Print this page
Saturday, 20 August 2022 13:01

‘ከተሜነት’ ሊናፍቀን ነው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በተለይ የደቡብ አሜሪካና የአንዳንድ የእስያ ሀገራት ዋና ከተሞችን ህዝብ ስናይ...አለ አይደል...ይሄ ሁሉ ህዝብ እንዴት ነው የሚኖረው እያልን እንገረም ነበር፡፡ ይኸው እኛ ወደዛ እየተጠጋን ይመስላል። የምር ግን እንግዲህ ጨዋታም አይደል... እዚች ከተማ ያለን ስንት ሚሊዮን እንሆናለን? አሀ...ልክ ነዋ! ቁጥር አለማወቅን የመሰለ አስቸጋሪ ነገር የለማ! እናላችሁ... የከተማዋ ብዙዎቹ ክፍሎች በሰው ጎርፍ እየተጥለቀለቁ ነው፡፡ እናላችሁ... ከሌሎቹ በሰው ከሚጨናነቁባቸው ከተሞች ጋር አንዱ ልዩነታችን ምን መሰላችሁ... የሌሎቹን ስናይ አብዛኛው ሰው ተረጋግቶ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ብዙ ግፊያ፣ ጉንተላ፣ መደነቃቀፍ ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ አንዱ የ‘ስልጣኔ’ ምልክት ይሄ ነዋ!
ታዲያላችሁ እኛ ዘንድ ደግሞ የምር እኮ አንዳንድ መንገዶች ህዝብ መተላለፊያዎች ሳይሆኑ ጣራ የሌላቸው የነጻ ትግል መድረኮች ሊመስሉ ምንም የቀራቸው አይመስልም። እኔ የምለው፣ ቆዩኝማ... የጤፉ ዋጋ ጣራ ላይ፣ የስንዴና የፉርኖ ዋጋ ጣራ ላይ፣ የሥጋ ዋጋ ከጣራም አልፎ ትንሽ ቆይቶ ጎፈንድ ሚ ምናምን ሊያሳስብ ጣራ በነካበት፣ ይሄ ሁሉ ሰው እንዲህ የሚያስፈነጥር ትከሻ የሚያወጣው ምን ቢመገብ ነው! አሀ  መጠየቅ አለብና! ዘንድሮ የሚመነጠረው ያልጠረጠረው ብቻ ሳይሆን፣ በአንዳንድ ነገሮች ላይ ጥያቄ ያልጠየቀው ነው፡፡
ደግሞላችሁ ከሀያ አራቱ ሰዓታት አስራ ምናምኑ 'ረሽ ሀወር' የሚባለው የግርግር ሰዓት የሚመስልባት የእኛዋ ከተማ ሳትሆን አትቀርም፡፡ አሀ...ሰው ሁሉ ሥራ ላይ ነው በሚባልበት ከረፋዱ ሦስት ከምናምን፣ አራት ሰዓት በአንዳንድ የከተማው ክፍሎች የሚታየው የሰው ብዛት ይገርማል፡፡ የመኪና መንገዶቹም ከሥራ መግቢያና መውጫ ውጭ ባሉ ሰዓታት ጭር ማለታቸው ቀርቶላችሁ እነሱም ሳይነካኩ ይገፋፋሉ፡፡
“ስማ ነገ የማዋራህ ጉዳይ ስላለኝ ስድስት ተኩል ወይ ሰባት ሰዓት አካባቢ ፒያሳ እንገናኝ።”
“እሺ ግን ሰዓቱን ለውጠው፡፡”
“ለምን፣ ሌላ ጉዳይ አለህ እንዴ!”
“ሌላ ጉዳይ ኖሮኝ ሳይሆን፣ በዛ ሰዓት እኮ ግርግር ይበዛል፡፡”
“ታዲያ ስንት ሰዓት ቢሆን ይሻላል?”
“ጠዋት ሦስት ተኩል ወይም አራት ሰዓት አድርገው፡፡ ያን ጊዜ ጭር ይላል፡፡”
እንዲህ ይባል የነበረው ያኔ ነው፡፡
እናላችሁ...መቼም ጨዋታም አይደል...ችግሩ መብዛታችን ሳይሆን የከተማዋ ሥርአት! እኔ የምለው...ከተሜነት የሚባል ነገር አለ አይደል እንዴ! አሀ ልክ ነዋ...የስምንት ሺህ ብር ስኒከር ማድረግ ብቻ ከተሜነት አይደለማ! በድቅድቅ ጨለማ ድፍን ጥቁር የፀሀይ መነጽር ማድረግ ብቻ ከተሜነት አይደለማ! (ቂ...ቂ...ቂ...) ስማኝማ እንትና... እንደው ጨለም ሲል ‘መነጥሩን’ ብታወልቀው፣ እንትናዬዎቹ እንደ ፋራ አያዩህም፡፡ ደግሞላችሁ...የሚገፋተረው፣ መንገድ ላይ ፊት ለፊታችሁ እግራችሁ ስር እንትፍ የሚለው፣ እንዳለ ሰማንያ ሰባት ኪሎ ‘ፍሌሽና ቦኑን’ እላያችሁ ላይ የሚከምረው!...ብቻ ምን አለፋችሁ፣ ‘ከተሜነት’ ሊናፍቀን ምንም አልቀረን!
ስሙኛማ... ከተጫወትን አይቀር...በየመሥሪያ ቤቱ ዓመታዊ ሪፖርት ቀርቦ አበቃ እንዴ! አይ እሱ ነገር ሁልጊዜም ስለሚገርመን ነው፤ ሰኔና ሐምሌ ከች ይላሉ፣ እናማ ዓመታዊ ሪፖርት ይቀርባል ...“በዓመቱ ውስጥ በገጠሙን የተለያዩ የውስጥና የውጭ ችግሮች፣ ድርጅታችን በዚህ ዓመት ሊያሳካ በእቅድ ከያዘው ምርት፣ በሠራተኞቻችን ብርቱ ጥረት 45% አሳክቷል፡፡” “ኢሮ!” ጭብጨባ! እናማ... አለቅዬው ስለተጨበጨበላቸው ደስ ይላቸዋል። ነገርዬው እኮ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ፣” አይነት ነው፡፡ እንተዋወቃለና! በእኛይቱ ሀገር በብዙ ቦታዎችና በብዙ አጋጣሚዎች ጭብጨባ አድናቆት መግለጫ ብቻ መሆኑ  ቀርቷል፡፡ ጭብጨባ የ“አብሮ መኖር በአገር ዙሪያ” አንዱ ዘዴ ነው፡፡ በተቆጡና ቁጣቸውን በጡንቻ የሚወጡ ዓይኖችን ውስጥ ላለመግባት አንዱ ‘ስትራቴጂያዊ መንገድ’ ነው፡፡
እናላችሁ... እንዲህ ሆነን እያለ እኮ ሰዎች በጭብጨባ ሲደሰቱ ስታዩ ግራ ይገባችኋል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ...እየተዋወቅን! ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ መሆኑን እየተነቃቃን! ለምን ይዋሻል... ከሚያጨብጨቡት መሀል እኮ አንዳንዱ ሆዱ ብግን እያለ... “ሀገሪቱ ቲማቲም በርካሽ የማይገኝባት ሆነችና ነው እንጂ እንደው አንድ ሁለት ቲማቲም ይዞ...” ምናምን ብሎ የሚያስብ ሊኖር እንደሚችል በመዝገብ ይያዝልንማ!
ታዲያላችሁ... የተጨበጨበላቸው የመሰላቸው አለቃ ይቀጥላሉ... “በመጪው ዓመት ምርታችንን 105% ለማድረስ እቅድ ተይዟል፡፡” ደብልቅልቅ ያለ ጭብጨባ! ይሄኔም በቃ የሚወዳትን አሻንጉሊት የሰጡት ህጻን ሆኖላችሁ ቁጭ ነው፡፡ (ሲያጨበጭቡብንና ሲያጨበጭቡልን የመለያ  ዘዴዎችን ሹክ የሚለን ይጥፋ!) ደግሞላችሁ...ሌላኛው መስከረም ይገባና ጊዜውም ‘ይሮጥና’ ሰኔና ሐምሌ እንደገና ከች... ሪፖርት ማቅረቢያ ስብሰባውም ከች! ሰውየው ምን የመሰለች የግል ታርጋ የለጠፈች መኪና ይዘዋል፡፡ ሽክም ብለዋል፡፡
“ስማ፣ አለቃችን እንዲህ አይነት የሆሊዉድ አክተሮች የሚይዙትን የሚመስል መኪና በየትኛው ብሩ ነው የሚገዛው?”
“አንተ ያምሀል እንዴ?”
“ምነው...ምን አጠፋሁ?”
“ሰው ምን ይለኛል አትልም! በአሁኑ ጊዜ እንደእሱ ተብሎ ይጠየቃል!”
“ታዲያ እንዴት ተብሎ ሊጠየቅ ነው? ሰውየው ስንት ልጆች እንዳሉት ትውቃለህ? አምስት! እና አምስት ልጆች ያሉበት ቤተሰብ እያስተዳደረ፣ እንዴት ነው ይቺን የመሰለች መኪና የሚገዛው?”
“ነገርኩህ እንግዲህ..እዚህ ሀገር ባለስልጣን፣ ሀብታም፣ፖለቲከኛ፣ አክቲቪስት ምናምን ገንዘብ ኬት አመጡ አይባልም፡፡”
 ምንም እንኳን በተያዘው እቅድ መሰረት ማሳካት ባንችልም፣ በማኔጅመንቱ ያልተቋረጠ ጥረትና በሠራተኞቹ ታታሪነት የምርት መጠናችንን ቀደም ሲል ከነበረበት ወደ 48% ማድረስ ተችሏል፡፡ “ኢሮ!” ጭብጨባ! “ያሉብንን ችግሮች አስወግደን በተከታዩ ዓመት.....” 'ላውድ' ላይ የተደረገ ድምጽ ብቻ።  ኢሮ! ጭብጨባ! እናላችሁ አላስፈላጊና ሰው ሊሳተፍባቸው የማይችሉ ጭበጨባዎች ድምጽ ብክለት እየፈጠሩብን ነው ለማለት ያህል ነው፡፡
እኔ የምለው...የከተማችን አሽከርካሪዎች ምን ሁኑ እያላችሁን ነው! እሺ ይሄ ዝናብ ከዘነበ በኋላ በየመንገዱ የሚፈጠረውን ኩሬ ውሀ የምትረጩብንን ለምደነዋል፡፡ ግን እጃችሁን ከመኪናው ጥሩምባ ላይ አንሱልና! መኪናውን ሁሉ ቀይ መብራት ጥርቅም አድርጎ ይዞት፣ ይሄ ሁሉ ጥሩምባ ማንባረቅ ምን የሚሉት ረብሻ ነው! ድሮ ቢሆን እኮ የሆነ አጅሬ መኪና ሲይዝ ሰው ሁሉ እንዲያይለት ሲያምባርቀው ሊውል ይቸላል፡፡ ዘንድሮ እኮ አይደለም የእናንተን መኪና ልናይ፣ ኑሮ ራሱ እኛን በአምስተኛ ማርሽ የሚበር መኪና አድርጎን፣ ፍጥነት መቆጣጠሪያው ግራ ገብቶናል፡፡ ብቻ እጃችሁን ከጥሩምባው ላይ አንሱልንማ!
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አንዳንድ ጊዜ ዜና ምናምን ነገር ላይ “ሀገራችን ውስጥ መኪና በከፍተኛ ቁጥር እየበዛ ነው፣” ምናምን ሲባል ትሰማላችሁ! “የመኪናው ቁጥር እየጨመረ ነው፣” ማለት አንድ ነገር ነው፡፡ ግን “እየበዛ ነው፣” ማለት ሌላ ነገር ነዋ! ልክ እኮ በሆነ ባልሆነው “ሀገራችን በእንትን ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ፣” “በእንትን ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ...” ምናምን እያልን ክፍለ አህጉራቱን ሁሉ እንደምናካልለው አይነት ነው፡፡ እናላችሁ...መቶ ሀያ ምናምን ሚሊዮን ህዝብ ባለባት ሀገር፣ በመኪና ብዛት ከህዝቡ ቁጥር በቅጡ ሁለትና ሦስት መቶኛ ሳንደርስ “በዛ...” ብሎ አማርኛ ‘ፌይር’ አይደለም፡፡ እናማ የአሥራ ምናምን ሚሊዮን፣ የሀያ ምናምን ሚሊዮን ብር መኪኖች፣ በዚች በድሀ ሀገር መንገዶች ላይ ታዩና “መኪና በዛ...” ብሎ ነገር ቅሽምና እንዳይሆንብንማ! የበዛ ነገር የለማ...ከግለኝነት በስተቀር!
 እናላችሁ “መኪና በዛ...” የሚለውን አባባል ለመጠቀም ጊዜው ገና አይመስላችሁም!
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል...የመኪና ነገር ከተነሳ አንድ ከዘመኑ ጋር ሊለወጥ ያልቻለ አስተሳሰብ አለ፡፡ መኪና ያለው ሁሉ ወይ ሀብታም፣ ወይ ሀብታም ዘመድ ያለው ምናምን ተደርጎ ነበር የሚታየው፤ መኪና የሀብት መገለጫ ተደርጎ ይታይ የነበረበት ዘመን ነውና! ግን እኮ በብዙ ሀገራት መኪና እንደ ሀብት መገለጫ የሚታይበት ዘመን አልፏል። መኪና እኮ ቅንጦት መሆኑ ቀርቶ ማንኛውም ሰው ከሚያስፈልጉት ነገሮች እንደ አንዱ መታየት ከጀመረ ከራርሟል!  
“አንቺ ያ ላይ ሰፈር ያለው ዘመድሽ መኪና ገዛ እንዴ?”
“አዎ፤ ከገዛ መንፈቅ ያህል ሆኖታል፡፡”
“እንደው በሞቴ፣ ያንን ሁሉ ገንዘብ ከየት አገኘው?”
“ብቻ አልሰማሁም እንዳትዪኝ!”
“ምኑን?”
“ሥራ ለቆ ንግድ ውስጥ ገብቶ የለም እንዴ!”
ጎሽ፣ ጎሽ ታዲያ እንደሱ አትይኝም! እኔ ደግሞ ሀሳብ ይዞኝ!”
“ለምን?”
“ደግሞ ያንን የመሰለ ጨዋ ልጅ አነካክተው የሆነ ነገር ውስጥ ከተዉት እንዳይሆን ብዬ ነዋ!”
አዎ...እዚህ ሀገር ደሞዝተኛ ተስፍንጥሮ አደገ ከተባለ ከሀገር ውስጥ ጫማ ምናልባት ወደ ውጭ ጫማ ይሸጋገር እንደሆን እንጂ ባለመኪናነት ‘ለሀብታም’ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ያሉ ወጎኖቻችንን ልብ በሉልኝማ፡፡ የግድ ለሥራ ስለሚያስፈልጋቸው የአቅማቸውን ያህል ይይዛሉ፡፡ በዛና በበርካታ ሌሎች ሀገራት መኪና ቅንጦት የሚሆነው ምናልባትም በስሪቱ ማለትም በብራንዱ ይሆናል እንጂ መኪና ያለው ሰው ገንዘብ ያለው ማለት አይደለም፡፡
ስሙኝማ...የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ! ለረጅም ጊዜ ስንሸወድ ኖረናል እኮ! መኪና ደገፍ ብለው ፎቶ ተነስተው ሲልኩልን አለ አይደል ኮምፕሌክሰ በኮምፕሌክስ ሆነን ቁጭ። “ሁልጊዜ ለቁርሱ ጮርናቄና ሻይ ስገዛለት እንዳልኖርኩ፣ እሱ ፈረንጅ ሀገር ሄዶ ባለመኪና ሆነ!” ብቻ መኪና የሀብት መገለጫ መሆኑ ቀርቶ ማንኛውም ዜጋ ሊይዘው የሚገባ መገልገያ ሆኖ የሚታሰብበትን ጊዜ እንናፍቃለን፡፡ እስከዛ ግን ባለመኪኖች ይሄ የጥሩምባችሁን ነገር ተዉንማ!
‘ከተሜነት’ እኮ ሊናፍቀን ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1771 times