Saturday, 24 September 2022 17:09

ግብረ ሃይሉ ህወሓት በአፋርና አማራ ክልል ሰብአዊ ጉዳት ማድረሱን አረጋግጫለሁ አለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ከ2200 በላይ ሴቶች በህወሓት ሃይሎች ተደፍረዋል
                       
          በኢሰመኮ እና በተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ የጣምራ ምርመራ ቡድን  ምክረ ሃሳብ መሰረት የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል፣ ህውሓት በወረራ በገባባቸው የአማራና አፋር ክልሎች ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት ማድረሱን በምርመራ ማረጋገጡን ገልጿል።
ባለፈው ዓመት ህውሓት በሃይል በያዛቸው የአማራና አፋር ክልል ነዋሪዎች ላይ ከህግ ውጪ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን መፈፀሙን ግብረ ሃይሉ አረጋግጧል።
አብዛኛው ግድያ የተፈጸመው በህወሓት ታጣቂ ሃይሎች መሆኑን ያመለከተው የግብረሃይሉ መግለጫ፤ በተወሰነ መልኩም በሸኔ ታጣቂ ቡድኖች ተፈጽሟል ብሏል።
ከ2 ሺ 200 በላይ ሴቶች በህወሓት ታጣቂ ሃይሎች መደፈራቸውን የጠቆመው የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል፤ ከደህንነት ጋር በተያያዘ በትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጸሙ ጥሰቶችን አለመመርመሩንም አስታውቋል።
በሁለቱ ክልሎች በታጣቂ ሃይሉ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል ያለው ግብረሃይሉ፤ የተፈጸሙት የዘረፋና የንብረት ውድመት ወንጀሎች እጅግ ከፍተኛ መሆናቸውን አመልክቷል።
ይኸው በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ የጣምራ ምርመራ ቡድን ምክረ ሀሳብ የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ሀይል ያወጣውን የምርመራ ሪፖርት፣ የህወሃት ታጣቂ ሀይሎች አንቀበለውም ብለዋል፡፡
ታጣቂ ቡድኑ በአንፃሩ፤ በተመድ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የባለሙያዎች ቡድን ባለፈው ሰኞ ያወጣውን ሪፖርት፣ ራሱን ከሚመለከቱት በስተቀር በአብዛኛው እንደሚቀበለው መግለፁ ይታወቃል፡፡

Read 20970 times