Saturday, 13 August 2022 00:00

የዘነበ ወላ “አይ ፐሲዜ እና ሌሎች ወጎች” ለንባብ በቃ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ “አይ ፐሲዜ እና ሌሎች ወጎች” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ከሰሞኑ ለንባብ በቅቷል፡፡
ደራሲው፤”የተከበራችሁ አንባቢያን” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ማስታወሻው፤ “እዚህ ጥራዝ ውስጥ የምታገኟቸው ወጎች አዳዲሶችም ከዓመታት በፊት የጻፍኳቸውም ናቸው።” ብሏል።
ከአንጋፋ ደራሲያን ጋር ያደረገውንም ቃለ-ምልልስ በዚህ መድበል ውስጥ ማካተቱን ጠቅሷል- ደራሲው።
የቋንቋና ሥነ-ጽሁፍ መምህርና ገጣሚ ባዩልኝ አያሌው በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት፤ “ዘነበ ወላ የምር ደራሲ፤ ብርቱ የሥነ-ጽሁፍ ሰው ነው። ሳይታክት ዘወትር ያነባል፤ ጠይቆ በአንክሮ ያዳምጣል፤ ሰነዶችን ሳይመረምር ቢሉ በበቂ ሳያጠና የሚጽፍበት ርዕሰ ጉዳይ የለም ብል እያጋነንኩ አይደለም። ዘነበ ድንቅ ተራኪ ነው። ተራና ተርታ የሚባለው ጉዳይ እንኳን በዘነበ ብዕር ሲቀርብ ጣዕምና ለዛው ላሳር ነው። ዘነበ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ በድንቅ ተራኪነታቸው ከማደንቃቸው (በድንቅ ተራኪነታቸው ነው ያልኩት) እጅግ ጥቂት ደራሲያን መካከል ከግንባር ቀደሞቹ የምጠቅሰው ነው። ይህንንም ምልከታዬን ሥራዎቹን ያነበቡ የሚናገሩት ይመስለኛል።…” ብለዋል።
መጽሐፉ በሦስት ክፍሎች የተሰነደና በ288 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን፤በ350 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ደራሲ ዘነበ ወላ ከዚህ ቀደም “ሕይወት በባህር ውስጥ”፣ “ማስታወሻ”፣ “ልጅነት”፣ “መልህቅ”፣ “ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት” እና “የምድራችን ጀግና” የተሰኙ መጻሕፍትን ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል።


Read 16901 times