Saturday, 24 September 2022 16:49

የገበታ ጨው በፎሊክ አሲድና በአዮዲን የሚያበለጽግ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዓለማቀፉ የሥነ ምግብ ድርጅት ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናልና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፤ በፎሊክ አሲድና በአዮዲን የበለጸገ የገበታ ጨው የሙከራ ምርትን ለማምረትና ተቀባይነቱን ለመፈተሽ የሚያስችል እንዲሁም የነርቭ ሕዋሳት ቱቦ የአፈጣጠር እንከኖችን የሚቀንስ ፕሮጀክት ባለፈው ማክሰኞ በካፒታል ሆቴል በጋራ ይፋ አድርገዋል፡፡
በአዮዲንና በፎሊክ አሲድ የበለጸገ ጣምራ የጨው ምርት ፕሮጀክትን በስኬት ለመተግበር ስለሚቻልባቸው መንገዶች ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር ለመምከርና ጠቃሚ ግብአቶች ለመሰብሰብ የሚያስችል ዎርክሾፕ በካፒታል ሆቴል ባለፈው ማክሰኞና ረቡዕ  መካሄዱ  ታውቋል፡፡
“የነርቭ ቱቦ እንከኖች ገና በጽንስ የሚፈጠሩ ጉዳቶችን የሚመለከት ሲሆን ይህም በእንግሊዝኛው “አነንሴፌሊ” የሚሰኘውን በአንጎል ውሃ መቋጠር የተነሳ  ጨቅላ ህጻናት የተጓደለ የአንጎልና የራስ ቅል ክፍሎች ይዘው የሚወለዱበትን ክስተት እንዲሁም “ስፒና ቢፊዳ” ተብሎ የሚጠራውን  በጀርባ አጥንት ክፍተት የተነሳ ህጻናት ያልተስተካከለ ኅብለ-ሠረሰር ይዘው የሚወለዱበትን ሁኔታ ያጠቃልላል፡፡” ብሏል፤ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል በመግለጫው፡፡
“የነርቭ ቱቦ እንከኖች የሚፈጠሩት በመጀመሪያዎቹ 18 የእርግዝና ቀናት ውስጥ ሲሆን በዚህ ወቅት ላይ አንድ እናት መጸነሷን እንኳን የማወቅ አጋጣሚዋ አናሳ ስለሚሆን አስፈላጊውን የቅድመ ወሊድ ክትትል በማድረግ ችግሩን የመከላከል ዕድሉ የጠበበ ነው፡፡ አነንሴፌሊ የተወለደ/ችውን ጨቅላ ህጻን ባጭር ጊዜ የሚገድል ሲሆን በስፒና ቢፊዳ ተጠቅተው የተወለዱና ከሞት የተረፉ ሕጻናት ደግሞ በህክምና እገዛ እንኳን ለዕድሜ ዘመን የሚዘልቅ ጉዳት ይዘው እንዲኖሩ ይገደዳሉ፡፡” ይላል፤ መግለጫው በማብራሪያው፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በነርቭ ቱቦ እንከኖች ተጠቅተው በህይወት የሚወለዱ ጨቅላዎች ምጣኔ ከ1ሺ ውልደቶች ውስጥ 13.8 ያህል የሚደርስ ሲሆን ይህም ከ1 እስከ 2.5 ምጣኔ ካለው ከአፍሪካ አማካይ ጋር ሲነጻጸር እጅግ የሚልቅ ከመሆኑም በላይ ብርቱ ግለሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኪሳራን እያስከተለ ይገኛል፡፡
በአንጻሩ የነርቭ ቱቦ እንከኖችን ለመከላከል የሚያስችለውን የፎሊክ አሲድ ንጥረ ምግብን ከመደበኛ መብሎች ለማግኘት ለብዙ ሰዎች አዳጋች መሆኑን ያመለከተው ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል፤ ተፈላጊውን ንጥረ ምግብ በተገቢው መጠን ለማቅረብ እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ዘይትና የመሳሰሉ እጅግ በሚበዛው ህዝብ ዘንድ ተዘውትረው የሚበሉ መደበኛ ምግቦችን ወይም እንደ ስኳር፣ ጨው፣ የቲማቲም ድልህና የመሳሰሉ ማባያዎችን በፎሊክ አሲድ የማበልጸግ አሰራር አንደኛው አማራጭ ነው ብሏል፡፡
በፎሊክ አሲድ የማበልጸግ መጠነ ሰፊና አስገዳጅ መርሃ ግብርን በተገበሩ ሃገራት ዘንድ የነርቭ ቱቦ እንከኖች ክስተት ምጣኔ በተከታታይ ቀንሶ በህይወት ከተወለዱት 1ሺ ጨቅላዎች መካከል ከ0.5 እስከ 0.6 ድረስ ወርዷል ያለው መግለጫው፤ በዚህም መሠረት ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የሚመረት እንዲሁም የፎሊክ አሲድና የአዮዲን ንጥረ ምግቦች የተካተቱበትን ጣምራ የገበታ ጨው ምርት ፕሮጀክትን መንደፉን አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ 25 ሚሊዮን 350ሺ በወሊድ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶችን እንዲሁም 11 ሚሊዮን 653ሺ ታዳጊ ልጃገረዶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የጠቆመው ተቋሙ፤ ይህም በዘንድሮው ዓመት ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ይደርሳል ብሎ ከተተነበየው አኃዝ ውስጥ ከ35 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው ተብሏል፡፡
ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ልገሳ ከ2014 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ በሚተገበረው በዚህ  ፕሮጀክት፤ በፎሊክ አሲድና በአዮዲን የበለጸገ የገበታ ጨው ምርት በሙከራ ደረጃ የሚዘጋጅና የገበያ ተቀባይነቱም ላይ ጥናት የሚካሄድበት ይሆናል ተብሏል፡፡
በፕሮጀክቱ መገባደጃ ላይም የጥናቱና የገበያ ፍተሻው ውጤቶች በይፋ የሚታተሙ ሲሆን በአዮዲንና በፎሊክ አሲድ የዳበረ የገበታ ጨው አስገዳጅ ደረጃን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ሊተገብራቸው የሚገቡ የህግ ማዕቀፍና የፖሊሲ እርምጃ ምክረ ሃሳቦች እንደሚካተቱበት ይጠበቃል ተብሏል፡፡

Read 11197 times