Saturday, 01 October 2022 12:05

ካፑችኖ፣ የዮሐንስ ሐሳቦች

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(0 votes)

“ልብወለድ በተዋበ ቋንቋ የተጻፈ ፍልስፍና ነዉ”

ክፍል አንድ
ይህ ጽሑፍ የዘመናችን ጎምቱ ልብወለድ ጸሐፊ እና ገጣሚ ዮሐንስ ኃብተማርያም ታላቅ የልብወለድ ሥራ በሆነዉ ካፑችኖ (2009) ላይ አትኩሮቱን ያደረገ ነዉ፡፡ ዮሐንስ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ነዉ፡፡ በሥራ ቆይታዉ በርካታ የግጥም እና የልብወለድ ሥራዎችን ማበርከት የቻለ አምራች (prolific) ጸሐፊ ነዉ፡፡ ደራሲዉ በግሉ በእዚህ ጽሑፍ የምዳስሰዉን ካፑችኖ የተሰኘዉን የአጫጭር ልብወለዶች መድበል እና ቀለም ሰዉ አምላክ (2008) የተሰኘዉን የግጥም መድበል ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ ከሌሎች ጸሐፍት ጋር ደግሞ በደቦ መስቀል አደባባይ (2007) እና ግጥም በመሰንቆ (2007) የተሰኙትን የግጥም መድበሎች እና አልፋ ተረክ (2011) የተሰኘዉን የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ለህትመት አብቅቷል፡፡ ዮሐንስ በዘመናችን ወጣት ልብወለድ ጸሐፍት እና ገጣሚያን ላይ ሙያዊ ተፅዕኖን የፈጠረና ብዙዎችም ፍሬአማ እንዲሆኑ በሙያዉ ያገዘ ጸሐፊ ነዉ፡፡ ሥነ ጽሑፍ በትዉልድ ቅብብል እያደገ የሚሄድ ኪናዊ ሥራ መሆኑን ከተገነዘቡ ጸሐፍት መካከል አንዱ ነዉ፡፡  
ዮሐንስ የድህረ ዘመናዊ ልብወለድ አጻጻፍ ቴክኒኮችን ሕፅናዊነትን (ቃሉ የአዳም ረታ ነዉ) (intertextuality)፣ ኢ-ቀጥተኛ ትረካን (nonlinearity)፣ ድቅል ታሪክን (stories within stories)፣ ፀሊም ለዛን (dark humor) (ተጠርጣሪዎቹን እና እኔ እና የጓደኛዬ  ትዕንግርትን ተመልከት) እና አስማተ ገሀድን (magic realism) በሥራዎቹ ዉስጥ ያቀረበ ድህረ ዘመናዊ ልብወለድ ጸሐፊ (postmodernist novelist) ነዉ፡፡ ዮሐንስ ድህረ ዘመናዊ ጸሐፊ ብቻ አይደለም፣ እዉናዊ ልብወለድ ደራሲም (realist novelist) ነዉ፡፡ እዉናዊ ልብወለድ የሚያተኩረዉ በዘወትራዊ የሰዉ ልጅ አኗኗር ላይ ነዉ፡፡ በምድረ አሜሪካ የእዉናዊ የሥነ ጽሑፍ ንቅናቄ ዐቢይ አቀንቃኞቹ ሄነሪ ጀምስ እና ማርክ ትዌን ናቸዉ (ማክሚሼል፣ 1985)፡፡ የዮሐንስ የልብወለድ ሥራዎች የሰዉ ልጅን ዝብርቅርቅ የሕይወት መልኮች ሳይኩሉ እንደ ወረደ (ከነግሳንግሱ፣ ከነጉድፉ ሰናዩንም እኩዩንም) የሚያስቃኙ ናቸዉ፡፡ ደራሲዉ የሳላቸዉ አብዛኞቹ ገጸባሕሪያት (የመናፍስት ማኅሌት የተሰኘዉ ትረካ ዉስጥ የተሳሉት ሴተኛ አዳሪዎች፣ ከመስከረም ጷግሜ የተሰኘዉ ትረካ ዉስጥ የተሳሉት ተመፅዋች ሰካራም ገጸባሕሪያት፣ ተጠርጣሪዎቹ በተሰኘዉ ትረካ ዉስጥ የተሳለዉ ቦዘኔ፣ ከማዕረግ ወደ ማዕረግ በተሰኘዉ ትረካ ዉስጥ የተሳለዉ ወንጀለኛ ዓለሙ አያልቅበት እና አበባ  ልብ  ዳይመንድ ጦር ካርታ በተሰኘዉ ትረካ ዉስጥ የተሳሉት የወህኒ ታራሚዎች ዋቢ ናቸዉ) በማኅበረሰባችን የአኗኗር እርከን ወይም ተዋረድ የታችኛዉን መደብ (low socitial class) የሚወክሉ ናቸዉ።
ለዮሐንስ በገሀዳዊዉ ኀልዮ እና በልብወለድ ሥራ መካከል ልዩነት የለም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ነገረ ሕይወት እና ነገረ ተረት እርስ በእርስ የተጋመዱ ናቸዉ፡፡ ዮሐንስ እንደሚነግረን፤ ነገረ ተረት የሰዉ ልጅ ኀልዮ ስንክሳር ድርሳን ነዉ፡፡ በሌላ አገላለፅ፣ ሥነ ተረት የሰዉ ልጅ ምናባዊ ሕይወቱን የቀነበበበት መዝገብ ነዉ፡፡ ስለሆነም፣ የሰዉ ልጅ ህልዉናዉን የሚመራዉ በገሀድ የሚመለከተዉን ተጨባጭ እዉነት ብቻ መሠረት አድርጎ አይደለም፤የፈበረከዉን ተረትም ተቀብሎ እንጂ፡፡ ገሃዳዊ እዉነት ከሳይንስ ጋር የተቆራኘ ነዉ፣ ነገረ ተረት ደግሞ ከሃይማኖት (ሜታፊዚክስ) ጋር፡፡ እነዚህ ሁለቱ የሰዉ ልጅ ፓራዳይም (world view) አምድ ናቸዉ፡፡ የዮሐንስን ሐተታ ሰፋ ስናደርገዉ፣ ሰዉ ነፍስ እና ሥጋ ነዉ፡፡ ሕይወቱም ሳይንስ (empirical world) እና ኪን (art) ነዉ፡፡ እንደ ዮሐንስ እሳቤ፣ ነገረ ሕይወት እና ሥነ ተረት የማይነጣጠሉ መንታ መልኮች ናቸዉ፡፡ ዮሐንስ ተጠርጣሪዎቹ በተሰኘ ሥራዉ ሕይወት ተረት ነዉ ይለናል፡፡ የመኖር ዑደት በራሱ በቀልድና ፌዝ የተቀነበበ ነዉ (ዮሐንስ፤ 2009፡ ገጽ 125)። ዮሐንስ እንዲህ ጽፏል፤ “መኖር መቀለድ ነዉ። ቀልድ ደግሞ ሳቅ መፍጠር ብቻ አይደለም የሁልጊዜ ሥራዉ፡፡ ለምሳሌ … የሰዉ ልጅ ሊሞት መወለድ የለየለት ቀልድ ነዉ … በስርአተ ቀብር ቀልድ ላይ ግን … በዋንጫ የሚሰፈር እንባ እንጂ - - በሐሴት የሚያሳክር ሳቅ የለም” (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 115)፡፡
ካፑችኖ የዮሐንስ ንጽረተ ዓለም የተዳሰሰበት ልጨኛ (ቃሉ የዕዝራ አብደላ ነዉ) (masterpiece) የፈጠራ ሥራ ነዉ፡፡ ካፑችኖ ንጥር ልብወለድ (quality fiction/interpretive literature) (ሦስት አይነት ልብወለዶች እንዳሉ ያስተዉሉ፡ ፐልፕ ልብወለድ (ኢስኬፕ ሊትሬቸር) (ምንጊዜም ሰናይ እኩዩን የሚረታበት ልብወለድ ነዉ)፣ ሲልክ ልብወለድ (ብዙ ጊዜ በወጣቶች የፍቅር ሕይወት ላይ የሚያተኩር ነዉ) እና ንጥር ልብወለድ (ጠጣር ፍልስፍናዎች የሚቀርቡበት ነዉ) (ሳንደርስ፣ 1967፤ ካርተር እና ስኬት፣ 1990)፡፡ የፐልፕ (ኢስኬፕ ሊትሬቸር) እና የንጥር ልብወለድን ልዩነት አስመልክቶ ካርተር እና ስኬት የተባሉ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን ኢለመንትስ ኦፍ ሊቲሬቸር (Elements of Literature) በተሰኘ ሥራቸዉ የሚከተለዉን ሐሳብ ጽፈዋል፡
The purpose of escape literature is to entertain, not to provide insights into human existence (Carte & Skate, 1990). The purpose of interpretive literature is to comment on human existence in a meaningful way (Carte & Skate, 1990: 688).
ካፑችኖ ዮሐንስ ልብወለድ ፍልስፍና የሚቀርብበት ሚዲየም መሆኑን ያሳየበት ሥራ ነዉ፡፡ ዮሐንስ ልብወለድን በእዚህ ደረጃ ተረድተዉ ከሚጽፉ ደራሲያን አንዱ ነዉ። በሥነ ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚዉ ፈረንሳዊዉ ደራሲ እና ፈላስፋ አልበርት ካሙ በፍልስፍና እና በልብወለድ መካከል ድንበር የለም ከሚሉት ደራሲያን አንዱ ነዉ፡፡ እኔም ይኸን የካሙ ሐሳብ የምጋራ ልብወለድ ጸሐፊ ነኝ፡፡ ለእኔ ልብወለድ በተዋበ ቋንቋ የተጻፈ ፍልስፍና ነዉ፡፡ ካሙ እንዲህ ጽፏል፤ “A novel is never anything but a philosophy expressed in images.” (“ልብወለድ በዐይን የሚታይ ምሥል ሆኖ የቀረበ ተጨባጭ ፍልስፍና እንጂ ሌላ ጉዳይ አይደለም።”) ለካሙ መሬት ያልወረደ ፍልስፍና ፋይዳ ቢስ ነዉ፡፡ ካሙ ከተጨባጩ ዓለም የሰዉ ልጅ ኀልዮ ተግዳሮት (existential human predicament) የራቀዉ ረቂቁ የአዉሮፓ ፍልስፍና (speculative philosophy) እርባና ቢስ ነዉ ብለዉ ጠንካራ ትችት ከሰነዘሩ ኤግዚስቴንሻሊስት ፈላስፎች አንዱ ነዉ፡፡ ለካሙ እጅግ አንገብጋቢዉ የፍልስፍና ጥያቄ የሕይወት ትርጉም ነዉ፡፡ እንደ ካሙ እሳቤ፣ ከእዚህ ወሳኝ ጥያቄ ይልቅ ረቂቅ የፍልስፍና ጥያቄዎች ላይ ጊዜን ማጥፋት ከንቱ ተግባር ነዉ፡፡ ካሙ ዘ ሚዝ ኦፍ ሲሲፈስ ኤንድ አዘር ኢሴይስ (The Myth of Sisyphus and Other Essays) በተሰኘ ታላቅ የፍልስፍና ሥራዉ እንዲህ ጽፏል፡-
Judging whether life is or is not worth living amounts to answering the fundamental question of philosophy. All the rest—whether or not the world has three dimensions, whether the mind has nine or twelve categories—come afterwards. These are games. . . . I have never seen anyone die for the ontological argument . . .  the meaning of life is the most urgent of questions (Camus, 1955: 3-4).
ልብወለድ በባሕሪዉ የደራሲዉ (የፈጣሪዉ) ንጽረተ ዓለም ነፀብራቅ ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የልብወለድ ሥራ የደራሲዉ የነፍስ አሻራ (ሥብዕና (personality trait)፣ ንጽረተ ዓለም (world view) እና ፍላጎት (intention)) የታተመበት ነዉ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ አቋሜ ግለ ታሪክ ሃያሲያን (biographic critics) የሚጋሩት ሚዛን የሚደፋ አቋም ቢሆንም የፎርማሊስቶች ተፃራሪ ሙግት የሚቀርብበት ነዉ፡፡ ባርኔት፣ በርማን፣ ቡርቶ እና ኬን (2001)፤ አብካሪያን እና ክሎትዝ (1994) እንደጻፉት፤ ለፎርማሊስት ሃያሲያን (formalist critics) የልብወለድ ሥራ ከደራሲዉ ግለ ታሪክም ሆነ ከተጻፈበት ዘመን አዉድ ወይም መንፈስ ተፅእኖ ነፃ የሆነ ጥበባዊ ሥራ ነዉ፡፡
 Formalist criticism emphasizes the work as an independent creation, a self-contained unity, something to be studied in itself, not as part of some larger context, such as the author’s life or a historic period. This kind of study called formalist criticism because the emphasis is on the form of the work, the relationship between the parts – the construction of the plot, the contrasts between characters, the functions of rhymes, the point of view, and so on (Barnet, Berman, Burto & Cain, 2001: 1591).  
Formalist critics assume that a literary text remains independent of the writer who created it. The function of the critic, then, is to discover how the author has deployed language to create (or perhaps failed to create) a formal and aesthetically satisfying structure. The influential American formalists of the the 1940s and 1950s (the New Critics) were found of describing literary texts as “autonomous,” meaning that poltical, historical, biographical, and other considerations were always secondary if not irrelevant to any discussion of the work’s merits (Abcarian & Klotz, 1994: 1265).   
በእዚህ ጽሑፌ የዳሰስኳቸዉ ትረካዎች በካፑቺኖ መድበል ዉስጥ ከቀረቡት አሥራ ስምንት ትረካዎች ዉስጥ የተመረጡ ናቸዉ፡፡ እነዚህን ሥራዎች የቃኘሁት ሁለት የልብወለድ መፈከሪያ አቀራረቦችን (literary critical approaches) መሠረት አድርጌ ነዉ፡፡ እነዚህ ሁለት የልብወለድ መፈከሪያ አቀራረቦች ቅርፃዊ የመሄሻ አቀራረብ (formalist criticism) እና እንስታዊነት የመሄሻ አቀራረብ (feminist criticism) ናቸዉ፡፡
፩. ልብወለዶቹ የተጻፉበት ቋንቋ (diction)
የልብወለድ ኪን ዋናዉ ሚዛን (aesthetic criterion) ቋንቋ ነዉ፡፡ የማንኛዉም ልብወለድ ደራሲ ክህሎት ታላቅነት የሚመዘነዉ የምናብ ሥራዉን በጻፈበት ቋንቋ ምርጫ (word choice) ነዉ፡፡ ዮሐንስ ልብወለድን በነጠረ ቋንቋ ከሚጽፉ ዘመነኛ ጸሐፍት አንዱ ነዉ። የዮሐንስ ቃላት በትረካዉ ያቀረበልንን ስሜት (tone) እሳትን ቀርቦ እንደ መሞቅ ዉስጣችን እንዲዋሀድ የማድረግ ኃይል ያላቸዉ ናቸዉ። ዮሐንስ የቱ ቃል የቱን ቶን በትክክል እንደሚፈጥር (የትኛዉ ቃል የትኛዉን ስሜት እንዴት ባለ ጥልቀት (intensity) እንደሚገልፅ) ጠንቅቆ የሚያዉቅ ለድርሰት የተፈጠረ ጸሐፊ (professional novelist) ነዉ፡፡  ፍልስፍናዉ ጠጣር ነዉ፣ ታሪካችን ላይ ያነሳዉ ትችት (critique) ብርቱ ነዉ፡፡ ልብወለድ አንባቢ እንዲያሰላስል፣ እንዲፈላሰፍ የሚጋብዝ ሐሳብ ይዞ መቅረብ አለበት፡፡
የዮሐንስ ጎምቱ ደራሲነት ዋናዉ ምስክር ምናቡን የከተበበት ቋንቋ ነዉ፡፡ የዮሐንስ ቋንቋ እንደ ወርቅ የነጠረ (high diction) ነዉ፡፡ ከእዚህ በታች የቀረቡት ከሥራዎቹ ቀንጭቤ የወሰድኳቸዉ ትረካዎች ይኸን አተያዬን የሚያስረግጡ ናቸዉ፡-
“ካንቺ’ኮ ነዉ ፍቅር የያዘኝ” ስልሽ … ቁመቱ ከአርያም የሚረዝም - - መሠረቱ ከበርባሮስ የሚጠልቅ - - ሳቅ ሳቅሽ … ሳቅ እንዲህ መጨረሻ አልባ ሆኖ ይረዝማል? ሳቅ እንዲህ ከፀሐይ ሰባት እጅ ልቆ ያንፀባርቃል? ሳቅ እንዲህ ከመንፈስ ልዕልና ጉልላት ላይ አፍቃሪን ያስቀምጣል?
ቤተሰቦቼ … እነዚህ ዘር እንደ ገለባ አንጓላይ- - ቤተሰቦቼ … እነዚህ ዘር እንደ ኮከብ ቆጣሪዎች- - ቤተሰቦቼ … እነዚህ ዘር እንደ እርከን ተላሚዎች- - ቤተሰቦቼ … አንቺን አፈቀረ በሚል ሰበብ- - ከሐብታቸዉ መጠጊያ እንደሌለዉ ምናምንቴ ቆጥረዉ ገፉኝ … ከአዱኛቸዉ መከታ እንደሌለዉ ወፍ ዘራሽ ነቀሉኝ (ሄራን፣ 2009፡ ገጽ 2-3)፡፡
የዛሬ ፊቷ ለፃረ ሞት አምስት ጉዳይ ሲቀረዉ ነዉ ይዛዉ የመጣችዉ - እንዲህ ሆና ደግሞ አይቻት አላዉቅም፡፡ ቋት አልባ - ስምጥ ሽብሯ ፊቷ ላይ እንደመንጋ ግሪሳ ይርመሰመሳል፡፡ ደግሞ ዛሬ ምን ገጥሟት ይሆን? ምላሷ ሳይበጠር - እንደተንጨፈረረ አፏ ዋሻ ዉስጥ ተቀምጧል። እንደፈራሁት ሳታበጥረዉ ወሬ ጀመረችበት (ሽንቁሬን በካንሰር፣ 2009፡ ገጽ 10)፡፡
እዉነትም ርጥብ ምኞት ነበረኝ - - ጭቃ ሰፈር ዉስጥ የምኖር - ርጥብ ምኞት የነበረኝ ርጥብ ልዕልት - - ፍቅር የለመለመብኝ ርጥብ ሴት - - ኅልቁ በሆነዉ ርጥባኔ መንደሬዉን ሁሉ ‘የሷ ሰፈር ልጅ እኮ ነኝ’ የሚል ርጥብ ኩራት የለገስኩት - ርጥብ ምትሀት - - የተረሳ እነሱነታቸዉን - የግንዛቤ ክብሪት ለኩሼ - ወደ እሳትነት ከፍ በማድረግ - ከቁብ እንዲጣፉ ያስቻልኩ ክብርት - - - ታጥቦ ጭቃ ቢሆንም ነገራቸዉ (ርጥብ ምኞት፣ 2009፡ ገጽ 37)፡፡  
እዉነት ሚጡ ለምትባል ፍቅረኛ እንዲህ ይመከራል-? በእሳት መጫወቷን ለወደደች ጉብል እቶን ያስታቅፏታል እንዴ - ? ማን ይሆን አዋቂዉ- - - የመጽሐፍ ተባይ መሆን የኑሮን ብልሀት ማግኘት አይደለምና ለካ - - ለካንስ ያለን ነገር ሁሉ ከመጽሐፍ ይገኛል ማለት ዘበት ነዉና - - መኖር ዉስጥ ያልተንቦጫረቀ ለካን ምልዓት የለዉም - - በመከራ ቀን መሸሸጊያ ፈጣሪ እንጂ መጽሐፍ አይደሉም ለካ - - (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 60)፡፡
‘- - - ዛሬ መሥራት አለባት - አታልቅም - ይህች ዓለም ትጀምራለች እንጂ አትጨረስም - - - ከማነቆ - ከማኅበረሰብ  እግረ - ሙቅ መፈታት - - - ሰማያት ዐይን አላቸዉ - ያያሉ - - - ፍርሃትን ምን አመጣዉ!? ምድር ሁለመናዋ ብሌን ነዉ - ፈጠጣዋ ፍጡር ሁሉ ላይ ነዉ - - - ሽርሙጥና ሞትን በደንዳና ገመድ ወደ ራስ መሳብ አይደለም - - - መሸጥ ከተለመደ - ማምለጥ - ማምለጥ - ከተራራ ርካብ በላይ - - - ከአምላክ ጣራ በላይ ማለፍ - - - መብረር - መክነፍ - - - አዋጁን በጆሮ - ከራስ ባይወጣስ? - ግን ኅሊና ከደማ ባይመሰጠርስ? - በአደባባይ ቢለፈፍስ ምን ሊመጣ - - - ? (የመናፍስት ማኅሌት፣ 2009፡ ገጽ 66)፡፡    
‘- - - ሲጨምቱ ኖረዉ - በይሉኝታ ሸምቀቆ ታብተዉ ቀንድ ካበቀሉ በኋላ - ድንገት እንደ ድማሚት የሚፈነዳ እብደት ከማበድ - በደህናዉ ቀን መለማመድ - መወፈፍን እንደ ቤት ባሪያ መጣራት - ጓዙን ጠቅልሎ ሲመጣ በአማን ማስገባት - ወዳጄ ሆይ - እነሆ ወደ እልፍኜ ዝለቅ - ከወገብ የጀርባ አጥንት እንደሌለዉ እባብ ተቀንጥሰዉ ሳይሆን ተስለክልከዉ - - -’ (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 67)፡፡
ሞት ለካ እንዲህ አፍንጫችን ስር ሆኖ የሚሰወር … ሩቅ የሚመስል ፅዋችን ነዉና … የትኛዉ ሰባኪ ነበር “ሞታችን ፈጣሪ በፈቀደ ጊዜ የሚመጣ የበለስ ሽንፈታችን ነዉ” ያለዉ? ዉሸታም ነዉ!
ሞት በጉልበተኞች መዳፍ ላይ ነዉ ያለዉ። የኛ ሞት በአምባ ገነኖች ክርን ላይ ታስሮ ያለ የለመጣ ድቁሻ ነዉ፡፡
እንደ እግዜሩማ ፈቃድ ቢሆን … ገና ብዙ ማየት የሚገባን … ኑሮን አገላብጠንና ተገላብጠንበት ማወቅ የነበረብን … እጅግ ብዙ ሕይወት የሚጠብቀን ወጣቶች ነበርን (ተጠርጣሪዎቹ፣ 2009፡ ገጽ 125)፡፡
ከአዘጋጁ፡ ጸሐፊዉን በቴሌግራም አድራሻው፡- @ MekonnenDefro77 ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1439 times