Saturday, 01 October 2022 11:48

“ሚስት እንጃልህ ስትል፣ ባል እንጃልህ ሲል፣ ቤት ለውሻ ይቀራል!”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ በአንድ አገር ታፍረው ተከብረው ይኖሩ ነበረ። ነገር ግን ልጅ አልወለዱም ነበረና “አገሬ ሰው አልተዋጣላትም፣ ወደፊት ዘውዴን የሚረከበኝና ዙፋኔን የሚወርስ ማን ሊሆን ነው?” እያሉ ሌት ተቀን ይጨነቁ ነበር።
አንድ ቀን በሀገሪቱ ውድድር እንዲደረግና አሸናፊ የሆነ ጀግና ዙፋኑን እንደሚወርስ ሊያውጁ ይወስናሉ። ውድድሩም የፈረስ ግልቢያ ነበረ። ከብዙ ማጣራት በኋላ ጥቂት ተወዳዳሪዎች ነጥረው  ወጡ። የፍፃሜው ውድድር መቼ እንደሚሆን ተወሰነና የሚጋልቡት ርቀት ምን ያህል እንደሚሆን፣ የት ቦታም እንደሚሮጡ ቁርጡ ታወቀ። ተፎካከሩ። ሆኖም ብዙዎቹ ተወዳዳሪዎች እየተመቀኛኙ፣ አንዱ አንዱን እያሰናከለ እንዳይሳካለት ማድረግ ጀመረ። ለፍጻሜው ሦስት ቀሩ።
የመጀመሪያው ሁለተኛው እንዳያሸንፍ  ፈረሱን መርዝ ሊያበላበት ወጠነ።
ሁለተኛው ደግሞ ሦስተኛው እንዳያሸንፍ ሰውየውን ራሱን የሚያደነዝዝ መድሃኒት ሊያጠጣው መላ መታ፡፡
ሦስተኛው ደግሞ የመጀመሪያው እንዳያሸንፍ ፈረሱ የሚሮጥበትን መንገድ በመሰናክል ሊያጥርበት ወሰነ።
ሁሉም ያሰቡትን አሳኩ። ሆኖም ከመጉላላት በስተቀር ምንም ፍሬ ሳያገኙ ቀሩ!
ንጉሡ አዘኑና “ዋ አገሬ! ሰው አልዋጣ አለሽ” አሉ አሁንም።
ስለዚህም ሌላ ፈተና ሊሰጡ አሰቡ። ፈተናውም አደን ሄደው ንጉሡ ያዘዙትን ፈጽመው መመለስ ነው። ተወዳዳሪዎቹ ቀረቡ። የንጉሡ ትዕዛዝ ግን ከወትሮው የተለየ ሆኖ አገኙት። ይኸውም፤
“ሄዳችሁ የፈለጋችሁን ሦስት ነገሮች አድናችሁ ኑ። የምፈልገው ግን እንድትይዙ ወይም ገድላችሁ እንድትመጡ አይደለም። ሦስቱም የምታደርጓቸው ጥረቶች ሳይሳኩላችሁ እንድትመለሱ ነው። ሆኖም ለምን እንዳልተሳካላችሁ እያንዳንዳችሁ እንድትገልፁልኝ እሻለሁ። ይህን መልስ በትክክል ለሰጠኝ መንግሥቴን አወርሰዋለሁ” አሉ።
አዳኞቹ ወደ ጫካ ሄደው በተባሉት መሰረት ሲያድኑ ውለው የማታ ማታ ሁሉም የየግላቸውን መልስ ይዘው መጡ።
ሌሊቱን እያንዳንዳቸው ለምን አደኑ እንዳልተሳካላቸው ሲያብራሩ አደሩ። ከሦስቱ ከአንደኛው በስተቀር ሁለቱ የውሸት የፈጠራ ወሬ ነበር ያወሩት። ውሸቱንም በሚገባ አላቀረቡትም።
ያ ሦስተኛው ተወዳዳሪ ግን የሚከተለውን ተናገረ፡-
“ንጉሥ ሆይ፤ በትዕዛዝዎ መሰረት ወደ ጫካ ሄጄ ሳድን ውዬ ምሽቱ ዐይን ሲይዝ ወደ ቤተ-መንግስትዎ እየሮጥኩኝ ተመልሻለሁ።” አላቸው።
ንጉሡም፤
“እኮ ለምን አደኑ ሳይቀናህ ቀረ? አስረዳና? ለመሆኑ ምን ነበር ለማደን የፈለግኸው?” ሲሉ ጠየቁት።
አዳኙም፤
“ወፎች ለማደን ነበር ንጉሥ ሆይ”
“ሁሉም በረሩ እንዳትለኝ ብቻ?”
“ኧረ አይደለም ንጉሥ ሆይ!
“ታዲያሳ?”
“ንጉሥ ሆይ፤ በርግጥ ሦስት ወፎች ለማደን ነበር የወጣሁት። ግን ሦስቱንም ለመምታት፣ ለመግደልም ሆነ ለመያዝ አልቻልኩም”
“እኮ ለምን?”
አዳኙ ተነስቶ ቆመና፤
“ንጉሥ ሆይ! የመጀመሪያዋን ከሩቅ ነው ያየሁዋት። ሁለተኛዋን ሰማሁዋት እንጂ አላየሁዋትም። ሦስተኛውን ግን ይኼው እስከ አሁኑዋ ሰዓት ድረስ ሳባርራት ነበር። ሰዓቱ ስለመሸ ባዘዙን ሰዓት ለመገኘት ስል ወደርስዎ መጣሁ” አላቸው።
ንጉሡ በጣም ተደሰቱ። እንዲህም አሉ፡-
“ብዙዎቻችሁ ትገርማላችሁ። አንዳንዶቻችሁ ዕውነቱን መግለጽ አትችሉም፡፡ አንዳንዶቻችሁ ደግሞ ከነጭራሹ መዋሸትም አትችሉም። ሌሎቻችሁ ውሸታችሁን ማስረዳት አትችሉም። ከፊሎቻችሁ ውድድር ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባችሁም። ስትመቀኛኙ እድል ያመልጣችኋል። ይሄ ተራ ሰው ግን እቅጯን ነገረኝ። ምነው ቢሉ፣ እሱ እንዳይሳካለት ያደረጉት ሦስት ዋና ዋና ችግሮች የአገራችንም ችግሮች ናቸው። ሦስቱ ችግሮችም-
1. ከሩቅ ሆነን እያየን ዝም ማለት
2. ሳናይ እየሰማን ብቻ ዝም ማለት
3. እያየንም፣ እየሰማንም ዘዴ መሻት አቅቶን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ፤ ናቸው” አሉ ይባላል።
***
በሀገራችን እያየን ዝም ያልናቸው አያሌ ነገሮች አሉ። እየሰማን ዝም ያልናቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። አይተን፣ ሰምተን ለመፍታት በቅጡ ሳንሯሯጥ እስከዛሬ ያልሆኑልንና ያስመሹብን ለቁጥር የሚያታክቱን ጉዳዮች አሉ።
እንደ ሎሬት ጸጋዬ፣ አፄ ቴዎድሮስ፡
“ከዚህ ሌላ ትዝብት ውረሽ፣ ሳይነጋ እንዳስመሸሽብኝ
 ጊዜና ትውልድ ይፍረደን፣ ሳልነቃ እንዳስረፈድሺብኝ።”
የሚያስብሉን ቁጭቶች አሉብን።
ከላይ እንደተጠቀሰው ዕውነቱን ለመግለጽ የማይሹ ሹማምንት አጋጥመውናል። በመሆኑም ከሕዝብ የተሸሸጉ አያሌ የአገር ጉዳዮች፣ ስምምነትና ድርድሮች መካሄዳቸው ይሰማል። አሊያም ከሆኑ በኋላ በዜና ማሰራጫዎች ሲነገሩ ይደመጣል። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ዛሬ ብቻ ሳይሆን የመጣ መሪ እና ኃላፊ ሁሉ ሲተገብረው የታየ ነው። የሕዝብን የማወቅ መብት ከመንፈጉም ባሻገር፣ ሕዝብን መናቅን ይጠቁመናል፡፡ መሪዎች አንዴ የሚመሩትን ሕዝብ መናቅ ከጀመሩ ውለው አድረው ወደ አምባ- ገነንነት እንዲያመሩ በር ከፋች ነውና፣ ቢያንስ ስጋት ላይ ይጥለናል!
አንጋፎች ሲያጠፉ፤ “የዛሬው ባሰ ሽበታም አበደ” ስንል ሰነበትን።
ወጣቱ ሲያጠፋ፤ “አይ የዛሬ ልጅ!” አልን።
አዋቂ ሲያጠፋ፤ “የባሰ አታምጣ!
ተመስገን ይለዋል፣ ሰው ባያሌው ታሞ
ካማረሩትማ ይጨምራል ደሞ” ተባባልን።
ሁሉም ዲሞክራሲንና ሰላምን አላመጡም። ሁሉም ከብሔር ብሔረሰብ ግጭትና ከማናለብኝነት፣ ከመብት ረገጣና ከአመጻ ደፈጣ፣ ጁንታና አምባገነነን ከመባባል አላዳኑንም! ጦርነትና መፈናቀልን እንደ ባህል ከማየት አላወጡንም፡፡ “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባልና” የውስጥ መናቆራችንን አይተው የውጭ ኀይላት ሠለጠኑብን!
በአዲሱ ዓመት ችግሮቻችንን ለማቃለል ያለ ይስሙላ ብንመክር፣ ያለ ድብብቆሽ ብንጓዝ፣ ያለ ሽርደዳ ግልፅ የሚዲያ ንግግር ብናደርግ መልካም ነው!
አዲሱን ዓመት የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ነው ባንልም እንኳ በከፊል ማቃለያና መንገድ መጥረጊያ ልናደርገው ይቻለናል! በአዲሱ ዓመት እንደ መስቀሉ ደመራ  የሁላችን ችቦ በየልባችን ይለኮስ! አዲስ የለውጥ ብርሃን ለማየት እንሞክር! አገራችን የጋራ ቤታች ናት! የጋራ ሃሳብ እናፍልቅባት። የሌሎች መጠቀሚያ እንዳንሆን መግባባትን፣ መረዳዳትንና መወያየትን ዋና መሳሪያችን እናድርግ! አለበለዚያ፣ “ሚስት እንጃልህ ስትል፣ ባል እንጃልሽ ሲል፣ ቤት ለውሻ ይቀራል” የሚባለውን ተረት መተረቻ እንሆናለን!

Read 11938 times