Monday, 19 September 2022 00:00

“ሃይኒከን አዲስ ቤት ሳይሆን አዲስ ህይወት ነው የሰጠን”

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ሃይኒከን ኢትዮጵያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ሲሆን መንግስት በደሌና ሀረር ቢራን ወደ ግል ይዞታነት ባዘዋወረበት ወቅት እነዚህን ፋብሪካዎች በመግዛት ነበር ወደ ሥራ የገባው፡፡ በኋላ በቂሊንጦ ተጨማሪ ፋብሪካ በመክፈት፣ የምርቶቹን አይነት  ከሁለት ወደ ስምንት                አሳድጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ 1 ሺህ በላይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው ሃይኒከን ኢትዮጵያ፤ ጎን ለጎንም ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ከነዚህ መካከል “ደራሽ” የተሰኘው ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በሃይኒከን ኢትዮጵያ የህዝብ፤ የውጭና የመንግስታዊ ጉዳዮች  ሀላፊ ከሆኑት ከአቶ ፍቃዱ በሻህ ጋር ባደረገችው ቆይታ በተለይ “ደራሽ” በተሰኘው ፕሮጀክት  ዙሪያ ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች::         እስኪ “ደራሽ” ስለተሰኘው ፕሮጀክታችሁ አጀማመርና ስለሰራቸው ስራዎች ያብራሩልኝ?
“ደራሽ” የተሰኘውን ፕሮጀክት የጀመርነው ከህዝብ ችግር ተነስተን ነው፡፡ እዚህ ከተማ ውስጥ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ አንዱና ዋነኛው የቤት ችግር ነው፡፡ እኔ እዚህ ከተማ ውስጥ ተወልጄ እንደ ማደጌ፣ ከተማው ውስጥ ያለውን የቤት ችግርና ኑሯችንን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት አዲስ አበባ ውስጥ ካሉት ችግሮች የትኛውን እንቅረፍ ብለን ስንነሳ፣ ዋነኛውና ቀዳሚውን፣ የቤት ችግርን መረጥን፡፡ ከዚያ በኋላ ለተቸገሩ ሰዎች እውነተኛ ድጋፍና እገዛ እናድርግ አልንና፣ ፕሮጀክቱንም “ደራሽ” አልነው፡፡ ለተቸገሩ ሰዎች ለመድረስ ማለት ነው፡፡ እንደምታውቂው በባህላችን ለችግሬ ደረሰችልኝ (ደረሰልኝ)፣ የችግር ቀን ደራሼ እንላለን፡፡ ለተቸገሩ ሰዎች እውነተኛ ድጋፍና ደራሽ ለመሆን ስለተነሳን ስያሜውንም “ደራሽ” ብለነዋል፡፡
መቼ ነው “ደራሽ” የተቋቋመው?
የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ2018  ዓ.ም  ነው፡፡ የመጀመሪያ ፕሮጀክታችን ልደታ አካባቢ ከረዩ ሰፈር የሚባል ቦታ ላይ ነበር፡፡  እዛም እንደዚሁ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆነ እጅግ ለኑሮ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ለሚኖሩ ሰዎች ነበር የደረስነው፡፡ መጀመሪያ ጊዜያዊ መጠለያ ሰጠናቸውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ የሆኑ 53 ቤቶችን ገንብተን አስገባናቸው፡፡ አሁን በነዚህ 53 ቤቶች ውስጥ ከ350 በላይ ቤተሰቦች በጥሩ ሁኔታ እየኖሩ ነው፡፡  
ከዚያ ቀጥሎ የሄድነው ቀጨኔ ነው፡፡ ቀጨኔም እንደዚሁ በሰዎች ላይ ሊፈርስ የደረሰ ቤት ነበረ፡፡ ሰዎች በንጉሱ ዘመን በተሰራ በጣም አሮጌ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበርና፣ ያንን ቤት ሙሉ ለሙሉ አፍርሰን ግራውንድ ፕላስ 1 (ባለ አንድ ፎቅ ቤት) ሰርተን አስገባናቸው፡፡ ዛሬ በጨርቆስ አካባቢ እኔና አንቺ ቆመን የምንናገርበት ደራሽ 3 ፕሮጀክታችን ነው፡፡ እነዚህም ወገኖቻችን ቆርቆሮ በቆርቆሮ በሆነ፣ እጅግ በተፋፈገ ሁኔታ ነበር የሚኖሩት፡፡ በነዚህ ሰዎች መካከል ምስጢር የሚባል አንዱን ቤተሰብ ከሌላው የሚከልል ነገር አልነበረም፡፡ ቅድም ከተጠቃሚዎች አንዱ ሲናገር እንደሰማሽው፤ “የምንኖረው ለነዚህ በጎች በማይመጥን ቤት ውስጥ ነበር” ብሏል፡፡ ዛሬ ከዚያ አስቸጋሪ ህይወት ወጥተው በዚህ በባለ አንድ ፎቅ ዘመናዊ ቤት ለመግባት ቁልፍ አስረክበናቸው፣ በዓሉን በጥሩ ሁኔታ ለማሳለፍ ሽርጉድ እያሉ ነው (ቃለ ምልልሱ የተደረገው ሐሙስ ጳጉሜ 3 ቀን ነው)፡፡ ከዚያ ትቢያ ላይ ተነስተው ይህን የመሰለ ዘመናዊ ቤት ውስጥ ሲገቡ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል መገመት ትችያለሽ፡፡
ምን ያህል ቤቶች ናቸው በደራሽ 3 ለነዋሪዎች የተሰሩት ?
ፎቅና ምድር ላይ ያሉ 50 ቤቶች ናቸው፡፡ 50 አባወራዎች ከነቤተሰባቸው በድምሩ 250 ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ፕሮጀክት ነው፡፡ አጠቃላይ ወጪው 17 ሚሊዮን ብር ሲሆን ግንባታው የፈጀው ሁለት ወር ተኩል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና እገዛ ትልቅ ነው፡፡
በፕሮጀክቱ  የከተማ አስተዳደሩ ሚና ምንድን ነው?
የከተማ አስተዳደሩ እነዚህ ሰዎች ከዚህ ተነስተው ሲሄዱ መጠለያ ውስጥ አስቀምጧቸዋል፡፡ በመጨረሻም እኛ ቤቱን ሰርተን የምናስረክበው ለመንግስት ነው፤ምክንያቱም ቦታው የመንግስት ስለሆነ፡፡ ሌላው ይህ ፕሮጀክት ከተጀመረ አንስቶ ከፍተኛ ክትትል ያደርግ ነበር፤ከተማ አስተዳደሩ፡፡ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ሳይቀር ከንቲባዋ እየመጡ ይጎበኙት ነበር፡፡ የወረዳና የክፍለ ከተማ ስራ አስፈፃሚዎችም ሲያበረታቱን ነበር፡፡ በአጠቃላይ በትብብር የተሰራ ቤት ነው፡፡
የልደታው ከረዩ ሰፈርና የቀጨኔው ቤት ግንባታ ምን ያህል ወጪ ወጣባቸው ?
እንደምታውቂው በየጊዜው የግንባታ ቁሳቁስ ዋጋ እየጨመረ ነው ያለው፡፡ ለከረዩ ሰፈር ቤት ግንባታ 13 ሚሊዮን ብር ነበር ያወጣነው፡፡ ለቀጨኔው 11 ሚሊዮን ብር የወጣ ሲሆን ደራሽ 3 ፕሮጀክት ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ 17 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ በቤት ደረጃ የከረዩው 53 ቤቶች፣ የቀጨኔው 27 ቤቶች፣ የአሁኑ የጨርቆሱ ደግሞ 50 ቤቶች ናቸው የገነባናቸው፡፡
በቤት ማስረከብ ስነ ስርዓት መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የሃይኒከን ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ሂዩበር ኢዜ፤እዚህ በችግር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ቤት ሊሰራላችሁ ነው ሲባሉ የነበራቸው ተስፋ፣ ቀድሞ የነበሩበት ጎስቋላ ህይወት እጅግ ልባቸውን እንደሰበረውና አሁን ህልማቸው እውን ሆኖ ፊታቸው ላይ ያዩትን ፈገግታና ደስታ እያነፃፀሩ ሲገልፁ ሰምተናል፡፡ እርስዎ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ምን ተሰማዎት?
እጅግ ደስ ብሎኛል፡፡ እንደነገርኩሽ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ፤ ያለውን የቤት ችግር፤ የኑሯችንን ጉስቁልና ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ እንኳን ይህን ሁሉ ህዝብ ከዚህ አስቸጋሪ ኑሮ ማላቀቅ ቀርቶ አንድንም ሰው ማትረፍ ቀላል አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እኔ በግሌ ከኪሴ አውጥቼ ባልሰራላቸውም፣ የምሰራበት ተቋም ይህን ሲያደርግ በቅርብ ፕሮጀክቱን ተከታትዬ ማስፈፀሜና የሰዎቹን ደስታና ተስፋ ማየቴ በጣም ያስደስተኛል፡፡ እንደምታያቸው በጣም ደስተኞች ናቸው፡፡  አዲስ ዓመትን ዋነኛ ችግራቸው ተቀርፎ፣ በአዲስ ቤት በአዲስ ምዕራፍ ሲያሳልፉ ማየት ስሜቱ ጥልቅ ነው፡፡ እናም ደስ ብሎኛል ባጭሩ፡፡
በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ በደራሽ ፕሮጀክት ለችግረኞች ቤት ከመገንባት ባለፈ በተለይ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የስራ እድል ፈጠራ ላይ እየሰራችሁ እንደሆነ ገልፃችሁ ነበር፡፡ ለሴቶች ስለፈጠራችሁት የስራ ዕድል ማብራሪያ ቢሰጡኝ ?
በዚህ የስራ ዕድል 40 ሴቶች ስራ ማግኘት ችለዋል፡፡ የስራው አይነት መልሶ ጥቅም ላይ የሚውል የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ (Reuseable Female Sanitary Pad) የሚባል ማቴሪያል ማምረት ነው፡፡ በመጀመሪያ ሴቶቹ ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ ፓዶቹ እንዴት እንደሚዘጋጁና እንደሚሰፉ በደንብ ከሰለጠኑ በኋላ ማሽን ይሰጣቸዋል፤የሚሰሩበትን ቦታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያ ያመርቱና ምርቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ይረከባቸዋል፡፡
ገበያ ፍለጋ አይቸገሩማ?
አዎ! ገበያ ፍለጋ አይሄዱም፡፡ ምክንያቱም እንደምታውቂው በሀገር አቀፍ ደረጃ እኔ ባለኝ መረጃ፣ ትምህርታቸውን ከሚያቋርጡት ልጃገረዶች 50 በመቶ ያህሉ በንፅህና መጠበቂያ እጦት እንደሆነ ነው፡፡ ትምህርት ቢሮውም ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ችግሩን ለመቅረፍ ከሴቶቹ ምርቱን የሚቀበለው፡፡ ይሄ ነገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም ነው ያለው፡፡ አንደኛ እናቶች በደራሽ ፕሮጀክት ቤት አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ የስራ ዕድል ተጠቃሚም ናቸው፡፡ ሶስተኛው ጉዳይ የንፅህና መጠበቂያ ፓድ በማጣት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ሴት ልጆቻችንን ቁጥር እንቀንሳለን ማለት ነው፡፡ በዚህ አይነት 40ዎቹ ሴቶች ስልጠና አግኝተው የመስሪያ ማሽንና የመሥሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው ስራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ሌላው በግሌ ያስደሰተኝ ባዶ አዲስ ቤት ብቻ አይደለም ያስረከባችኋቸው፤ የበዓል መዋያውንም ጭምር ነውና ምን ምን ሰጣችኋቸው? የዚህስ በጀት ምን ያህል ነው?
እውነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የበዓል መዋያ ስጦታ ያበረከትነው እዚህ ብቻ አይደለም፡፡ አንዱ ፋብሪካችን ለሚገኝበት ለቅሊንጦ አካባቢ 100 ሰዎችም ስጦታ ሰጥተናል፡፡ እዚህ ለሚገኙት ለጨርቆስ 50 አባወራ ቤት ተረካቢዎች በድምሩ ለ150 አባወራዎች የበዓል ሥጦታ አምጥተናል፡፡ እያንዳንዱ አባወራ በግ፣10 ኪሎ ሽንኩርት፣  አስር ኪሎ ዱቄትና ሁለት ኪሎ ቡና አግኝቷል፡፡ ለዚህ ስጦታ 1.5 ሚሊዮን ብር አውጥተናል፡፡ እነዚህ ሰዎች አዲስ ቤት ሲገቡ ይሄኛው ስጦታ ሲታከልበት፣ እውነተኛ በዓል እንደማንኛውም ሰው አክብረውና ተደስተው ይውላሉ፡፡ እውነተኛ እገዛና ድጋፍ ማድረግ ነው አላማችን ብዬሻለሁ፡፡ አሁን አዲስ ቤት ለመግባት ወለሉን በማፅዳትና በተለያዩ ስራ ላይ ናቸው፡፡ ይሄን ስጦታ ባናመጣላቸው እንደገና ሌላ ትግል ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ አረፍ እንዲሉ ነው ይህንን ያደረግነው፡፡ አንቺም እየዞርሽ ስትጠይቂያቸው ነበር፤ እውነተኛ ስሜታቸውን ሳትሰሚ አትቀሪም፡፡
እኔ ያነጋገርኳቸው አብዛኛዎቹ “ሃይኒከን አዲስ ቤት ሳይሆን አዲስ ህይወት ነው የሰጠን“ ነው ያሉኝ---
እውነት ነው! ከዚያ አስቸጋሪ ህይወት ወጥተው ይህንን በመሰለ ዘመናዊ ቤት መኖር መጀመራቸው አዲስ ህይወት ነው፡፡ እኛም በዚህ ደስተኛ ነን፡፡ እንደ ሃይኒከን ኢትዮጵያ “ከማህበረሰቡ ጋር አብረን እናድጋለን” የሚል መርህ ነው ያለን፡፡
ሃይኒከን ኢትዮጵያ በኪነ ጥበብም በበደሌ ስፔሻል ብራንዱ “ጉማ አዋርድ”ን ስፖንሰር ያደርጋል፡፡ አሁን በቅርቡ በዋሊያ ብራንዱ ከወጣቱ አርቲስት ሮፍናን ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት አድርጓል፡፡ በደራሽ ደግሞ የማህበረሰቡ ዋነኛ ችግር የሆነውን የቤት ችግር በመቅረፍና በሴቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ በመስራት ሀላፊነቱን እየተወጣ ነው፡፡ ከዚህ ሌሎች ምን ሊማሩ ይችላሉ?
ቅድም እንዳልነው እኛ ከማህበረሰቡ ጋር አብረን እናድጋለን የሚል መርህ ነው ያለን፡፡ በፊት በደሌና ሀረር ቢራዎችን ገዝተን ነው ስራ የጀመርነው፡፡ ከዚያ ሶስተኛ ፋብሪካችንን ቂሊንጦ ላይ ስንከፍት ለኛ ዕድገት ነው፤የበለጠ ኢንቨስትመንት ነው፤የበለጠ የስራ ዕድል ፈጠራ ነው፤ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለን አበርክቶም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እኛ በዚህ መልኩ ስናድግ ከዚህ እድገት ደግሞ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ መሆን አለበት እንላለን፡፡ ምክንያቱም እድገታችንም ከማህበረሰቡ የሚመጣ ነው፡፡ ስለዚህ መልሰን ለማህበረሰቡ ማበርከት አለብን፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ሥራዎች ለነፍስም ለስጋም ደስ የሚያሰኝ ነገር አለው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልሽ፣ ከኪሴ ብር አይደለም ይህን የማሰራው፤በኩባንያው ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ለማሰራት ወደዚህ ቦታ በመጣሁ በተመላለስኩ ቁጥር ዛሬም የሚመርቁኝ ምርቃት ውስጤን ዘልቆ ይሰማኛል፡፡ በዚህ ሁላችንም ደስተኞች ነን፡፡ የካምፓኒም ነገር ቢሆን ወደ ህዝብ የእውነት ሲወርድ፣ የነፍስም የመንፈስም እርካታ ይሰጣል፡፡ ሌሎችም በተቻለ መጠን ማህበረሰብ ተኮር ችግሮችን በመቅረፍ ከሰሩና ከተባበርን ያለምንም የውጭ ድጋፍና እርዳታ ችግሮቻችንን በራሳችን መቅረፍ እንችላለን።
የሃይኒከን ኢትዮጵያ አሁናዊ አቅም ምን ይመስላል?
ሃይኒከን ኢትዮጵያ ወደ ኢትዮጵያ የገባው እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ነው፡፡ በመጀመሪያ መንግስት በደሌና ሀረር ቢራዎችን ወደ ግል ይዞታ የማዞር አዋጅ ሲያወጣ፣ እነዚህን ሁለቱን ገዝተን ነው ስራ የጀመርነው፡፡ ከዚያ ቅሊንጦ ሌላ ፋብሪካ ከገነባን በኋላ ስንጀምር የነበሩን ሀረርና በደሌ ቢራ ነበሩና፣ አሁን ላይ እነዛን አስፋፍተን፡- ሃይኒከን፤ዋሊያ፤ሀረር በደሌ ስፔሻል፤ በደሌ ሬጉላር፤ሶፊ በክለርና በቅርብ ጊዜ ለገበያ ቀርቦ ተወዳጅነትን ያተረፈው ብርታት የተሰኘ ከአልኮል ነፃ የሆነ ገብስ ላይ የተመሰረተ ሀይል ሰጪ ምርት ይዘን ቀርበናል፡፡ በአጠቃላይ ምርቶቻችን እነዚህ ሲሆኑ ከ1ሺህ በላይ ሰራተኞች አሉን፡፡ አመታዊ የማምረት አቅሙ ደግሞ 6.5 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ነው፡፡  በመጨረሻም ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ አመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡


Read 9517 times