Saturday, 01 October 2022 12:27

የኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት በወለጋና በጋምቤላ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኦነግ ሸኔ እና በአማራ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች  100 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል
በጋምቤላው ውጊያ  የፀጥታ ኃይሎች ቢያንስ 50 ሰላማዊ ሰዎች ገድለዋል
መንግስት የሲቪል ሰዎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ በኦሮሚያ ክልል፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ በአሙሩ ዞን፣ በሆሮ ቡልቅ እና በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች፣ ከነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሽኔ)፣ በአማራ ኢ-መደበኛ ታጣቂ ኃይሎችና ግለሰቦች በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሰላማዊ  ሰዎች መገደላቸውን መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም  ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከግድያው በተጨማሪ የግል ንብረትና የቁም ከብቶች መዘረፋቸውን፤በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ያለበቂ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከአካባቢው የፍትሕና የአስተዳደር አካላት እንዲሁም በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የእርዳታ ድርጅቶች ማረጋገጡን አመልክቷል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ”የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት በአካባቢው ብሔርን መሰረት አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በመወሰድ ላይ የሚገኙትን እርምጃዎች ችግሩን በሚመጥን ደረጃ በማሳደግ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል” ሲሉ በድጋሚ አሳስበዋል።
በአካባቢው ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች አሁንም ተስፋፍተው መቀጠላቸውን ኮሚሽኑ ጠቅሶ፤ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አስገንዝቧል።
በሌላ በኩል፤ በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ በኦነግ ሸኔ  እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር የተደረገውን ውጊያ ተከትሎ፣ ቢያንስ 50 ሰላማዊ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን  ኢሰመኮ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በከተማዋ በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እና በአማጺያኑ ታጣቂዎች መካከል የተደረገውን ውጊያ ተከትሎ የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ የአካል ጉዳቶችንና ዘረፋዎችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ምርመራ ማድረጉን ጠቁሟል፡፡  ሰሞኑን  ይፋ ባደረገው ባለ 13 ገፅ ሪፖርትም፤ ከሰኔ 7 እስከ 9  2014 ዓ.ም  በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ዘረፋ  በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎች  መፈጸሙን አመልክቷል።
ይህንን ድርጊት ሲመሩና ሲያስፈጽሙ የነበሩ ሃላፊዎች ላይ የህግ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ ይገባል  ብሏል፤ኢሰመኮ በሪፖርቱ፡፡
በሦስቱ ቀናት ውስጥ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ ሴቶችና የአዕምሮ ህሙማንን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰላማዊ ሰዎችን በተናጠልና በጅምላ ከፍርድ ውጪ መግደላቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ በተጨማሪም 25 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት፣ ቁጥራቸው ያልተጠቀሱ በርካቶች ላይ ደግሞ ድብደባና የማሰቃየት ተግባር መፈጸሙን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ታጣቂዎቹ ከተማዋን ለቀው ከወጡና ከተማው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ከገባም በኋላ ግድያዎቹ የተፈፀሙ ሲሆን ለዚህም የክልሉ  የጸጥታ ኃይሎች ተጠያቂ መሆናቸውን ኢሠመኮ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ኮሚሽኑ እንደሚለው፤ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ መደበኛ ፖሊሶችና  ሚሊሻዎች በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ሲሆን  ከጸጥታ ኃይሎች ጋር የተባበሩ የተወሰኑ ወጣቶች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡
የፀጥታ ኃይሎቹ “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና መሳሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል፤ የደበቃችሁትን መሳሪያ አውጡ” የሚል ምክንያትም እየሰጡ ነበር  ተብሏል፤በሪፖርቱ።
የኦነግ ሸኔ እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎችም ውጊያው በተካሄደበት ዕለት “ተኩሳችሁብናል” በሚል ምክንያት በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ ያገኟቸውን ቢያንስ ሰባት ሰዎች መግደላቸውን ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም፣ በተኩስ ልውውጡ ወቅት በየትኛው አካል እንደተገደሉ ያልታወቁ ስድስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉንም ሪፖርቱ አመልክቷል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ  ከውጊያው በኋላ ባደረገው ማጣራት፣ የክልሉ ልዩ ኃይሎች ሰኔ 8 እና ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማዋ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ገልጾ፣ መወሰድ ያለባቸውን ተጨማሪ  ሕጋዊ እርምጃዎችን መጠቆሙም ተመልክቷል፡፡
“የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ተጎጂዎች ፍትሕና ተገቢውን የካሳና መልሶ የመቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙና” ተፈጻሚነቱንም እንደሚከታተል ኢሰመኮ አሳስቧል።


Read 10771 times