Saturday, 17 September 2022 13:23

“እህቴን” ፊልም የፊታችን ማክሰኞ ይመረቃል ፡፡

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   በደራሲያኑ ዮሴፍ ተክሉ፤ በረከት ተከስተና ኤርሚያስ ገ/ሚካኤል ተፅፎ በዮሴፍ ተክሉ የተዘጋጀው “እህቴን” ፊልም ማክሰኞ መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በዓለም ሲኒማ ይመረቃል፡፡ የልብ አንጠልጣይ በድርጊት የተሞላ ዘውግ ያለው ፊልሙ በተለይ ማርሻል አርት በተለይም ቴኳንዶ ስፖርት የሰዎችን ስብዕና በመገንባት ጠንካራ ፤ በራሱ የሚተማመንና ጥቃትን የሚከላከል ትውልድ የመገንባት ጥበብ ያለውን ጉልህ ሚና አጉልቶ ያሳያል የተባለ ሲሆን፤ የ5ኛ ዳን ጥቁር ቀበቶ ባለቤት የሆነው ማርሻል አርቲስት ሳቦም ኤሊያስ ኩመል በመሪ ተዋናይነት እንደተወነበትና የ100 ደቂቃ ርዝመት እንዳለውም ታውቋል ፡፡ በቢኬ ታለንት ፊልም ፕሮዳክሽን በተዘጋጀው በዚህ ፊልም ላይ ከኤሊያስ ኩመል በተጨማሪ ቅድመ ዓለም ውሂብና ትዝታ ጥበበ በዋናነት እንደተውኑበትም ታውቋል ፡፡ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ የማርሻል አርት ስፖርት አድናቂዎች ፤ትላልቅ የሙያው ባለቤቶች፤ ለፊልሙ ትብብር ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ሀላፊዎች፤ የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ተብሏል፡፡ ፊልሙ ከመስከረም 10 ጀምሮ በሁሉም የግልና የመንግስት ሲኒማ ቤቶች ለእይታ እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡


Read 31273 times