Print this page
Saturday, 10 September 2022 19:58

‹‹መገናኛ ብዙሃን ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል››

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት  በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ዳግም ጦርነት ውዱ  የሰው ህይወት በመቀጠፉ የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ፣ ሁኔታውን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ  ህዝብና መንግስት እንዲሁም ተፋላሚ ሀይሎች ሊጀምሩ ያቀዱት  የድርድር ሂደት ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ እናምናለን ብሏል፡፡
 ‹‹ዳግም ያገረሸው ግጭት ተባብሶና ሰፍቶ የሚቀጥል ከሆነ ከሰው ልጅ ህይወት መጥፋት በተጨማሪ ለከባድ ሰብዓዊ ቀውስና የንብረት ውድመት የሚያጋልጥ መሆኑ ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የጦርነት ጠባሳ ህያው ምስክር ነው›› ይላል ምክር ቤቱ ትላንት ያወጣው መግለጫ፡፡
በመሆኑም ከጦርነትና ግጭት ትርፍ ሊያገኝ የሚችል የህብረተሰብ አካል ያለመኖሩን ከግምት በማስገባት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተሰንቆ የነበረው የሰላም  ሂደት በአስቸኳይ እንዲጀመር የመገናኛ ብዙሃን ስለ ሰላምና አብሮነት ትኩረት ሰጥተው እንደሚገባ መክሯል
ሆኖም መገናኛ ብዙሃን  ወቅቱን አስመልክተው የግጭት መረጃዎችን ለህዝብ በሚያደርሱበት ጊዜ በምክር ቤታችን የጸደቀውንና ማንኛውም ጋዜጠኛ ሊከተላቸው የሚገቡ የስነ ምግባር ደንቦችን በማክበር መሆን ይኖርበታል ሲልም አስታውሷል ምክር ቤቱ፡፡  ‹‹የሚዲያ ተቋማት በዚህ ወቅት  በተቀናጀ መልኩ የሀገርና የህዝብ ደህንነት ላይ በማተኮር  እንዲሁም የህዝቦችን ለዘመናት የኖረውን አብሮነት በማስቀደም ተጨማሪ ግጭትና መራራቅ እንዳይፈጠር ተግተው ሊሰሩ የሚገባበት ሰዓት ነው›› ብሏል፡፡
ካገረሸው ጦርነት ጋር ተያይዞ ለህዝብ የሚቀርቡ  ዘገባዎችን ከፍ ባለ የሀላፊነት መንፈስ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ሊዘነጋ አይገባም፤ በተለይም መገናኛ ብዙሃን ጦርነቱን የሚያባብሱ፣ ጥላቻን የሚሰብኩና ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ የአደባባይ መግለጫዎችን በተመለከተ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት የተደነገጉትን ክልከላዎች ማክበር አለባቸው ያለው መግለጫው በዘገባዎቻቸው ማናቸውንም የህብረተሰብ ክፍል በዘር፣ በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካዊ አስተሳሰብን አስመልክቶ ጥላቻን የሚያበረታታ እንዲሁም ንቀትን ወይም መገለልን ሊፈጥር የሚችል ቋንቋን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ በምክር ቤቱ በፀደቀው የሥነ ምግባር ደንብ ላይ መስፈሩን አስታውሷል፡፡
‹‹የፕሬስ ነፃነት ከሙያ ስነ ምግባር ጋር የተቆራኘ ነው፤ በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን የጋራ ሰላምንና ወዳጅነትን ለማሳደግ እጅግ የተለየ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከሕዝቦች፣ ከብሔረሰቦች ወይም ከሃይማኖቶች ጋር በተያያዘ በሚነሱ አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች ላይ የሚሠሩ ዜናዎች፣ አስተያየቶች ወይም የሚሰነዘሩ ሃሳቦች እውነታዎቹ በተገቢው ሁኔታ ከተረጋገጡ በኋላ መቅረብ ያለባቸው ሲሆን ትኩረታቸው በመፍትሄው ላይ ሆኖ የሕዝቦችን ትስስር፣ ወዳጅነትና ሰላምን ለማስፈን በሚያስችል መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ በህዝቦች መካከል የመነሳሳት ስሜቶችን ሊፈጥሩ የሚችሉ የጦር ሜዳ  ፎቶግራፎችንና አሰቃቂ ምስሎችን ከማሳተም ወይም ከማሰራጨት መታቀብ አለባቸው፡፡››ብሏል ምክር ቤቱ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነፀ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን  የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን  እንዲጎለብት የሚሰራ ሲሆን ከ60 በላይ የመንግስትና  የግል መገናኛ ብዙሃን፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙህን እንዲሁም የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራትን በአባልነት ያቀፈ ተቋም ነው፡፡


Read 1044 times
Administrator

Latest from Administrator