እ.ኤ.አ በ2011 በተደረገው የህዝብና ጤና ጥናት መሠረት፤ 27 በመቶ የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት እስከ 14 ዓመት የሚደርስ ህፃናት ትምህርታቸውንና የመጫወቻ ጊዜያቸውን መሥዋዕት በማድረግ የጉልበት ሥራ በሚጠይቁ የሥራ መስኮች ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
የአገሪቱ የሥራ ገበያ በበቂ ሁኔታ አድጓል ብሎ በድፍረት መናገር እንደማይችል የገለፀው ሰነዱ፤ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሠራተኞች ምንዳ፣ በበቂ ሁኔታ ያላደገ የግብይት ሥርዓት፣ ከፍተኛ የግብይት ዋጋና በሥራ ገበያው ውስጥ ወቅቱን የጠበቀ የመረጃ ፍሰት ሥርዓት አለመኖር ለሥራ ገበያው አለማደግ መገለጫዎች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በሥራ ላይ ያሉት ተቆጣጣሪ ተቋማት በአብዛኛው መደበኛ የሆነው የምንዳ ተቀጣሪ ክፍለ ኢኮኖሚ ሴክተር ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸው፣ የሥራ ዋስትና አለመኖር፣ የማህበራዊ ምክክር አለመጐልበት እንዲሁም የተደራጀ የሥራ ገበያ አገልግሎት አለመኖር ፍፁም ባልሆነው የሥራ ገበያ ውስጥ የገበያ መነቃቃትን የገደቡ ክፍተቶች መሆናቸውን መረጃው ጠቁሟል፡፡