Print this page
Saturday, 10 September 2022 21:00

“መንኳኳት የማይለየው በር!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 አንዳንድ በሀገራችን እንደቀልድ የሚወሩ ወጎች ውስጠ-ነገራቸው ታሪክ-አዘል ሆኖ ይገኛል።
የሚከተለው ቀልድ ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት የቀድሞው የሩሲያ መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭና አሁን በኢትዮጵያ በሌሉት  በቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ  በሊቀ መንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ዙሪያ የተቀለደ ነው።
የሩሲያ መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ ከዕለታት አንድ ቀን ለኢትዮጵያው መሪ ለጓድ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም የገና በዓል ሥጦታ (X-mas gift) ይልኩላቸዋል አሉ።
ሥጦታቸው አንዲት የኮርስ ብስክሌት ናት። የብስክሌቷ ልዩ ነገር፣ ምንም ዓይነት የእግር መሽከርከሪያ ወይም ፔዳል የሌላት መሆኑ ነው።
ሊቀ መንበር መንግሥቱ ፔዳል እንደሌላት ሲያዩ በጣም ተበሳጭተው፡-
“የጉምሩክ ሰራተኞች ይሆናሉ የሰረቁኝ (የበሉኝ) እሰሩና ጠይቁልኝ!” አሉና ትዕዛዝ ሰጡ። የጉምሩክ ፈታሾች በሙሉ ታሰሩ - እንደ ሕጉ። እንደ ባሕሉ። የጉምሩክ ፈታሾች በሙሉ ተከረቸሙ። በምርመራ የተገኘ ምንም ነገር አልነበረም።
በቁጣ፤ “ፓይለቶቹንም እሰሩና መርምሩልኝ” አሉ። ፓይለቶቹም ታሰሩ። ፔዳሉ ግን አልተገኘም።
ጥቂት ወራት እንዳለፈ የእስር ቤቱ መርማሪዎች፣ ምንም ፍንጭ አለመገኘቱን ሪፖርት አደረጉ።
ሊቀ መንበር መንግስቱ አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው መላ ምቱ አሉ።
አማካሪዎቻቸውም፤
“ለምን ፕሬዚዳንት ጎርባቾቭ ዘንድ ተደውሎ፣ የላኳት ብስክሌት ፔዳል ያላት ይሁን፣ ፔዳል የሌላት አይጠየቁም?” ሲሉ ሀሳብ አቀረቡላቸው።
ተደውሎ የጎርባቾቭ የቅርብ ረዳት ተጠየቀ።
የቅርብ ረዳታቸው አረጋግጦ ያመጣው መልስ፣ ዕውነትም የተላከችው ብስክሌት ፔዳል የሌላት ናት።
መንግሥቱ ኃይለማርያም በጣም በሽቀው፤
“እኮ ለምን? ለምንድነው ፔዳል የሌላት ብስክሌት የላካችሁት?” ብለው ጠየቁ።
ከሩሲያ ወገን ያገኙት መልስ፡-
“ጓድ ሊቀመንበር፣ እርሶ ሁልጊዜ ወደ ቁልቁለት እየወረዱ ስለሚሄዱ፣ ፔዳል መምታት (መዘውሩን ማሽከርከር) አያስፈልግዎትም!” የሚል ሆነ፤ ይባላል።
***
የአገር ኢኮኖሚ ወደ ቁልቁል በሄደ ቁጥር አገር ቁልቁል ትሄዳለች። የሕዝብ ኑሮ ከቀን ወደ ቀን እየተጎሳቆለ ይሄዳል። የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ እያሻቀበ፣ የሕዝብ ህይወት እያዘቀዘቀ ሲሄድ፤ ውጤቱ ምሬት ይሆናል። ምሬት አመፅን ይወልዳል።
ገዢ በግድ ልግዛ ካለ፣ ተገዢው ሕዝብ አልገዛም ማለቱ የማይታበል ሐቅ ነው። ይሄን የሚሸመግልና የሚያረጋጋ አካል ከሌለ፣ ህዝብና መንግሥት እሳትና ጭድ፣ አዳኝና ታዳኝ እየሆኑ ይመጣሉ። በታሪክ፣ በሀገራችን በርካታ ወደ ከፋ ሁኔታ የሚያመሩ ክስተቶች አይተናል። የሀገሪቱ ወሳኝና የነቃው ምሁር ክፍል በእሳቱ ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ ይልቅ፤ ቆም ብሎ በጥበብ የመንቀሳቀሻ መላ መምታት ይጠበቅበታል። የማረጋጋት ሚና ለመጫወት ደግሞ አስቀድሞ ራሱን የማረጋጋት ሂደትን መወጣት አለበት። ብዙ የበሰሉና ጥሞና ያላቸው ሰዎች አሉ። አለን አለን አይሉም። በመጮህም አያምኑም። እንዲህ ያሉትን ሰዎች ፈልጎና ስራዬ ብሎ፣ “ኑ እስቲ የአገራችንን ነገር እንምከርበት” ማለት ያስፈልጋል፡፡
ነገን የተሻለ ለማድረግ ያለቀውን ዓመት መጠነኛ ግምገማ እናድርግበት፡፡  መጪውን ዘመን ከመነሻው እንቅረፀው። ዘመን ተለወጠ ማለት የሚቻለው ከትላንት የተሻለ ቅላፄና ቃና ያለው ሙዚቃ ለመፍጠር ስንችል ነው። ጦርነት እንዲያባራ በቅን ልቦና ጥረት ስናደርግ ነው። ዛቻን ትተን በክብ ጠረጴዛ መነጋገር ስንችል ነው። የ”እኔ አሸነፍኩ፣ አንተ ተሸነፍክ”ን መዝሙር መዘመርን፣ ቢያንስ በመጠኑ እየቀነስን ለመሄድ ዝግጁ ስንሆን ነው። በተራ በተራ እየሞተ ያለው የሕዝብ ልጅ ነው። ማርጋሬት ሚሼል የተባለችው ደራሲ፤ “WAR IS LIKE CHAMPAGNE, IT GOES TO THE HEADS OF FOOLS AS WELL AS BRAVE MEN AT THE SAME SPEED.” ትለናለች፡፡
(“ጦርነት ልክ እንደ ሻምፓኝ መጠጥ ነው። እጅሎችም፣ እጀግኖችም እናት ላይ በእኩል ፍጥነት ነው የሚወጣው”) እንደማለት ነው። በጦርነት ስንሰክር የሚፈስሰው ዞሮ ዞሮ የሰው ልጅ ደም መሆኑን ረስተን፣ የሚታየን ማሸነፍ ብቻ ነው። መጨረሻው ግን የአገር እጦት ነው።
 ከጦርነት ያተረፈ የለም። ጊዜያዊ ድል እንጂ ዘላቂ ትርፍ አይገኝበትም! ብዙ ጊዜ ስለ ሰላም ይነገራል። ብዙ አድማጭ ግን አይገኝም። “ኧረ በገላጋይ፣ በሕግ አምላክ!” የማይባልበት ጊዜ ሆነና መጠፋፋት ብቻ እየታየን ያለበት ዘመን በመሆኑ፣ከዚህ ይገላግለን ዘንድ እግዚኦታ ያስፈልገናል። “ምህረቱን ይላክልን!” ማለት ደግ ነው።  እስከ ዛሬ ብዙ የጦር ጀግና አፍርተን ሊሆን ይችላል። የሥልጣኔ ጀግና ግን አላፈራንም። ይሄ ከእርግማን አንድ ነው። ዓለም ወደፊት ሲጓዝ እኛ ወደ ኋላ እየተመለከትን፣ ገና የታሪክ ሰበዝ ከመምዘዝ አልተላቀቅንም! መፍትሔው አንድ ብቻ ነው - የሚንኳኳውን በር አለመስማት። መንኳኳት የማይለየውን በር ነቅሎ አዲስ በር መግጠም!
ይሄንን ስናደርግ ብቻ ነው፣ አዲሱ ዓመት አዲስ የሚሆንልን! አዲስ ዓመት፤ የአዲስ ለውጥ የአዲስ ሕይወት ፀሐይ የሚፈነጥቅልን በዚህ መልኩ ነው! በአዲሱ ዘመን መንኳኳት ከማይለየው በር ይገላግለን! አሜን።


Read 11711 times
Administrator

Latest from Administrator