Saturday, 03 September 2022 14:03

አድማስ ዩኒቨርስቲ 14ኛውን የጥናትና ምርምር ጉባኤ ዛሬ ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  አድማስ ዩኒቨርስቲ 14ኛውን ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤውን ዛሬ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በማግኖሊያ ሆቴል ያካሂዳል። ዩኒቨርስቲው ለዘንድሮው ጉባኤ የመረጠው የጥናትና ምርምር ርዕስ “የከፍተኛ ትምህርት ጥራት፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ” የተሰኘ ሲሆን ለአንድ ሀገር ወሳኝ የሆነውን የትምህርት ጥራትና ከዩኒቨርስቲዎች ተልዕኮ አንዱና ዋነኛው የሆነውን የማህበረሰብ አገልግሎት ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካ ቀንድን የሚዳስስ የጥናትና ምርምር ወረቀት በጉባኤው እንደሚቀርብ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ሞላ ጸጋ (ዶ/ር) ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።ፕሬዚዳንቱ አክለውም ባለፉት 13 ዓመታት ዩኒቨርስቲያቸው የትምህርት ጥራቱን ማዕከል ያደረገና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው በዚህ ረገድ ሃላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በዘንድሮውም የጥናትና ምርምር ጉባኤ ከላይ በተመረጠው ርዕስ ዙሪያ ምሁራን ጥናትና ምርምር ስራቸውን እንዲያቀርቡ በመጋበዝና ከቀረቡት ውስጥ የተሻለ ይዘት ያላቸውን በማወዳደር ለጉባኤው ማቅረባቸውን የገለጹት ሞላ ፀጋ (ዶ/ር) በዚህም ዘርፍ እየታየ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መፍትሄ ጠቋሚ የሆኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና  ከባለ ድርሻ አካላት ተወከሉ ሃላፊዎች እንደሚታደሙ ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል።አድማስ ዩኒቨርስቲ በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ካምፓሶቹ ከ20 ዓመታት በላይ በርካታ ዜጎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በማስተማር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ባለሙያ ከማድረጉም በላይ በሀገሪቱ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት በመሙላት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ተቋም ነው ተብሏል።

Read 11960 times