Print this page
Saturday, 17 September 2022 13:11

“አስታዋሽ ያጣው ወሳኝ ድል”

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 በየትኛውም አካባቢ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ፣ በተለይ ደግሞ በድሬደዋና በአካባቢው በሚኖረው ሕዝብ ዘንድ መረሳት የሌለበት ቀን ነው - ነሐሴ 10 ቀን 1969 ዓ.ም።
ነሐሴ 10 ቀን 1969 ዓ.ም የሶማሌ ጦር የድሬደዋ ከተማን ለመያዝ ከፍተኛ ጦርነት ከፈተ። የከተማው ነዋሪ ሕዝብ መሳሪያ ያለው መሳሪያውን አንስቶ ከመከላከያ ጎን በመሰለፍ የሶማሌን ጦር ወደመጣበት መለሰ። የከተማውን ብቻ ሳይሆን በሰፊውም የአገሩን ዳር ድንበር በማስከበር ከፍተኛ ድርሻ ያለው ተግባር ፈጸመ። መደፈር በፈጠረው ቁጭት፣ የሶማሌ ጦር ተጠራርጎ እንዲወጣ ተደረገ።
በአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ስር በሚገኘው በአካል ጉዳተኞች ተሐድሶ ማዕከል ግቢ ውስጥ፣ የድሬደዋን ጦርነትና ድል 45ኛ ዓመት የሚዘክር ፕሮግራም ተካሂዷል። ፕሮግራሙን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ መከላከያና ፖሊስ ጀግኖች ቨትራን አሶሴሽን ነው። ፕሮግራሙ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙት የመከላከያና የሴቶችና ወጣቶች ቢሮ ሰዎች አልተገኙም። እኔን ቅር አሰኝቶኛል። እነሱም ሳይከፋቸው አይቀርም።
ኢህአዴግ በ1990 ዓ.ም ደብረዘይት የሚገኘውን የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አምባን ዘግቶ የመከላከያ ኮሌጅ አደረገው። በአምባው ውስጥ የነበሩ በምስራቅና በሰሜን በተካሄዱ ጦርነቶች ጉዳት የደረሳባቸውን አባላትና የራሱን ወታደሮች ጨምሮ በአጠቃላይ 275 ሰዎችን አምጥቶ ማዕከሉ ውስጥ አስገባቸው። ልደታ ፀበል አካባቢ የሚገኘው ማዕከሉ ድሮ የወጣት ወንዶች ሆስቴል እየተባለ ይታወቅ እንደነበር የነገሩኝ መቶ አለቃ ጥላዬ ሽፈራው፤ በአሁኑ ጊዜ አንድ መቶ አርባ የሚሆኑ ሰዎች በማዕከሉ ውስጥ ሲገኙ አንዳንዶቹም የድሬደዋን ከተማ በመከላከሉ ጦርነት የተሳተፉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አበው ነገር ከስሩ ወይም ከጥሩ ይላሉ። ሶማሊያ ሰኔ 24 ቀን 1952 ዓ.ም ነፃነትዋን አገኘች። የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደ አደረገው ሁሉ ለነፃነት ታጋዮቻቸው ሥልጠና እና የዲፕሎማሲ ሽፋን እንዲያገኙ በማድረግ፣ በገንዘብና በመሳሪያ ድጋፍ በመስጠት ረድቷቸዋል።
ይሁን እንጅ ሶማሊያ ነፃነቷን ከአገኘች በኋላ ይዛ የተነሳችው ሃሳብ “ታላቋን ሶማሊያ” መገንባት ሆነ:: “ታላቋ ሶማሊያ”  የሚለውን ሀሳብ የጠነሰሱትና በሶማሌ ወጣቶች ልብ እንዲያድር ያደረጉት ደግሞ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው አርነስት ቤቨን እና በሐረር የእንግሊዝ ቆንስል የነበረው ኮሎኔል ፔክ ናቸው። እነሱን ወደ እዚህ ሃሳብ እንዲሄዱ ያደረጋቸው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስኪያልቅ ድረስ በጊዜያዊነት  እንግሊዝ ይዛ የነበረውን የኦጋዴንን ግዛት የኢትዮጵያ መንግስት እንዲያስረክቡና ከአካባቢው እንዲወጡ ስለአደረጋቸው ነው።
“ታላቋ ሶማሊያ” የተባለው አካባቢ የጣሊያን ሶማሌ ላንድን፣ የእንግሊዝ ሶማሌ ላንድን፣ የፈረንሳይ ሶማሌ ላንድን (የአሁኗን ጅቡቲ)፣ ከኢትዮጵያ የኦጋዴንን አውራጃ እስከ ሐረር አልፎም እስከ ባሌ፣ አርሲ ሲዳሞ ድረስ የሚሸፍን ሲሆን ከኬኒያ ደግሞ ዋጅራ፣ ጋራሳና ማንደራ የተባሉ አካባቢዎችን የሚያጠቃልል መሆኑ መታወቅ አለበት።
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር  አብዱል ረሽድ ሸርማርኬ የሶማሌ ወጣቶች ሊግ አባል የነበረ ሲሆን ታላቋን ሶማሊያ እንመሰርታለን ብለው ከተነሱትም ውስጥ በዋናነት ስሙ የሚጠቀስ ሰው ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ካይሮ ላይ ያፀደቀውን “እያንዳንዱን አገር ነፃ በወጣ ጊዜ በያዘው ክልል ወይም ድንበር ወሰን የፀና ይሆናል” የሚለውን ውሳኔ እንደማይቀበል የገለፀው የሶማሊያ መንግስት፤ ፍላጎቱን በኃይል ለማስፈፀም መጀመሪያ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈተ። ቀጥሎ በፈርፈሪ፤ በቶጎ ውጫሌና በሌሎችም ቦታዎች ላይ ጥቃት ፈፀመ። የንጉሠ ነገሥቱ መንግስት  ለሶማሊያ የሚሰጠው ስንዝር መሬት እንደሌለው አሳወቀ። የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ወስዶ ወደ መቃዲሾ እየገሰገሰ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ወደ ኋላ እንዲመለስ የተደረገው በንጉሡ ትእዛዝ እንደሆነም ይነገራል።
ጥቅምት 11 ቀን 1962 ዓ.ም ጀኔራል መሐመድ ዚያድባሬ አበደርሽድ ስርማርኬን ገድሎ፤ የሶማሌን መንግስት ስልጣን  ያዘ። በዚህ ጊዜ ሊሆን ይችላል ግብፆች መሐመድ ካሊህ ሳላ የተባለ ሰው ወደ መቃድሾ ልከው ታላቋን ሶማሊያን የሚመሰርት ጦር ማሰልጠን ጀመሩ፡፡ ይህ ሰው መሐመድ አሚን ዳን በተባለ ካይሮ በተማረና ለኢትዮጵያ አንድነት በሚቆረቆር ኢትዮጵያዊ ቢገደልም ውጥኑ የተቋረጠ አልነበረም።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ሐርጌሳ በጨረሰና ሶርያ  በሰለጠነ የሱፍ ዳህር መሐመድ በተባለ ሰው፣ በሶማሌ መንግስት የሚደገፍ “የምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጪ ድርጅት” ተመስርቶ ኦጋዴን ውስጥ የደፈጣ ውጊያ ማካሄድ ጀመረ፡፡ የጥቃቱን ክልል ባሌ፤ ሲዳሞና አርሲ ለማድረስ ሲባልም ሌላ “የሶማሌ አቦ” የሚባል ድርጅት ተቋቋመ፡፡
 ሁለቱም እየተናበቡ ከምስራቅ እስከ ከደቡብ ያለውን የኢትዮጵያ አካባቢ ሰላም ነሱት። የጄኔራል ዚያድ ባሬ መንግስት ከሚሰጠው የትጥቅና የስንቅ ድጋፍ በተጨማሪ ሶስት ሺህ ወታደሮቹን የአማፅያን ልብስ አልብሶ ከጎናቸው እንዲሰለፍ በማድረግ ይበልጥ አጎለበታቸው። የንጉሡ መንግስት መውደቅና ኢትዮጵያ በሽግግር መንግስት ምስረታ ላይ መሆን፤ በኤርትራ የሚካሄደው ጦርነት፤ በደርግና በተቃዋሚዎች መካከል የሚደረግ  የሥልጣን ሽኩቻ በዚያድ ባሬ ዘንድ በመልካም አጋጣሚነት ተወሰዱ።
ከሩሲያ ባገኘው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ልቡ ይበልጥ ያበጠው የሶማሊያ መንግስት፤ ሐምሌ 1 ቀን 1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ከፈተ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም የጦር ቀጠናውን ወደ አስራ አንድ አሳደገው፤ ዋናው ግን ኦጋዴን ነበር፡
በጦር ግንባሩ ኢትዮጵያ የነበራት የጦር ኃይል በሶስተኛው ክፍለ ጦር ሥር ያሉ ሁለት የፈጥኖ ደራሽ የሸለቆችን ጨምሮ አራት ብርጌዶች ነበሩ፡፡ አምስተኛ ብርጌድ ጎዴ፤ ዘጠነኛ ብርጌድ ቀብሬ ዳር፤10ኛ መካናይዝድ ብርጌድ ጅጅጋ አስራ አንደኛ ብርጌድ ደግሞ ደጋሐቡር ላይ ይገኙ ነበር። ሁሉም ስማቸው እንጂ በሰው ኃይልና በመሳሪያ በተሟላ ደረጃ ላይ የሚገኙ አልነበሩም ፡፡ እንደ ቢኤም ባሉ መሣሪያዎች መቶ በመቶ፣ በሌሎች መሳሪያዎች ደግሞ ሰባ ከመቶ በላይ ብልጫ የነበረውን የሶማሊያ ጦር መቋቋምና ሙሉ በሙሉ መግታት ባለመቻሉ፣ የመከላከሉን ስራ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ይወጣ ዘንድ አስገድዶ ነበር ፡፡
ሌላው ሁኔታ ደግሞ በወቅቱ የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ዋና አስተዳደሩ አቶ አብዱላሂ ሙሜ ለሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም፤ “ሶማሌ ኦጋዴንን የወረረችው ዛሬ አይደለም። በሰርጎ ገብ ስም አካባቢውን እስከ ሐረር ተቆጣጥረዋለች፡፡ ከሐረር ጅጅጋ ያለኮንቮይ መሔድ አይቻልም። ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው።
የኦጋዴን ገጠር በሙሉ በሰርጎ ገቦች እጅ ነው፡፡ ሰርጎ ገብ ሲባል ዩኒፎርም አልለበሰም ታንክ አልያዝም እንጂ ግማሽ በግማሽ የሶማሌ ወታደር ነው” በማለት ሲገልጡት እናገኛለን፡፡ቆራሄ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ጦር መሐል ላይ ትቶ በግራ በቀኝ በማለፍ የባቡሩን ሐዲድ ተከትሎ ድሬደዋን እንዲያጠቃ የሶማሌ የጦር አዛዥ ለጦሩ ትዕዛዝ ሰጠ።
መቶ አለቃ በቀለ ጎንፋ ሁለት የሻለቃ የነበልባል ጦር መርተው በውጊያው ተሳትፈዋል።  ሶማሌ ሐምሌ 10 ቀን 1969 ዓ.ም ድሬደዋን ለመያዝ ሙከራ አድርጋ እንደነበር  እኚህ መቶ አለቃ ገልጠውኛል። አያይዘውም ነሐሴ 10 ቀን 1969 በነበረው ውጊያ መሰለፋቸውን፣ የአየር ማረፊያው ግራና ቀኝ የውጊያ ቀጠና እንደነበር፣ ሶስተኛ ክፍለ ጦር መሀንዲስ ክፍል በቀበረው ጸረ-ታንክ ፈንጂ ቀድመው የመጡት ስድስት የሶማሌ ታንኮቻቸው በመመታታቸው ሶማሌዎች ሁሉ ፀረ ታንክ የተቀበረበት ስለመሰላቸው ወደፊት መግፋት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ  ጦሩ ወደፊት ገፍቶ በጨበጣ ውጊያ እንዳደረገ፣ መለየት ስላልተቻለ የወገንን ጦር አየር ኃይላችን አባሮ ለመምታት መገደዱን፣ እሳቸው ምድርና የአየር ኃይሉን ውጊያ በማቀናጀት ማገልገላቸውን አስረድተዋል።
ጦርነቱ እየተቃረበ በመጣበት ጊዜ እሳቸው የሚመሩት በኢትዮጵያና በሶቪየት ህብረት መካከል “መርዞ” የሚባል የሥልጠና ፕሮግራም ሆለታ ላይ መጀመሩን፣ ዓላማው ከሶቭየት ህብረት የሚመጡ መሳሪያዎች አጠቃቀምን ማስተዋወቅ እንደነበር ብርጋዴር ጀኔራል ኃየሎም ገብረ ሥላሴ አውስተው፤ መጀመሪያ ወደ ደብረዘይት፣ ከዚያ ወደ ድሬደዋ ከ37 ሰልጣኞች ጋር መሄዳቸውን ጠቁመዋል።
“ድሬደዋ በደረስን ጊዜ መረጃ የሚሰጠን አላገኘንም። ደግነቱ በአካባቢው አንድ የማውቃቸው አዛዥ ስለነበሩ እሳቸው እርዳታ እያደረጉልን የራሳችንን ዝግጅት ማድረግ ጀመርን” የሚሉት ብ/ጄኔራል ኃየሎም፤ ረፋድ ላይ የአየር ኃይል ድጋፍ ተገኝቶ የጦርነቱ መልክ መለወጡን አስታውሰዋል።
የድሬደዋ ከተማ ኗሪ ቁስለኛ በማንሳት፣ ከሰራዊቱ ጎን ባለው መሳሪያ በመዋጋት ከፍተኛ ተጋድሎ መፈጸሙን አውስተው፣ “ሶማሌ በዚያን ቀን አሸንፋ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ታሪክ ምን ይሆን ነበር” ሲሉ አጥብቀው ይጠይቃሉ።
ብርጋዴር ጀኔራል ኃየሎም ጦርነቱ ላይ የየት አገር ዜጎች እንደሆኑ ያልታወቁ የነጮች ሬሳ መገኘቱን አስታውሰው፣ ጦርነቱ የሶማሌ ብቻ አልነበረም ብለዋል። የድሬደዋን ጦርነት የሚገልጹትም “አስታዋሽ ያጣው ወሳኝ ድል” በማለት ነው።የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሜጀር ጀኔራል መርዳስ ለሊሳ፣ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው፣ የቀድሞ የጦር አባላትን ለማክበርና ለማስታወስ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ፕሮግራሙም በዚሁ ተጠናቋል።



Read 3682 times