Saturday, 17 September 2022 12:53

“ኤርትራ የሽብር ቡድኖችን አዝልቃ መቅበር ትቀጥላለች” የኤርትራ ጦር ጠቅላይ አዛዥ፤ ጄ/ፊሊፖስ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   የህወሓትን አሸባሪነት ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ያሉት የኤርትራ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጄነራል ፊሊፖስ ወ/ዮሓንስ፤ እኛ ደግሞ ለቀጠናው ሰላም ስንል፣ አሸባሪዎችን አዝልቀን መቅበራችንን  እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
 “የህወሓትን አሸባሪነት ያረጋገጠው የኢትዮዽያ ህዝብ ነው። ህወሓትም አለማቀፍ የሽብርተኝነት መስፈርቶችን ከበቂ በላይ አሟልቶ አጠናክሮ ቀጠለበት እንጂ ከስህተቱ ተምሮ የኢትዮዽያን ህዝብና መንግስት ይቅርታ አልጠየቀም። ይልቁንስ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ቁልፍ ስጋት ሆኖ አረፈው።” ሲሉ መናገራቸውን ኤርትሪያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡  የኢትዮዽያ ሰላም ለምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ኢትዮዽያ ውስጥ ሰላም የለም ከተባለ፣ ኤርትራም ሁለቱም ሱዳኖች፣ ኬንያም፣ ሱማልያም ሆነች ጅቡቲ ሰላም ሊሆኑ አይችሉም ያሉት ጄነራሉ፤  በተለይ ለኤርትራ ሁሉን አቀፍ እድገትና  ሰላም የኢትዮዽያ አንድነት፣ ሰላምና እድገት ወሳኝ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ዋጋ ያለው ነው፤ ብለዋል።
“ለአሸባሪው ህወሓት የኢትዮዽያ ጥምር የጦር ኃይል ከበቂው በላይ ነው። ይሁን እንጂ ህወሓት ጋላቢዎቹን  ግብጽ፣ አሜሪካና ምእራባውያንን ጣልቃ ለማስገባትና ቀጠናው በእነርሱ ቁጥጥር ስር እንዲሆን የሰጡትን ተልእኮ ለማሳካት ሲል አስቀድሞ “በኤርትራ ልወረር ነው” ከአለ በኋላ፣ የኤርትራን ሉአላዊነት በተደጋጋሚ እየተዳፈረ በሚገባ እየተመታ ሲመለስ “የኤርትራ መንግስት ከዐቢይ ጋር ሆኖ ወረረኝ!” እያለ ያላዝናል፤ብለዋል ጄነራሉ።
“እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ቁልፍ ጉዳይ ግን ምንም እንኳን ህወሓት የቀጠናው የሽብር ስጋት ቢሆንም፣ ኤርትራ የራሷን ሉአላዊነት ታስከብራለች እንጂ፣ የኢትዮዽያን ሉአላዊነት በመዳፈር በኢትዮዽያ ምድር ገብታ የምታደርገው ኦፕሬሽን ፈጽሞ ሊኖር እንደማይችል ሊሰመርበት ይገባል።” ሲሉ መግለጻቸውን ኤርትሪያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡
 “ይህ የሽብር ቡድን ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ላይ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮዽያ መንግስትና ህዝብ ጋር ሆኖ መታኝ ተባበረብኝ.... ወዘተ እያለ መዘላበዱ የኢትዮዽያ ጥምር ጦር አቅሙ ውስን እንደሆነ ለውጭ ጠላቶች ማሳያ አድርጎ የተጠቀመበት ከመሆኑ ባሻገር፣ የሽብር ቡድኑ ከመሬት በታች መቀበሪያው ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን አመላካች መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።” ብለዋል፤ጄነራሉ፡፡
 “ኤርትራም ለቀጠናው ሰላም የሚበጅ እስከሆነ ድረስ ሉአላዊነቷን የሚዳፈሩ የሽብር ቡድኖችን አዝልቃ መቅበር ትቀጥላለች!” ሲሉ የኤርትራ መከላከያ ጦር አዛዥ ጄነራል ፊሊፖስ ወ/ዮሓንስ  መናገራቸውን ኤርትሪያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡


Read 12506 times