Friday, 02 September 2022 00:00

ኢትዮ-ቴሌኮም ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ጋር የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌ ብር ለመፈጸም የሚያስችል አሰራር ጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     “በኤጀንሲያችን ኔትዎርክ የለም የሚባል ነገር ታሪክ እየሆነ ነው”


      ኢትዮ ቴሌኮምና የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ፤ የአገልግሎት ክፍያን በቴሌብር እንዲፈጸም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከትላንት በስቲያ የፈጸሙ ሲሆን አገልግሎቱም ተግባራዊ መደረጉ ታውቋል፡፡
አገልግሎቱ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲን የአሰራር ስርዓት በማዘመን ባለጉዳዮች ያለምንም ውጣ ውረድና እንግልት፣በኦንላይን አገልግሎት እንዲስተናገዱ በማድረግ፣ቀላል ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ የሆነውን ቴሌብር ተጠቅመው፣የአገልግሎት ክፍያቸውን በቀላሉ እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ተብሏል። ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሸራተን አዲስ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩና የሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉቀን አማረ የስምምነት ውሉን ተፈራርመዋል።
የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጄንሲ በአሁኑ ወቅት 15 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፣ 27 ልዩ ልዩ አገልግሎቶች እንዲሁም ከ7 ሺ በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ በቀን በአማካይ ከ6.5 ሚሊዮን ብር በላይ የአገልግሎት ክፍያ እያስተናገደ እንደሚገኝ ታውቋል። አዲስ በተተገበረው አሰራር መሰረት፤ባለጉዳዮች በኤጀንሲው አገልግሎት ካገኙ በኋላ በሚላክላቸው ወይም በሚሰጣቸው የክፍያ ማዘዣ ቁጥር በመጠቀም የመኪና ሽያጭ ውል፣ የስጦታ፣ የውክልና፣ የብድር፣ የማህበር ምስረታና ቃለ ጉባኤ የመሳሰሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን በቀላሉ በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር (*127#) በመፈጸም አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ኢትዮ ቴሌኮም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኩባንያው በቅርቡ ሁሉን አካታች የፋይናንስ አገልግሎት የጀመረ ሲሆን እነሱም፡- #ቴሌብር መላ (የግለሰብ ደንበኞች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ወኪሎች የአነስተኛ ብድር አገልግሎት በቴሌብር አካውንታቸው አማካኝነት የሚያገኙበት)፣ #ቴሌብር እንደኪሴ (የቴሌብር ደንበኞች በአካውንታቸው ላይ ያላቸው ቀሪ የሂሳብ መጠን በቂ ባልሆነበት ጊዜ የሚጠቀሙበት) እንዲሁም #ቴሌብር ሳንዱቅ (ደንበኞች ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ መጠን የሚታሰብባቸው የቁጠባ አይነቶችን የሚጠቀሙበት) ሲሆኑ፤ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶቹን ከዳሸን ባንክ ጋር በአጋርነት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።
ከመንግስት መ/ቤቶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የቀድሞው ውልና ማስረጃ፣ የአሁኑ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር፤ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የጀመሩት አዲስ አሰራር በየቀኑ አገልግሎት የሚሰጧቸውን ከ7 ሺህ በላይ ደንበኞች የሚያስደስት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ “ዕድሜ ለቴሌኮም፣ በአሁኑ ወቅት በተቋማችን ኔትዎርክ የለም የሚባል ነገር ታሪክ እየሆነ ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮቴሌኮም የኤጀንሲውን አገልግሎት በማዘመንና በማቀላጠፍ ረገድ ለተጫወተው ጉልህ ሚና፣ በተቋሙና በደንበኞች ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ “ደንበኛ እንዲህ ስለ አገልግሎታችን ብቃት ሲናገር እንዴት ልብ ያሞቃል መሰላችሁ!” በማለት፤ የኢትዮ ቴሌኮም ባለድርሻ አካላትን “እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።
በአገሪቱ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ የሆነው 40 በመቶ ብቻ መሆኑን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤”የፋናንስ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል ኩባንያቸው በጀመረው እንቅስቃሴ ይሄን ክፍተት ለመሙላት እየጣረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“አንድ ባንክ ዓመቱን ሙሉ ከሰጠው የብድር አገልግሎት ይልቅ እኛ በጥቂት ቀናት በቴሌብር የሰጠነው የብድር አገልግሎት ይበልጣል፤” ያሉት ወ/ት ፍሬህይወት፤”ይሄ ልቤን ያላሞቀው ምን ሊያሞቀው ይችላል?” ብለዋል፤በደስታ ተሞልተው፡፡

Read 12128 times