Saturday, 06 August 2022 14:44

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ማጠቃለያ


          የእኔ ዓላማ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛው በቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘመነ ቅስና የነበሩትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣
ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ቀውሶችን ጠባይ፣ ምንጭ፣ ተገብሮት (Effect)፣ ክትያና ምላሽ፥ ለእኛ በሚኾን መልኩ መመርመር ነው፡፡ የወሰዷቸው
ኹለተኛ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ (ፍልቪያኖስ) እና የጊዜው ባሕታውያን እነዚህን ቀውሶች ለመፍታት ርምጃዎች፥ ለታሪካዊና ወቅታዊ ሕመሞቻችን ድኅነት ሊኾኑ በሚችሉበት ኹኔታ ማጤን ነው፡፡ ሦስተኛ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለአንጾኪያ እና ለአንጾኪያ ቤተክርስቲያን ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲ’ኮ’ ሃይማኖታዊ ስንጥቆችና ሽንቁሮች መፍትሄ እንዲኾን የአደረጉትን ዕሴታዊና ክሂሎታዊ ብቁነቶቹን፥ የሀገራችን የሃይማኖትና የፖለቲካ ልሂቃን ሊማሩበት በሚችሉት አኳኋን ማመላከት ነው፡፡ እነዚህን ሦስት ዓላማዎች በተናጥል ወይም በትስስር ከማሳካት አንጻርበዚህ መጽሐፍ፤ የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን አስተዳደግ፣ የሊቅነት አበቃቀል፣ ታሪካዊ መቼት፣ አእምሯዊ ሥሪት፣ ሥነ ልቡናዊ ውቅርንና ማኅበረ ፖለቲካዊ እሳቤዎቹን በጥንቃቄ ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ የእርሱን ዘመነ ቅስና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓትና መዋቅር ባሕርይን በመጠኑ ለመተንተን ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ እርሱ የተነሣበት ጊዜ የሽግግር ዘመን እንደመኾኑ፥ የቀውስ ዘመን መሻገሪያ ትምህርቶቹንና ተግሣጾቹን፣ አሕዛባዊ የባህል ዕሴትን በክርስቲያናዊ የባህል ዕሴት የመተካት ውጥኖቹን፣ አዲስ ማኅበራዊ ሥርዓት የማዋለድ ተጋድሎውን ለማስገንዘብ ጥሬያለሁ፡፡  የቤተ ክርስቲያን እና የቤተ መንግሥት ጋብቻና ፍቺ፥ በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የሚያሳድሯቸውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖችን ገለጥለጥ አድርጌ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ አኹን ሀገራችን እና ቤተ ክርስቲያናችን የሚገኙበት ኅሊናዊ እና ነባራዊ ኹኔታ፥ አንጾኪያ እና የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ከዛሬ አንድ ሺሕ ስድስ መቶ ዓመታት በፊት ከነበሩበት ኹኔታ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል፡፡ ከዚህ አኳያ ከዚህ መጽሐፍ በኹለት ወገን የምንማራቸው ቁም ነገሮች አሉ፡፡ እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ እና እንደ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበረስብ፡፡ እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ታሪካዊ እና መስክ ወለድ ችግሮችን በጊዜ እና ጊዜ ወስዶ አለመፍታት፥ ለማኅበረሰባዊ ቅራኔ፣ ለሕዝባዊ ዐመፅ፣ ለማኅበራዊ ዕሴቶች መሰባበር፣ ለብሔራዊ ጥርጣሬና ክፍፍል፣ ለእርስ በእርስ እልቂት፣ ለታሪካዊ ቁርሾና ቁርቁስ እንደሚዳርግ ተምረናል፡፡ በብሔረ ሀገር እና በብሔረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ መልክዐ ምድራዊ መስፋትና መጥበብ፣ መገፋፋትና መዋዋጥ፣ ፍጥጫና ጦርነት ክሡታዊ ኹነቶች መኾናቸውን፤ የሀገር ግንባታ ሥራ ትውልዳዊ ቅብብሎሸና የትላንትና የዛሬ ጥረት ድምር ውጤት እንደኾነም ለመገንዘብ የቻልን ይመስለኛል፡፡ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ልሂቃን አለመስከን ወይም የእርስ በእርስ ፍጥጫ ሀገርን ለብተና፤ ማኅበረሰብን ለሰብአዊና ቁሳዊ ጉስቁልና እንደሚያጋልጥ ኹሉ፥ የእነዚህ አካላት ስክነት ለሀገር እና ለማኅበረሰብ ፍቱን መድኃኒት እንደሚኾንም ተምረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚከሠት ቅጽበታዊና ሂደታዊ የማኅበራዊ ዕሴቶች መናጋት፣ የባህልና የዕሴት ተቃርኖ፣ በተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች መካከል ያሉ ማኅበራዊ ግንኙነቶች መዛባት፣ የምጣኔ ሀብት ክፍፍል ኢ-ፍታሐዊነትና የአልተመጣጠነ የሀብት ሥርጭት ይዘዋቸው የሚመጧቸው ሀገራዊ ቀውስ ምንነቶችን በሚገባ ተረድተናል ብዬ እገምታለሁ፡፡


Read 1429 times