Saturday, 27 August 2022 11:01

ኃያላኑ የኢትዮጵያ ዳግም ግጭት አስደንግጦናል አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ተኩስ እንዲቆምና ንግግሩ እንዲቀጥል ጠይቀዋል

         በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀ  በሰው ጦርነት አስደንግጦኛልም አሳዝኖኛልም ያሉት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆምና ንግግሩ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያሳሰቡት ዋና ፀሀፊው፤ የሰብአዊ እርዳታዎች እንዳይስተጓጎሉ እንዲሁም ችግሩ በውይይትና ድርድር የሚፈታበት መንገድ ላይ ሁለቱም ወገኖች እንዲያተኩሩም በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ማለዳ ላይ ትግራይን በደቡብ በኩል በአማራ በሚያዋስኑ አካባቢዎች ለተጀመረው ጦርነት የፌደራል መንግስት ህወሓትን በተንኳሽነት ተጠያቂ ሲያደርግ፣ የህወሃት ቡድን በበኩሉ የፌደራሉን  መንግስት ተጠያቂ ማድረጉን ያነሱት ጉቴሬዝ፤ ከአምስት ወራት የተኩስ  ማቆም አቋም ሂደት በኋላ ድንገት ግጭት መቀስቀሱ እጅግ አስደንጋጭ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በበኩላቸው፤ ግጭቱ በአስቸኳይ ቆሞ በንግግር ብቻ መፍትሄ እንዲመጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ በኩል ድርድር የሚፈጠርበትን ሁኔታ በማመቻቸት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰውም፤ ሆኖም ነገር ግን በህወሓት እምቢተኝነት እንዳልተሳካ ሊቀ መንበሩ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡
አሁንም የአፍሪካ ህብረት ጦርነቱ በሚቆምበት ሁኔታ ላይ አበክሮ እንደሚሠራ፣ ለዚህም ሁለቱም ተፋላሚ ሀይሎች ከህብረቱ ተወካይ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ጋር  እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ላለፉት 5 ወራት የነበረው የተኩስ አቁም የበርካቶችን ህይወት መታደጉንና እርዳታ እንዲደርስ ማስቻሉን ያወሱት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ ዳግም የተቀሰቀሰው ግጭት አሜሪካንን ስጋት ውስጥ እንደከተታት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስና በመጨረሻም ግጭቱን በዘላቂነት ለማስቆም ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ብሊንከን ጥሪ አቅርበዋል።
“እንደገና ወደ ጦርነት መግባት የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ በሚጥሩት ላይ ሚና እንደሚጫወት፣ የሰዎችን መጠነ ሰፊ ስቃይ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣና ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ያስከትላል” ብለዋል-ብሊንከን።
አንቶኒ ብሊንከን አክለውም “አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅና ለአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ቁርጠኛ አቋም  አላት። አገሪቷ ያጋጠማትን ሁለንተናዊ ተግዳሮቶች፤ ታሪካዊ ድርቅን ማሸነፍና ክልላዊ ደህንነትን ማስፈንን ጨምሮ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነን።” ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና  የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳት ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ግጭት ማገርሸቱን የሚገልፁ ሪፖርቶች የሰላም ተስፋ ላይ ጥላቸውን ያጠላሉ ብለዋል።
ሁሉም ወገኖች ሁኔታው ይበልጥ ከመባባሱ በፊትና ወደለየለት ጦርነት ሳይገባ ግጭቱን እንዲያረግቡም ጠይቀዋል።
“ወቅቱ ለሰላም ውይይት የሚደረግበት ጊዜ ነው” ብለዋል-ቦሬል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ግጭት መቀስቀሱ እንደሚያሳስባት የገለጸችው እንግሊዝ በበኩሏ ሁኔታው ወትሮም አስከፊ ነበረውን የሰብአዊ ሁኔታ ይበልጥ ያባብሰዋል ብላለች።
የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሓት ግጭት እንዲያቆሙና የፖለቲካ መፍትሄ ይመጣ ዘንድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር እንዲመጡ እንግሊዝ አሳስባለች።
ቱርክ በበኩሏ በፌደራል መንግስት ለሰብአዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ከታወጀ በኋላ ድግም ግጭት መቀስቀሱን የሚገልፁ ሪፖርቶች መውጣታቸው እንዳሳሰባት ገልጻ፤ ሁለቱም ወገኖች ግጭት በዘላቂነት እንዲቆም ለማድረግና በአገሪቱ ሰላና መረጋጋት እንዲሰፍን ወደ ንግግር እንዲመለሱ ጠይቃለች።
በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ቱርክ ገልጻለች።


Read 11868 times