Saturday, 03 September 2022 14:10

የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በጦርነቱ ለሚደርሰው ጥፋት ተጠያቂው ህውሓት ነው አለ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

   ህውሓት ያስታጠቀው የትግራይ ወጣት፤ አፈሙዙን ወደ ቡድኑ አመራሮች ሊያዞር ይገባል ብሏል
                
       የትግራይ ህዝብ በህውሓት ታጣቂ ቡድን  እየደረሰበት ያለውን መከራና ሞት ማቃለል እንደሚገባና በታጣቂ ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር እንደሚያስፈልግ የትግራይ የዲሞክራሲዊ ፓርቲው (ትዴፓ) ገለፀ፡፡ ታጣቂ ቡድኑ ከማዕከላዊ መንግስት ሥልጣኑ በህዝብ አመፅ ተወግዶ ወደ ትግራይ ከሸሸ በኋላ ዳግም እንደገና ወደ ስልጣን ለመመለስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ብሏል፡፡
የህወሃት ታጣቂ ቡድን ከፌደራል መንግስቱ የሚቀርብለትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በመግፋትና የአገራችንን መከላከያ ሃይል ከጀርባ በመውጋት ፀረ ሰላምነቱን ብቻ ሳይሆን አገር ከሃዲነቱን ለዓለም አሳይቷል ያለው ፓርቲው፤ ታጣቂ ቡድኑ ዛሬም ድረስ በዚሁ ፀረ ሰላም ቡድንነቱ ቀጥሎበታል ብሏል፡፡ቡድኑ በቀሰቀሰው የመጀመሪያ ዙር ጦርነት፣ ሰለባ የሆነው የትግራይ ህዝብና ወጣቱ መሆኑን ያስታወሰው የፓርቲው መግለጫ ቡድኑ በመንግስት በኩል የሚቀርብለትን የሰላም ጥሪ በተደጋጋሚ ባለመቀበል የትግራይን ህዝብ ለክፉ ስቃይና መከራ ሲዳርገው መሰንበቱን ገልጿል፡፡
ፓርቲው በዚሁ ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ መንግስት ይህ ታጣቂ ቡድን የጀመረውን ጦርነት አቁሞ ለሰላማዊ ድርድር  እንዲቀርብ ተደጋጋሚ ጥሪ ያስተላለፈ ቢሆንም፤ በህወሃት ታጣቂ ቡድን በኩል ጥሪው ተቀባይነትን ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
ታጣቂ ቡድኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን ለሞት አስረክቦ ተመልሶ በትግራይ ክልል አጥር ውስጥ ተኮራምቶ እንዲቀመጥ መሆኑን ያመለከተው የፓርቲው መግለጫ፤ ቡድኑ ዛሬም የተዘረጋውን የሰላም እጅ በመግፋት ህዝቡን ለዳግም ጦርነት፣ ሞትና መከራ እየዳረገው ነው ብሏል።
ቡድኑ ጦርነቱን በጀመረ ማግስት በረሃብ ምክንያት በበሞት አፋፍ ላይ ላሉ ዜጎች እህል ለማድረስ ከዓለም ማህበረሰብ በእርዳታ የገባውን ከ750ሺ ሊትር በላይ የሆነ ነዳጅ ከረሃብተኞች አፍ በመንጠቅ ለህዝቡ ደንታ እንደሌለው ያረጋግጣል ብሏል-  ፓርቱው በመግለጫው።
ይህንን እብሪተኛ ቡድን ለማቆምና በሰላማዊ ድርድር ወደ ሰላም ለመምጣት የትግራይ ህዝብ በታጣቂ ቡድን ላይ እንዲነሳና ህውሓት ጦርነቱን አቁሞ የሰላም ጥሪውን በመቀበል ከመንግስት ጋር እንዲደራደር ተፅእኖ ማሳደር ይገባዋል ብሏል።  የትግራይ ህዝብ ልጆቹ ከሞት ይታደግ ዘንድ ለህወሓት ታጣቂ ቡድን እምቢተኝነቱን ማሳየት እንዳለበትም ገልጿል። እንዲታጠቅ ተገዶ ለግሰቦች የስልጣን ጥቅምና ፍላጎት በማለቅ ላይ ያለው ወጣት፣ ለወላጆቹ ሰላም ለራሱም ነጻነት ሲል በተመቸው መንገድ የመሳሪያውን አፈሙዝ ወደጨቋኞቹ የህወሓት አመራሮች እንዲያዞር ወይም በሰላም እጁን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል እንዲሰጥ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ትዴፓ ጥሪ አቅርቧል።




Read 12261 times