Saturday, 20 October 2012 10:04

ከ70 ዓመት በላይ ለሆኑ አረጋውያን የጡረታ ዋስትና ለመስጠት ታቅዷል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(4 votes)

ከ70 ዓመት በላይ ዕድሜ ላላቸው አረጋውያን በመዋጮ ላይ ያልተመሠረተ ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ ዋስትና ለመስጠት የሚያስችል አሠራር መታቀዱ ይፋ ሆነ፡፡ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ በግዮን ሆቴል ለውይይት ያቀረበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ የመጨረሻ ረቂቅ ላይ ይፋ እንደተደረገው፤ በኢትዮጵያ በመቶ ከሚገኙት 3.6 ሚሊዮን አረጋውያን መካከል በመደበኛ የጡረታ አበል ውስጥ ታቅፈው ወርሃዊ የጡረታ አበል የሚያገኙት 500ሺ ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ አረጋውያን ከቅርብ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በሚያገኙት ድጋፍና በደካማ አቅማቸው ሠርተው በሚያገኙት ጥቂት ገንዘብ ይተዳደራሉ፡፡

ይህንን ሁኔታ ለማሻሻልና የመደበኛ ጡረታ ሽፋንን ለማሳደግ መንግስት በመዋጮ ላይ ያልተመሠረተ ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ ዋስትና ከሰባ ዓመት በላይ ዕድሜ ላላቸው አረጋውያን ተግባራዊ የሚያደርግ አዲስ አሠራር ለመጀመር ዕቅድ ይዟል፡፡ 
በማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ረቂቁ ላይ እንደተገለፀው፤ አረጋውያን ተገቢውን እንክብካቤና ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረጉ ተግባር በበጀት የተደገፈ ባለመሆኑ በአጥጋቢ ሁኔታ እየተተገበረ አይደለም፡፡ ሁኔታውን ለማሻሻልና ዕድሜያቸው ከሰባ ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉም ወንድና ሴት አረጋውያንን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የዕቅዱ ረቂቅ መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡

 

Read 2785 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 10:08