Saturday, 20 October 2012 10:08

ድሬዳዋ፣ ሃረርና ጂጂጋ ጨላልመው ሰነበቱ

Written by  በጽዮን ግርማ
Rate this item
(7 votes)

ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ የሚገኙት የአገሪቷ ትልልቅ ከተሞች ከአንድ ሣምንት በላይ በጭለማ እና በውሃ ጥም አሳልፈዋል፡፡ ከስልክ እና ከኢንተርኔት ተቆራርጠው ለማሳለፍም ተገደዋል፡፡ ለከተሞቹ ኤሌክትሪክ የሚያስተላልፉ አራት ትልልቅ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ማገናኛ በ“ሽፍቶች” በመዘረፉ ነው ከተሞቹን ጨለማ የወረሳቸው ተብሏል፡፡
ዘጠኝ ቀናት በጨለማ
ሐሙስ ጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በድሬዳዋ ድንገት መብራት ተቋረጠ፡፡ የራሱን እንጂ የጎረቤቱን ያላስተዋለ ነዋሪ፤ የመብራቱ መቋረጥ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ስላልመሰለው እስኪመሽ ድረስ የመብራቱን መጥፋት ነገሬ አላለውም ነበር፡፡
በማግስቱ ግን ወሬው በየመንደሮቹ ተዛመተ፡፡ በድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን በሐረርና በጅጅጋ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች ጭምር መብራት መጥፋቱ ተሰማ፡፡

ከአየር ጠባዩ እና ከአኗኗር ባህሉ አንፃር፤ ከአንድ ሣምንት አስቤዛ በላይ መሸመት ልማዱ ያልሆነው ማኅበረሰብ የመብራት መጥፋቱን ከአራት ቀናት በላይ ታግሶ መቆየት አልቻለም፤ በእንጀራ እና በዳቦ እጦት ይሰቃይ ጀመር፡፡ ያለው ለሌለው እያካፈለ ክፉ ጊዜን ሊያሳልፉ ሞከሩ፡፡ ችግሩ ግን በአንድና በሁለት ቀን አልተገታም … ጨለማው ሰነበተ፡፡ ከመብራቱ ጋ ውሃም አብሮ ጠፋ፡፡ የእንጀራ፣ የዳቦ፣ የሻማ እና ከመብራት ጋር የተያያዙ ፍጆታዎች ሁሉ ዋጋቸው ናረ፡፡ 
በድሬዳዋ ከተማ በአዲስ ከተማ ሰፈር ነዋሪ የሆኑት የ37 ዓመቱ የመንግሥት ሠራተኛ አቶ መሐመድ ቡሽራ ስለተፈጠረው ሁኔታ ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፤ “መጀመሪያ አካባቢ ላይ መብራት የጠፋው እኛ አካባቢ ብቻ መስሎኝ ነበር፤ በኋላ ላይ ስንሰማ ግን ለካ የጠፋው በሁሉም ከተሞች ነው፡፡ መብራት በመጥፋቱ ምክንያት ቀድሞውንም በተራ የሚደርሰን ውሃ አብሮ ጠፋ፣ እንደምንም ብለን ጀኔረተር ያለበት ቦታ ሄደን ስልክ ቻርጅ አድርገን ስልክ እንዳንጠቀም የሞባይል ኔትወርኩ ተቋረጠ፤ ምግብ የለ፣ መጠጥ የለ፣ ኢንተርኔት የለ፣ ቴሌቪዥን የለ … የመጀመሪያዎቹ አራትና አምስት ቀናቶች በጣም አስጨናቂዎች ነበሩ፡፡ የድሬዳዋ ሕዝብ ቀልደኛ ነውና ሳምንቱን “የሻማ እራት ሣምንት” በማለት ሰየመው” ሲሉ አስከፊ ክራሞታቸውን በቀልድ አዋዝተው ነገሩን፡፡
መሸትሸት ሲል በየቤቱ ደጃፍ ላይ እየተቀመጠ ሰብሰብ ብሎ መጫወት የለመደው የከተማው ሕዝብ፤ ቀን ቀን በውሃ እና የሚበላ ፍለጋ ሲዳክር ስለሚውል ከጭለማው ጋር ተያይዞ በጊዜ ወደቤቱ መክተት ጀመረ ያሉት አቶ መሐመድ፤ ከተማዋ በድቅድቅ ጨለማ መዋጧ አስፈሪ ድባብ እንደፈጠረ ይናገራሉ፡፡
በሐረር ከተማ ተወልደው ያደጉት እና በማስተማር ሥራ ከ30 ዓመት በላይ ያሳለፉት ወ/ሮ ጸሐይ አበራ “የሐረር ከተማ በርካታ ችግሮች እና መከራን አሣልፏል፤ ከ20 ዓመት በላይ በውሃ ችግር ተሰቃይቷል፤ በመንገድ እጦት እና በከተማዋ ዕድገት ሰንካላነት ምክንያት ወደ ኋላ ቀርቷል፡፡ እነዚህን ሁሉ ዘመናት እዚሁ ቁጭ ብዬ አይቻለሁ፤ በዚህ ሣምንት እንደገጠመን ዓይነት ድፍን ያለ ጊዜ ግን አላየሁም” በማለት አማረዋል፡፡
የጂጂጋ ከተማ ነዋሪዎችም ችግር ከሐረር ከተማ የተለየ አልነበረም፡፡ ከከተማዋ ሞቃታማነት እና በረሃማነት አንፃር፤ የመብራት መቋረጡ ከተማዋን ምድረበዳ አስመስሏታል፡፡ የሚጠጣ ነገር አለመኖሩ፤ ያለውም የሚጠጣ ነገር ቀዝቃዛ አለመሆን፤ እንደበፊቱ ሰውነትን በየሰዓቱ ወይም በቀን አንድ ጊዜ ለመታጠብ አለመቻሉ፤ ምግብ እንደልብ አለመገኘቱ እና ጭርታው ከተማዋ ላይ አስጨናቂ ድባብ እንደፈጠረባት ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡
መብራት መጥፋቱ እና ገበያው
በድሬዳዋ ከተማ መብራት ከጠፋ በኋላ ጥቂት ጄነሬተር ያላቸው ነጋዴዎች የፍጆታ እቃዎችን ዋጋ አስወድደውት ሰንብተዋል፡፡ ሁለት ሊትር ውሃ የሚይዘው ጀሪካል ቀደም ሲል ሲሸጥበት ከነበረው 10 ብር ወደ 17 ብር ከፍ ብሏል፡፡ 20 ሊትር የሚይዘው ቀደም ሲል 23 ብር ይሸጥ የነበረው ውሃ ደግሞ ከ40 እስከ 45 ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ ቀድሞውንም በመከራ የሚገኘው ዳቦ ዋጋው በእጥፍ ጨምሯል - ያውም ከተገኘ፡፡ ቀደም ሲል ሁለት ብር የሚሸጠው እንጀራ ከአምስት እስከ ስድስት ብር እየተሸጠ ሲሆን በሐረር እና በጂጂጋ ደግሞ እስከ 10 ብር ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች በፖሊስ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በድሬዳዋ ከተማ ባሉ አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ጄኔረተር ያላቸው ትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ ዘመድ ወይም የሚያውቁት ያላቸው ሰዎች የሞባይል ስልኮቻቸውን እየላኩ ቻርጅ ያስደርጋሉ፡፡ እነዚህ አማራጮች የሌሏቸው ደግሞ ጀነሬተር ያላቸው ነጋዴዎችጋ በመሄድ ለአንድ ጊዜ ሙሉ ቻርጅ ለማስደረግ 10 ብር ለመክፈል ተገደዋል፡፡ ተራ ላይደርሳቸውም ይችላል፡፡ በአንድ ሱቅ ውስጥ ሞባይሎቻቸው ላይ ስም እየተለጠፈ ተራ ይይዛሉ፤ ተራ የደረሰው ሰው ቻርጅ አስደርጎ 10 ብር ከፍሎ ይወጣል፡፡
ለከተሞቹ መብራት መቋረጥ ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ በወለንጪቴ ከተማ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ባለ ጫካ የተተከለው የኤሌክትሪክ ማሰራጫ በ“ሽፍቶች” በመዘረፉ ነው፡፡ የአካባቢው እማኞች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ምሰሶዎቹ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ትልልቅ እና ወፋፍራም ብረቶች ሲሆኑ እያንዳንዳቸው በአራት በአራት ምሰሶዎች የቆሙ ናቸው፡፡ አራቱን ብረቶች አቅፈው የያዙ ደግሞ ሌሎች የጎን ብረቶች አሏቸው፡፡
አካባቢው ለረጅም ጊዜ በሽፍቶች መሸሸጊያነት የሚታወቅ ጫካ ያለው ሲሆን መብራት የጠፋ እለት የእነዚህ ምሰሶዎች ግማሽ አካል ተሰርቆ ሌሎች ብረቶች ደግሞ ወድቀው ታይቷል ብለውናል፡፡ ከዚህ ቀደምም በ1996 ዓ.ም ቦታው ዝርፊያ ተፈጽሞበት ነበር የሚሉት ነዋሪዎች፤ መንግሥት ዝርፊያውን የፈፀሙት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነበሩ ቢገልጽም፤ ያኔም ሆነ አሁን የተያዘ ሰው እንደሌለ እና እንዲህ ዓይነት ከባድ ዝርፊያ ለመፈፀም የሚደፍሩት “ሽፍቶች” እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ስርቆቱን የፈፀሙ ግለሰቦች ላይ አደጋ ሊደርስ ይችል እንደነበር የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ “ሆኖም በአካባቢው ምንም የተጐዳ ሰው አልተገኘም፤ “አደጋው ቢደርስም እንኳን እንዳይታወቅ ተደጋግፈው ተመልሰው ጫካ ገብተው ሊሆን ይችላል” ይላሉ የአካባቢው የዓይን እማኞች፡፡

ምስራቅ እና ውሃ
የመብራት መጥፋቱን ተከትሎ በከተሞች የተከሰተው ሌላ ቀውስ የውሃ መጥፋት ነው፡፡ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች የውሃ እጥረትን አስቀድመው ቢላመዱትም መብራት መጥፋቱን ተከትሎ የተከሰተው የውሃ እጥረት በሌሎች ችግሮች ላይ በመደረቡ መቋቋም እንዳቃታቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
የከተማው የውሃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤትም የኤሌትሪክ ኃይሉ ከተቋረጠ በኋላ ለአስቸኳይ ጊዜ ተብሎ ከተቆፈሩት ጉድጓዶች በጄኔሬተር በመታገዝ በጥቂቱ ውሃ ለማከፋፈል ሙከራ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል፡፡
አሁን ድንገት በተከሰተው የመብራት መቋረጥም የከተማው ውሃና ፍሳሽ መስሪያ ቤት፤ ስምንት ጀነሬተሮችን በማስነሳት ዳር ላሉ ሰፈሮች በቧንቧ ለማዳረስ እየሞከረ ሲሆን ለመሀል ከተሞች ደግሞ በቦቴ አማካኝነት እያደረሰ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የከተማውን የውሃ እጥረት ለማስቀረት አዲስ ፕሮጀክት መነደፉን ፣ ፕሮጀክቱም 570 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ አቶ ጀማል ተናግረዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክትም ፀድቆ ከዓለም ባንክ የ18 ሚሊዮን ዶላር ብድር እና የ4.2 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ በአጠቃላይ የ320 ሚሊዮን ብር ገንዘብ መገኘቱን ቀሪውን ገንዘብ የከተማው መስተዳድር ሸፍኖ ሥራውን ለመጀመር አጠቃላይ ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ጀማል አስረድተዋል፡፡ በከተሞቹ የተከሰተውን የመብራት እጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከ100 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች ቀንና ሌሊት በመስራት ላይ ሲሆኑ እያንዳንዱ የወደቁት ብረቶችን መልሶ ለመሥራት ወደ 34 ሚሊዮን ብር በማስፈለጉ እና አንዱን ብረት ለመትከል 3 ወራት ገደማ የሚወስድ በመሆኑ፣ በጊዜያዊነት ማገልገል የሚችሉ 160 የሚጠጉ የእንጨት ምሰሶዎችን በመትከል፣ ከተሞቹ ትናንት ከዘጠኝ ቀናት በኋላ መብራት እንዲያገኙ መደረጉ ታውቋል፡፡

 

Read 5422 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 10:14