረቤት ነበር የሚያስቀሯት፡፡ ምሥራቅ አፍሪካን እኮ በትዊተር አመሷት!!
ሌ/ጄነራሉ ከአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጣን መነሳታቸው የተሰማው ሰሞኑን  የጎረቤት አገር ኬንያን መዲና በጦር ሠራዊታቸው ለመቆጣጠር ሁለት ሳምንት እንኳን እንደማይፈጅባቸው በትዊተር ገፃቸው መፃፋቸውን ተከትሎ ነው፡፡ (ድንገት ተነስተው እኮ ነው ናይሮቢን ስለመውረር የጻፉት!)
ባለፈው ማክሰኞ ሌ/ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ፣ ከኡጋንዳ የምድር ጦር ዋና አዛዥነታቸው ተነስተው የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ እንደተሰጣቸውና የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አማካሪ ሆነው እንዲቀጥሉ መወሰኑን ሮይተርስ የአገሪቱን የጦር ሠራዊት መግለጫ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ያሻቸውን ሃሳብና አቋም በማንኛውም አገርና መንግስት እንዲሁም ግለሰብ ላይ ያለምንም ገደብ በትዊተር ገጻቸው ላይ በማንጸባረቅ የሚታወቁት የኡጋንዳው ከፍተኛ የጦር መኮንን ካይኒሩጋባ፣ሰሞኑን ጎረቤት አገር ኬንያን በተመለከተ ትዊት ባደረጉት ሃሳብ (ቅዠት ቢባል ይሻላል) ኬንያውያንን ክፉኛ ነው ያስቆጡት፡፡ (ዓላማቸውም ማበሳጨት ይመስላል!)
ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ፣ ኡጋንዳና ኬንያ መዋሃድ እንዳለባቸውና ቀጣይዋን የጣሊያን ጠ/ሚኒስትር ለማግባት የከብቶች ጥሎሽ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ  ፅፈው ነበር፤ ጄነራሉ፡፡
“እኔና ሠራዊቴ የኬንያን ዋና ከተማ ናይሮቢን ለመቆጣጠር 2 ሳምንት አይፈጅብንም” ብለዋል።
በሌላ ተያያዥ የትዊተር ጽሁፋቸው ደግሞ፤ “መዋሃድ የግድ ነው! ማናቸውም ክብር ያላቸው ሰዎች ከእንግዲህ በኋላ እነዚህ ሰው ሰራሽ፤ የቅኝ ግዛት ዘመን ድንበሮች እንዲቀጥሉ ሊፈቅዱ አይችሉም፡፡ በእኛ ትውልድ ውስጥ በእርግጥ እውነተኛ  ሰዎች ካሉ፣ እነዚህ ድንበሮች መፍረስ አለባቸው!” የሚል ቅጥ አምባሩ የጠፋ ሃሳብ አንጸባርቀዋል፡፡ (በድፍረት!)
 ይህ የጄነራሉ ሃሳብ ታዲያ ኬንያውያንን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡ ትችትና ዘለፋም አስከትሎባቸዋል፡፡ አንዳንዶች እንደውም ሙሴቪኒ የሰፋቸውን ሙሉ ልብስ ለብሰው የሚያሳይ ምስል በመለጠፍ፤ “በቅድሚያ የአባትህን ልብስ ሰፊ ተቆጣጠር” ሲሉ ተሳልቀውባቸዋል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ማንም በኬንያውያኑ አይፈርድባቸውም፡፡ እንዴ ጄነራሉ እኮ የሚያወሩት ሉአላዊት አገርን ስለመውረር ነው፡፡ (ያውም በ21ኛው ክ/ዘመን ነው!)  
ይህንንም ተከትሎ የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ የጄነራሉን የትዊተር መልዕክት በቀጥታ ሳይጠቅስ፣የኡጋንዳ  መንግስት ከጎረቤት አገር ኬንያ ጋር ለሚኖር ሰላምና ትብብር ቁርጠኛ መሆኑን  አስታውቋል።  
አንድ የኡጋንዳ ጦር ሰራዊት ቃል አቀባይ ጉዳዩን አስመልክተው ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ፤ አገራቸው ከኬንያ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰው፤ የኡጋንዳ  ጦር ሠራዊት ጎረቤት አገር ኬንያን ሊወርር እንደማይችል አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ (ዕድሜ ለጄነራሉ! ወረራ አጀንዳ ሆኖ አረፈው!)
ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒም የጄነራል ልጃቸውን የትዊተር መልዕክት በተመለከተ ኬንያውያንን ይቅርታ ለመጠየቅ መገደዳቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል፡፡ (የልጅ ዕዳ ለአባት ይሏል ይሄ ነው!) በነገራችን ላይ በኬንያ በቅርቡ በተደረገው ምርጫ አሸንፈው አምስተኛው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዊሊያም ሩቶ፣በሲመተ በዓላቸው ላይ ባደረጉት ንግግር ዩዌሪ ሙሴቪኒን “የአፍሪካ አባት” ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡ (ልጃቸው ግን ከእኚህ ወዳጃቸው ጋር ሊያጣሏቸው ነበር!)
የሙሆዚ ካይኒሩጋባን የትዊተር መልዕክቶች በቅጡ ለፈተሸም “ብሽሽቅ ነው እንዴ ጄነራሉ የያዙት?!” ሊያሰኘው ይችላል፡፡ ናይሮቢን ለመያዝ ሁለት ሳምንት አይፈጅብንም የሚለውን ሃሳብ በሉት ቅዠት የለጠፉት ባለፈው ሰኞ ሲሆን፤ የዚያኑ ዕለት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ተከታዩን መልዕክት አጋርተዋል፡፡
”እናንተን ኬንያውያንን ትንሽ በማስደንገጤ ደስ ብሎኛል፡፡ ሁለት ሳምንት ረዥም ነው፤ በእርግጠኝነት ናይሮቢን በአንድ ሳምንት እንቆጣጠራለን! በካርኒቫል ወንድሞቼ በመታገዝ!”
 ጄነራሉ ባለፈው ሰኞ ጎረቤት አገር ኬንያን የሙጥኝ ብለዋት ነበር ማለት ይቻላል - በትዊተር፡፡ በጥቂት ሰዓታት ልዩነት ደግሞ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን በተመለከተም አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
“ከተወዳጁ ትልቁ ወንድሜ ጋር ያለኝ ብቸኛ ችግር፣ ለሦስተኛ ዙር አለመወዳደሩ ነው፡፡ በቀላሉ ማሸነፍ እንችል ነበር” ሲሉ ፅፈዋል። (ኬንያን እንደራሳቸው ግዛት ወይም አገር ቆጥረው ማለት ነው!)  
ሌ/ጄነራሉ በኬንያ ብቻ አልተወሰኑም፡፡ ከኢትዮጵያ እስከ ኮንጎ፣ ከሩሲያ እስከ ጣልያን በትዊትር ያላተራመሱት አገር የለም፡፡ አቧራ አስነስተዋል፡፡ ቁጣ ቀስቅሰዋል፡፡ ውዝግብ ፈጥረዋል፡፡
ካይኒሩጋባ የትግራይ አማፂ ቡድንን በመደገፍም ትዊት አድርገው ነበር፡፡ በምስራቃዊ ኮንጎ እየተዋጋ ለሚገኘው አማፂ ቡድንም ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ጦርነት ሁሉም አፍሪካውያን ከሩሲያ ጎን መቆማቸውንም ፅፈዋል - በትዊተር ገፃቸው፡፡
ሌተናል ጄነራሉ በሌላኛው አነጋጋሪ የትዊተር መልዕክታቸው ደግሞ ባለፈው  ሳምንት በተደረገ ምርጫ ፓርቲያቸው በማሸነፉ፣ የጣሊያን ጠ/ሚኒስትር ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ሰፊ ግምት ለተሰጣቸው ጂዮርጂ ሜሎኒ፣ ጥሎሽ የመስጠት  ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ (ለማግባት መሆኑ ነው!)
“ለቀጣይዋ የጣልያን ጠ/ሚኒስትር ስንት ከብቶችን ልትሰጡ ትችላላችሁ? አውሮፓውያን ለሚወዷቸው ሴቶች አበባ ይሰጣሉ፤ በአገሬ ባህል ግን ለምንወዳቸው ሴቶች የምንሰጠው ከብቶችን ነው፡፡” ሲሉ ለ60 ሚሊዮን የትዊተር ተከታዮቻቸው ምኞታቸውን አጋርተዋል፤ ጄነራሉ፡፡  
የሜሎኒ የቅርብ ረዳት ጉዳዩን አስመልክተው ለሪፖርተሮች በሰጡት ምላሽ፤ “ጥሎሹ ረብ ያለው ርዕስ ጉዳይ አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡ (ቅጥ-አምባርነቱ  ግን ፈፅሞ  አያጠያይቅም!)
እስካለፈው ማክሰኞ ድረስ የኡጋንዳ ምድር ጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ሌ/ጄነራል ሙሆዚ ካይኒራጋባ፣የኢትዮጵያን የሰሜኑን ጦርነት በተመለከተም የትግራይ አማፂ ቡድንን ደግፈው ትዊት አድርገው ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት የትግራዩ ግጭት በተፋፋመበትና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በክልሉ ተፈፅሟል ያሉትን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ጄነራሉ በትዊተር ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “የትግራይ መከላከያ ሃይሎች… የምትታገሉለትን ዓላማ እደግፋለሁ፡፡ የትግራይ እህቶቻችንን የደፈሩና ወንድሞቻችንን የገደሉ መቀጣት አለባቸው፡፡” ብለው ነበር፡፡
ባለፈው ነሐሴ ወር ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውንና ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ማነጋገራቸውን ተከትሎ ግን የጄነራሉ አቋም መለወጡን ዘ ኢስት አፍሪካን  ዘግቧል። ጄነራሉ አዲስ አበባን ጎብኝተው ሲመለሱ የሚከተለውን ነበር ትዊት ያደረጉት፡፡
“ህዝቡ በፍቅርና በደግነት ተቀብሎናል፡፡ ልኡካናችን ከታላቁ ወንድማችን ከኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በጣም ጥሩና ፍሬያማ ውይይት አድርጓል፡፡ ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካውያን መፍትሄዎች በሚለው መርህ እናምናለን፡፡ የኢትዮጵያውያን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታ ተስፈኛ ነኝ፡፡ እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ!” ብለዋል፡፡
ሌተናል ጄነራሉ ባለፈው ማክሰኞ ከሥልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ ባሰፈሩት የትዊተር ፅሁፋቸው፤ በቀጣዩ ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለተሰጣቸው የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ አባታቸውን አመስግነዋል፡፡ (እንዴት አያመሰግኑ!)  
“ለዚህ ሹመት በካምፓላ ጎዳና ላይ የምናከብረው በዓል ይኖረናል፡፡ ለዚህ ትልቅ ክብር በመብቃቴ  አባቴን አመሰግነዋለሁ፡፡” ሲሉ ጄነራሉ ፅፈዋል፡፡
የኡጋንዳ የፖለቲካ ተንታኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ የ78 ዓመቱ ሙሴቪኒ፣ ልጃቸውን የሥልጣናቸው ወራሽ ለማድረግ እያዘጋጁት ነው በሚል ለረዥም ጊዜ ሲከሷቸው ቢቆዩም፤ ለ36 ዓመታት በሥልጣን የዘለቁት ሙሴቪኒ ግን ክሱን በተደጋጋሚ አስተባብለዋል፡፡ (የነገ ሰው ይበለንና ፤እውነቱን አብረን እናየዋለን!)  
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኡጋንዳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ከሥልጣን ቢነሱም የተሰጣቸውን የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ በመቃወም፣ የቀድሞው የምድር ጦር ዋና አዛዥ በሉአላዊ  አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እንዲሁም የትንኮሳ መልዕክት በማስተላለፍ ለፈጸሙት ወንጀል ወህኒ መውረድ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ ፖለቲካ ተንታኞች፣በአፍሪካ ሥልጣን የቤተሰብ አክስዮን ሆኖ ሲያዝ ምን እንደሚመስል በቅጡ ለመረዳት ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል፤ የአባትና ልጅ ሥልጣንን!

Read 873 times