Saturday, 27 August 2022 11:06

ትኩረት ለሁለተኛው የጦርነት ግንባር!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

    “--መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ፣ ችግሩን በድርድር ለመፍታት መፈለጉን ቢያሳውቅም፣ ከትህነግ በኩል ይታይ የነበረው ተነሳሽነት ከቃላት ያለፈ አልነበረም። ሦስተኛውን ዙር ጦርነት ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ንጋት ላይ ሲጀምር ያረጋገጠው፣ ወትሮም ለሰላም ዝግጁ አለመሆኑን ነው።--”
        
        ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ትሕነግ፣ በክልሉ በነበረው የመከላከያ ኃይል ላይ በሴኮቱሬ አገላለጽ፤ “መብረቃዊ ጥቃት” ፈጸመ። ከዚሁ መብረቃዊ ጥቃት የተረፉ የጦሩ ክፍሎች ከፊሉ ኤርትራ በመግባት፣ ከፊሉ የወገን ኃይል እስኪደርስለት  ራሱን በመከላከል ላይ ቆየ። መንግስት ከፍተኛ ሃይል በማንቀሳቀስ ሃያ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ የትህነግን ኃይል በመሰባበር፣ መቀሌ ከተማን ተቆጣጠረ። በዶ/ር ሙሉ ነጋ የሚመራ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም ተቋቋመ።
የትህነግን አገዛዝ የሚቃወሙ ወንድሞችና እህቶች፣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን ተሰለፉ። በትግራይ መሬት ከትህነግ የጸዳ አስተዳደር ይዘረጋ ዘንድ ሙሉ ፈቃዳቸውን ሰጥተው፣  ዳገት  ቁልቁለቱን መውጣት መውረዱን ተያያዙት።  በዶ/ር ሙሉ ነጋ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ስልጣን የያዙት ሰዎች፣ ስጋቸው እንጂ ልባቸው ለፌደራሉ መንግስት ቦታ ስላልነበረው፣ የትግራይ ህዝብ ከትህነግ አገዛዝ ተላቆ ራሱን በአዲስ መንፈስ ይመራ ዘንድ የሚጥሩትን ወገኖች እየመረጡ መግደል ያዙ፡፡ አንዳንዶች ቆስለው ሲተርፉ፣ ሌሎች ታፍነው እንዲወሰዱም ተደረጉ። በሙሉ ነጋ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ እየተሰራ ያለውን ደባ በቅርብ የተረዱት እንደ ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋ ማርያም አይነቶች፣ ችግሩን እየዘረዘሩ ሴረኛውን በስም እየጠቀሱ፣ መንግስት ይሰማቸው ዘንድ እስከሚችሉት ድረስ ጮሁ። መንግስት፣ ጆሮውንም አይኑንም ዘጋባቸው፡፡ የሚያሳዝንና የሚያስተዛዝብ ጊዜ ነበር።
መቀሌ ላይ በዶ/ር ሙሉ ነጋ አስተዳደር ውስጥ የተሰገሰገው አሸባሪው ቡድን፣  በመከላከያ ኃይል ላይ ደግሞ የጥቃት እጁን አነሳ። ጥቃት ደረሰብን ወይም ጥበቃ አድርጉልን ብለው የሚመጡ መልዕክተኞች፣ ጦሩን  ስበው አደጋ ላይ የሚጥሉት ሆኑ።  ጦሩ በተደጋጋሚ ለአደጋ ተጋለጠ።
የዶ/ር  ሙሉ ነጋ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በዶ/ር አብርሃ በላይ ተተካ። ለውጡ የተደረገው እጅግ በጣም ዘግይቶ ስለነበር፣ አዲሱ ተሿሚ ቢሮ ገብተው ተደላድለው መቀመጥ እንኳ አልቻሉም። የዶ/ር አብርሃም ጊዜያዊ የትግራይ አስተዳደር፣ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ለፌደራል መንግስት ባቀረበው ደብዳቤ፣ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጠየቀ። ከዚህ ጥያቄ በፊት መከላከያ ከትግራይ መውጣት መጀመሩን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ለተወካዮች ምክር ቤት  አሳወቁ። ጦሩ ለምን ጥርግ ብሎ ወጣ? ስለምንስ አንዳንድ ወታደራዊና እስትራቴጂያዊ ቦታዎችን ይዞ ለመቆየት አላሰበም? የሚሉ  ጥያቄዎች ቢነሱም፣ የሆነው ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ነው።
የመከላከያ ከትግራይ መውጣትና መንግስት በተናጠል ያወጀው የተኩስ ማቆም፣ ለትህነግ ታላቅ የምስራችና ስጦታ ሆነለት። ሰራዊቱን ከኋላ እየተከተለ በማጥቃት አንዳንድ ከባድ መሳሪያዎችንም በእጁ ለማስገባት እድል እንዳስገኘለትም እየተናገረ ነበር። ትሕነግ ወዲያው ወደ ጦርነት ገባ፡፡ ማይጸብሪ፣ አላማጣ፣ ኮረም ቆቦ  ወዘተ---በተከታታይ በጥቃት ሥር ወደቁ። የአማራ ክልል “የህልውና ዘመቻ” የክተት አዋጅ አወጀ። በአፋር ክልል የተደረገውም ተመሳሳይ ነው።
አሸባሪው ቡድን በደረሰበት የአማራ አካባቢዎች ሰዎችን በግፍ እየረሸነ፣ ከብቶቻቸውን እየገደለ፣ የጓሮ አትክልታቸውን እየጠፈጠፈ፣ የእርሻ ማሳቸውን እያወደመ፤ ሕይወታቸው የተረፈ ሰዎች ወደ ፍጹም ድህነት ላይ እንዲወድቁ አደረገ። የትምህርትና የሕክምና ተቋማትን አፈራረሰ። በአፋር ክልልም ሰዎችን በጅምላ መጨፍጨፉ፣ ግመሎቻቸውን መግደሉ፣ የትምህርትና የህክምና ተቋማትን ማጥፋቱ የሚዘነጋ አይደለም። በዚህ የትህነግ የወረራ ጥቃት አማራ ክልል 280 ቢሊዮን ብር፣ አፋር ደግሞ ከ74 ቢሊዮን ብር በላይ የሃብት ጉዳት እንደደረሰባቸው ገለጡ።
ትህነግ በጦርነቱ እየገፋ መጥቶ ደብረ ሲና ጣርማ በር አካባቢ ደረሰ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  አህመድ ሕዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም ወደ ጦር ሜዳ ተንቀሳቀሱ። አዲስ አበባ በእጁ እንደገባች አስቦ የነበረው ትህነግ፤ በመከላከያ በአማራና በአፋር ልዩ ሃይል እንዲሁም በአማራ ፋኖ እየተቀጠቀጠ ወደ ኋላ እንዲፈረጥጥ ተደረገ። እጅግ አጭር በሆነ ጊዜም በአማራና በአፋር ክልል የሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ከትህነግ ቁጥጥር ነጻ ወጥተው፣ ሰላማዊ ኑሮአቸውን እንዲጀምሩ ተደረገ። እንዲያም  ሆኖ በአማራ ክልል ውስጥ ቆቦና ዋግ ህምራ አካባቢ፣ አንዳንድ ቀበሌዎች በትህነግ እጅ መቆየታቸው አልቀረም።
መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ፣ችግሩን በድርድር ለመፍታት መፈለጉን ቢያሳውቅም፣ ከትህነግ በኩል ይታይ የነበረው ተነሳሽነት ከቃላት  ያለፈ አልነበረም። ሦስተኛውን ዙር ጦርነት ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ንጋት ላይ ሲጀምር ያረጋገጠው፣ ወትሮም ለሰላም  ዝግጁ አለመሆኑን ነው።
ጦርነቱ ለሦስተኛ ጊዜ ከተጀመረ በኋላ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለኢትዮጵያ ሚዲያ አገልግሎት (EMS) በሰጡት መግለጫ፤ “ይህን ስድስት ወር ቦታ ለመያዝ ለማሻሻል እያሉ ትንኮሳ ሲያካሂዱ ነበር፡፡ እኛ ችለናቸው ነው። ተኩስ ከፈቱብን  የሚሉት ጦርነቱን ፊት ለፊት ለማድረግ ምክንያት ለመፈለግ ነው።
ተኩሰን ቢሆንም ለምን ተብሎ ንግግር ይደረጋል እንጂ ውጊያ አይከፈትም። እኛ ተኩስ ማቆሙን ጠብቀን ቆይተናል። ማጥቃት ብንፈልግ ማጥቃት እንችል ነበር። የትግራይ ሕዝብ ተጎድቷል። መፍትሔውን እንዲፈልግ የተውነው ለትግራይ ሕዝብ ነው። የቆየ ልምድ ስለአለን መንግስት ወደ ትግራይ የመግባት ፍላጎት የለውም።” በማለት ተናግረዋል። እዚህ ላይ ትልቅ ችግር አለ።
በሦስተኛው ዙር የጦርነት አጀማመር ላይ መንግስትና ትህነግ እርስ በእርስ እየተካሰሱ ነው። ሁለት ሶስት ቀን ቀደም ብሎ ትህነግ፣ በቃል አቀባዩ በጌታቸው ረዳ አማካኝነት፣ በመንግስት ጥቃት እየተፈጸመብኝ ነው እያለ እየጮኸ ነበር። መንግስት የሰላም ድርድሩን ለማደናቀፍ መንገድ መፈለግ ነው በማለት ሲያጣጥል ቆይቷል።
እኔ ጦርነቱን አልጀመርኩም የሚለው መንግስት አቋም ፈተና ላይ የወደቀው፣ መንግስት ቀደም ሲል የነበሩ ትንኮሳዎችን አደባባይ ለማውጣት ባለመፈለጉ ወይም ችላ በማለቱ እንደሆነ በደንብ በድርብ ሰረዝ ሊሰመርበት ይገባል።
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ድርጅት 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ ከመቀሌ መጋዘኑ በትሕነግ መዘረፉን የድርጅቱ የፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤዝሌይ ገልጸዋል። ይህን ለመግለጽ የደፈሩት ባለስልጣኑ፣ ለምን ወደ ትግራይ ገብተው የትሕነግ ሰራዊትና መሳሪያ ማጓጓዣ ስለሆኑት ከአንድ ሺህ በላይ ከባድ መኪናዎች አይናገሩም?› ለምንስ መንግስት ይህን ወንጀል ደጋግሞ አያጋልጥም? ብሎ መጠየቅም አስፈላጊ ነው። እንዲህ አይነቱን የፕሮፓጋንዳ ጥሬ እቃ ንቆ ማለፍም ያስተዛዝባል።
በውጊያ ውስጥ የጦር ሜዳ አሸናፊነት ብቻ አይበቃም። የሰራዊት ሞራልም መገንባት አለበት፡፡ የሰራዊት ሞራል የሚገነባው በየግንባሩ የሚያገኘው ድል፣ ሌላው ሲነገረውና አበጀህ ሲባል ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላይ የሚሳየውን ቸልተኝነት ፈጥኖ ሊያርመው ይገባል። ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ በትሕነግ መበለጡ በጣም የሚያሳዝን ነው። ይህም ሌላው የጦር ግንባር ነውና፣ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ አስቦና ተጨንቆ በቂ ዘማች ሊያሰልፍበትም ይገባል፡፡
ዓለማቀፉን ጫና ማስቀረት ካልሆነም እንዲቀንስ ማድረግ የሚቻለው፣ በዚህ መስክ አብዝቶ መስራት ከተቻለ ብቻ ነው።
ድል ለመከላከያ ሠራዊትና ከጎኑ ለተሰለፉት ሁሉ!


Read 1889 times