Monday, 19 September 2022 00:00

ባንክ የዘረፈ ካልታሰረ የተበላሸ ነገር አለ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

1. የደግ መንግስት ክፋቱ፣ በአንድ እጅ ድጎማ እየሰጠ በሌላ እጅ አገር ማራቆቱ ነው። ወጪው እየበዛ ብርዱ እየተቆለለ፣ መላ የሌለው አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል። እንደ ድጎማው ጦሱም ለብዙዎች ይደርሳል።
    2. ሳሊ ሃፊዝ፣ የቤሩት ነዋሪ ናት። በዚህ ሳምንት ረቡዕ እለት ባንክ ሄደች። በሽጉጥ አስፈራርታ 13 ሺ ዩሮ ወሰደች። አልታሰረችም። እሷም አድራሻዋን ለማጥፋት፣ ማንነቷን ለመደበቅ አልሞከረችም። እንዲያውም፣ አንድ ሰዓት የፈጀው “የባንክ ዝርፊያ ዘመቻዋን” በቀጥታ በኢንተርኔት አሰራጭታ ብዙ ተመልካችና አድናቂ አግኝታለች። በዚያው ቀን ሌላ ባንክ ላይ ተመሳሳይ ዝርፊያ ተፈጽሟል። ግን የታሰረ ሰው የለም። የዛሬ ወርም እንዲሁ ተፈጽሟል። ምንድነው ነገሩ?

        የአረቡ ዓለም “ፓሪስ”፣ የመካከለኛው ምስራቅ ብርሃናማ ከተማ… እያሉ ያወድሷት ነበር። የሊባኖስ መዲና ቤሩት ከተማ።
በነውጥ የተከበበች የሰላም አገር፣… ግጭትና ምስቅልቅል በማያባራበት የበርሃ ውሽንፍር መሃል በቀለች ለምለም ስፍራ ትመስል ነበር። ጥንታዊ የስልጣኔ ታሪክ በሊባኖስ ምድር የተሰራው ያህል፣ የዘመናዊ ስልጣኔ ችቦ ቢበራና ቢደምቅ እንዴት ይበዛበታል? ድሮ ጥንትም፣ የኪነጥበብና የንግድ የግንባታና የሙያ ጥበብ መነሃሪያ ስመ ጥር ባለዝና አገር ናት ሊባኖስ። እንደገና መልካም ዝናዋን ብትላበስ አይበዛባትም ነበር።
ባይበዛባትም እንኳ አልዘለቀላት። የመካከለኛው ምስራቅ የነውጥ ማዕበል እረፍት የለውም። አገራትን ከማተራመስ ውጭ ሌላ ስራ የለውም። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማንንም አይምርም። እንዲያውም የአረብ አገራት የግጭት ውሽንፍር ሊባኖስን ለማመሳቀል ጊዜ አልፈጀበትም። ከሁሉም በፊት መዘዙን ቀምሳለች። በእርግጥ፣ ዛሬ የየመንና የሊቢያ ትርምሶችን ካየን በኋላ፣ የሊባኖስ ታሪክ አዲስ ላይሆንብን ይችላል።
በእርስ በርስ ጦርነትና በታጣቂ ጎራዎች ግጭት፣ ከነ ቤንጋዚና ከነትሪፓሊ በፊት ነው ቤሩት አበሳዋን ያየችው።
ታጣቂ ቡድኖች በዘመናዊ ከተማ ላይ ለጥቂት ቀናት ቢፈነጩ፣… መጥፎ አጋጣሚ ነው። ከተማዋን እንደ ቅርጫ ተቀራምተው፣ በየመንደሩና በየመንገዱ፣ በየአደባባዩና በየቅያሱ ኬላ ሲቀስሩና ትናንሽ የሰፈር መንግስታት ሲሆኑባት ግን እርግማን ነው። የቀበሌ ጥቃቅን ግዛቶችን ሲፈጥሩ ይታይችሁ።
ሱቆች ፎቆች ምሽግ ይሆናሉ። ከጥቃት ለማምለጥ ለመሸሽ፣ ሁሉም ሰው መኖሪያ ቤቱንና የስራ ቦታውን እንደ ምሽግ ግንብና አጥር ይጨምርበታል። እየዋለ ሲያድር ግን ታጣቂዎች ይሰፍሩበታል። መሽገው ለመታኮስ የሚፈልጉ ታጣቂዎች።…
ደግሞስ በመስታወት ያማሩ መስኮቶች፣ በሰላም አገር እንጂ በትርምስ አገር ውስጥ በደህና አይሰነብቱም። በአመፅና በግጭት በምትታመስ ከተማ ውስጥ መስተዋቶች ምን እድሜ ይኖራቸዋል?
ዛሬ ባይሆን ነገ ተሰብረው መድቀቃቸው አይቀርም። ሰፋፊ መስኮቶች ወይም ከወለል እስከ ጣሪያ የተዘረጉ መስተዋቶች፣… ብርሃን እንደልብ ያስገባሉ።
 የደንበኞችን ቀልብ ይማርካሉ፤ የገበያኞችን ዓይን ያጠምዳሉ። ይሄ ግን በሰላም ጊዜ ነው። ሰላም በጠፋበት ጊዜ ግን፣ መስኮትና መስተዋት ዘራፊዎችንና ነፍሰ ገዳዮችን ይጋብዛሉ።
ጋጠወጥ የሰፈር ዱርዬስ፣ መች መስተዋት እያየ በዝምታ ያልፋል? በሰላም ጊዜ፣ ይሉኝታ አለ። ሰው እያየው መስኮቶችን አይሰብርም። በይሉኝታ አደብ ባይገዛ እንኳ፣ “ሕግ አለ” ብሎ ይሰጋል። ሰላም ሲደፈርስ ግን፣ ሐራም ነገሮች ሐላል የሆኑለት ይመስለዋል።
እግረ መንገድ ፊት ለፊት ያጋጠመውን ነገር መስበርና መቅጨት የሚፈልግ የክፋት ተለማማጅ፣ ብዙ የክፋት ማመካኛ ሰበቦችን እንደልብ የሚያገኘው፣ ሰላም ሲደፈርስ አይደል?
ዛሬ አንድ መስኮት ብቻ ሰብሮ ሊሮጥ ይችላል። ነገ ግን አይሮጥም። በዚያ ላይ፣ ሁለት ሦስት መስኮት ካልሰበረ አይረካም። በየቀኑ ይብስበታል።
ለነገሩ፣ መስተዋት የሚሰብሩ ጋጠወጦች ባይኖሩ እንኳ፣ በተቃወሰ አገርና በተናወጠ ከተማ ውስጥ የመስኮት መስተዋት ምን ይረባል? ለተባራሪ ጥይትና ለፍንዳታ ፍንጥርጣሪ ያጋልጣል እንጂ ምን ይጠቅማል?
ግርግር ሲዘወተር፣ አመፅና ነውጥ ሲደጋገም፣ መስኮቶችን በግንብ መድፈን ይለመዳል።  የመደብር መስኮቶች፣ የአደገኛ ወንጀለኞች እስር ቤት እስከመሰሉ ድረስ፣ በወፋፍራም ፍርግርግ ብረቶች ይታጠራሉ።
ክላሽና ባዙቃ የታጠቁ ወጣቶች፣ በየጎራው ተቧድነው በየመንደሩ ሲታኮሱ ይውላሉ። ሲገዳደሉ ያድራሉ። በትርፍ ጊዜያቸውም፣ አላፊ አግዳሚውን እያስቆሙ ያሸማቅቃሉ። ይዘርፋሉ። ሲብስባቸውም ይደበድባሉ። ቤት ለቤት ለፍተሻና ለዝርፊያ ይዘምታሉ። እያንዳንዱ ታጣቂ ቡድን በየፊናው፣ እስር ቤት ያዘጋጃል። ግዛቱን ያስፋፋል። ሕንፃዎችን ምሽግ ያደርጋቸዋል። የእስር ቤት ቅርንጫፎችን በየመንደሩ ይከፈታል።
እንደ ቅርጫ በተቀራመቷት ከተማ ውስጥ፣ “ግዛት ለማስፋፋት” ይዋጋሉ። ያው፣ የመድፍና የታንክ አፈሙዛቸውን ይወድራሉ። የሚያነጣጥሩት፤ የከተማው ህንፃዎች ላይ ነው። በየሰዓቱ በየእለቱ፣ ሁልጊዜ አዲስ ነገር ይኖራል። በየቀኑ መርዶ አለ።…
ትናንት ያልነበረ ተጨማሪ ቃጠሎ፣ ዛሬ ጭስና አመዱ ይታያል። ከሰልና ጥላሸት ይበረክታል። ትናንት ሙሉ የነበረ ሕንፃ፣ ዛሬ ተገጣጥቦ ይታያል። የተገመሰ ፎቅ፣ የተዝረከረከ ፍርስራሽ… በየቀኑ ይበረክታል። የሶሪያ ከተሞችን አይታችሁ የለ? ብዙም ሳይቆይ ከተማው ራሱ የፍርስራሽ ማከማቻ ይመስላል።
በየጊዜው አዳዲስ የግንባታ ጅምር ማየት፣… ለካ መታደል ነው። በየዕለቱ የፍርስራሽ ክምር ማየትም አለና።
ከሶሪያ በፊት ሊባኖስ ይህን መከራ አይታለች። ቢሆንም ግን፣ እንደገና ነፍስ መዝራት እንደምትችልም አሳይታለች። ፈራርሳ አልቀረችም። ብርቱ ናት።
ግን እንደ ቀድሞ የብሩህ ተስፋ ተምሳሌት መሆን አልቻለችም። ወደ ስልጣኔ የምትገሰግስ አርአያ ተብላ የምትሞገስበት እድል እንደገና መልሳ አላገኘችም።
በእርግጥ፣ ባለፉት 25 ዓመታት፣ ትንሽ የሰላም አየር ተንፍሳለች። ከለየለት ጦርነትና ትርምስ ፋታ አግኝታለች። ነገር ግን፣ ከታጣቂ ጎራዎች አልተገላገለችም። በጥላቻ የሚያቧድንና ለግጭት የሚቀሰቅስ ክፉ የፖለቲካ ቅኝትን አብርዶ የሚገራ መፍትሄ አላገኘችም። ስንት ዘመኗ!
የሊባኖስ ፖለቲካ እንደዚህ ሆኗል። የተሟላ ሰላም የለውም። የለየለት ጦርነት ውስጥም አልገባም። የዳር ዳርታ ነው። የመረጋጋት፣ ከዚያም ባሻገር የማንሰራራት ምልክቶችና ሙከራዎች አልራቋትም። ግን ወደ ሌላ የግጭትና ወደ አዲስ የትርምስ አዙሪት ጎትተው ከሚያስቡ ችግሮችና ጥፋቶችም አልራቀችም።
ዳር ዳርታውን ለዓመታት የተጓዘችው ሊባኖስ፣ ዛሬም ተስፋ በማይሰጥ የቁልቁለት አዙሪት እየተናጠች ነው።
ከሰሞኑ ቤሩት ውስጥ የተፈጸሙ “የባንክ ዝርፊያዎች”፣ የአገሪቱን አዝማሚያና ድርዳርታ ይመሰክራሉ። አፋፍ ላይ የደረሰ፣ ሙሉ ለሙሉ ያልለየለት የጥፋት ቁልቁለት ምን እንደሚመስል በእውን ለማየት ይረዳሉ።
ነገሩ እንዲህ ነው። ሳሊ ሃፊዝ ትባላለች። የቤሩት ነዋሪ ናት። ሽጉጥ ይዛ ወደ ባንክ የሄደችው ሳሊ ሃፊዝ፣ ሽጉጧን ደግና 20ሺ ዩሮ እንዲሰጧት ጠየቀች። አሁን ይሄ ምን የሚሉት ዝርፊያ ነው? ሃያ ሺ ዩሮ? ደግሞም ሳሊ እንደተናገረችው ከሆነ፣ ከራሷ የባንክ ሂሳብ ነው የራሷን ገንዘብ ለማውጣት የፈለገችው።
ያው፣ ብዙ የቤሩት ነዋሪዎች፣ በተለያዩ ባንኮች በዶላርና በዩሮ የባንክ ሂሳብ ይቆጥባሉ። በአብዛኛው “ከዳያስፖራ” የሚመጣ ገንዘብ ነው። አገር ቤት ከሚኖሩ ሊባኖሳዊያን ይልቅ፣ በየአገሩ ተበትነው የሚኖሩ ይበዛሉ። የአገሪቱ  የህዝብ ቁጥር 7 ሚሊዮን ነው።
ዳያስፖራው 10 ሚሊዮን ይሆናል። ለሁለት ለሦስት ዓመት በውጭ አገራት ሰርተውና ጥሪት አፈውርተው የሚመለሱም ጥቂት አይደሉም። በሄዱበት አገር እዚያው ከቀሩም፣ ብዙዎቹ ለወዳጅ ለቤተሰብ ዶላርና ዩሮ ይልካሉ። ደግነቱ፣ ሊባኖስ ውስጥ በዶላር በዩሮ መገበያየት ይችላሉ። በባንክ ሂሳብም ያስቀምጣሉ።
 ችግሩ ምንድነው? የሊባኖስ መንግስት በየጊዜው የውጭ ብድር እያከማቸ እየቆለለ እዳውን የመክፈል አቅም አጥቷል። ኢኮኖሚው ተቃውሷል።
ይህም የመንግስትን አቅም ባስኑ እያዳከመ እዳውን ያከብድበታል። መውጪያ የሚያሳጣ አጣብቂኝ ይሆንበታል። አለመረጋጋት ሲባባስ፣ የባንኮች ስራ ይወሳሰባል፡ ሁሉም ሰው ይሰጋል። ነገር ሳይበላሽ በፊት፣ የባንክ ሂሳባቸውን ለማውጣትና በእጃቸው ለማስገባት የሚፈልጉ ሰዎች ይበራከታሉ። ባንኮች ይጣበባሉ።
ዶላርና ዩሮ የሚያስቀምጥ ሰው ይጠፋል። አውጥቶ ለመውሰድ የሚፈልግ ደግሞ መዓት ነው። መቼም ሁሉንም ተቀማጭ የቁጠባ ሂሳብ ካዝና ውስጥ ይዞ የሚጠብቅ ባንክ የለም። ገሚሱን ለደንበኞች ያበድራል። በማበደር ነው ገቢ የሚያገኙት።
 አሳዛኙ ነገር፣ መንግስት የውጭ ብድር ሲበዛበት፣ አለመፀፀቱ ነው። ወደ ህሊናው ተመልሶ አደብ ቢገዛ ቀውሱ ባልተባባሰ ነበር።
ነገር ግን፣ ጊዜያዊ ማምለጫ መንገዶችን ፈጠረ። ከአገር ውስጥ ባንኮች እየተበደረ ዶላርና ዩሮ እያፈሰ መውሰድ ጀመረ። ዜጎች ያስቀጡት ዶላርና ዩሮ በመንግስት ተሟጠጠ። ባንኮችስ በምን ተማምነው ይሆን ለመንግስት ዶላር ያበደሩት? ሁሉም ሰው የቁጠባ ሂሳቡን አውጥቶ መውሰድ ሲፈልግ ባንኮች ምን ይውጣቸዋል? ያው፣ ወይ ተራቁተው ይከስራሉ። አልያም ደግሞ፣ የገደብና የክልከላ መመሪያዎችን ያወጣሉ።
በአገር ውስጥ ገንዘብ መንዝረን እንስጣችሁ ለማለት ይሞክራሉ። በሳምንት ከ500 ዶላር በላይ ማውጣት አይቻልም… የድጋፍ ደብዳቤ አምጡ፤ … ምናምን።
ሳሊ ሃፊዝ እንደበርካታ የቤሩት ነዋሪዎች ከዚህ ዓይነት ጣጣ አላመለጠችም። ታናሽ እህቷ እንደታመመችና የህክምና ሂሳብ መክፈል እንዳለባት የገለጸችው ሳሊ ሃፊዝ፣ የራሴን የባንክ ሂሳብ ለማውጣት እንጂ ለመዝረፍ አልሞከርኩም  ብላለች።
ከሁለት ተባባሪዎቿ ጋር ወደ ባንክ ከገባች በኋላ፤ በሮች ተዘጉ። ለአንድ ሰዓት የቆየሙ የሳሊ ሃፊዝ ዘመቻ፣ ተሳክቷል ማለት ይቻላል።13ሺ ዩሮ አውጥታ ወስዳለች። ያሰበችው ያህል አይደለም። ግን፣ ይሄስ ማን አየበት! ሽጉጥ ታጥቀው ወደ ባንክ መዝመት የማይችሉና የማይፈልጉ ብዙ የቤሩት ነዋሪዎች፣ የባንክ ሂሳባቸው፣ እንደ ሰማይ ርቋቸዋል። ሽጉጥ ታጣቂዋ ሳሊ ሃፊዝ፣ ከሃያ ሺ ዩሮ ውስጥ ገሚሱን አውጥታለች - የያዘችው ሽጉጥ የውሸት ሽጉጥ ቢሆንም።አዎ፣ እንደ ሳሊ ሃፊዝ የመሳሰሉ የሊባኖስ ዜጎች እንደ ጀግና ተጨብጭቦላቸዋል። የሌላ ሰው ገንዘብ አልዘረፉም። ደግሞም፣ ተመሳሳይ ተግባር የፈጸሙ በርካታ ሰዎች ያቀረቡት ምክንያት አንድ አይነት ነው። እህት ለማሳከም፣ አባት ለማሳከም ወይም ሌላ ተመሳሳይ ምክንያት ተናግረዋል።
ግን በመሳሪያና በጉልበት? የሳሊ ሃፊዝ ሽጉጥ የውሸት ቢሆንም፣ ሌሎቹ ግን የምር ጠመንጃ ተጠቅመዋል። ሳሊ ሃፊዝም፣ ቤንዚን አምጥታ ባንክ ውስጥ አርከፍክፋ ዝታባቸዋለች- አጋያችኋለሁ ብላ። ይሄ ነገር ያዛልቃል? በዚህ ከቀጠለ አደጋ መፈጠሩ ይቀራል?
ደግሞስ የዝርፊያ መለማመጃ አይሆንም? ጉልበትና ሽጉጥ የሌላቸው ሰዎችስ ምን ይሁኑ? ኧረ ከነጭራሹስ፣ ያለ ሕግ ያለ ሥርዓት… የሰላምና የጤና ተስፋ ይኖራል?

Read 9487 times