Tuesday, 09 August 2022 00:00

መርካቶ

Written by  ከነቢይ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

     “የሰው ፈጣሪ መሐንዲስ አካባቢው ነው”
                             
             የመርካቶ ስም ሲነሳ ዋና መጠቅለያዋ ሆኖ የሚያገለግለን “አራዳነት” የሚለው ቃል ነው፡፡ ጋሽ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ደግሞ በራሱ ቃል “የመርካቶ ልጅ ነቄ ነው” ይለናል፡፡
አንዳንዶች “የመርካቶ ልጅ ቀልጣፋና ጨላጣ ነው!” ይሉታል፡፡
ሌሎች ደግሞ የመርካቶ ልጅ “ቢዝነስ ሁሌም በእጁ ነው” ለማለት ሲሹ፤ “የመርካቶ ልጅ ጦሙን አያድርም” ይላሉ፡፡
አንዳንዶች ደግሞ ፍጥነቱና  አዋቂነቱ እያስደመማቸው፤ “የመርካቶ ልጅ ከጨበጥክ
በኋላ የእጅህን ጣቶች መጉደል አለመጉደላቸውን ቁጠር” ይላሉ፡፡
በሥልጡንነቱና በዕውቀቱ እንዲሁም በልምዱ የሚኮሩት ደግሞ፤ የመርካቶ ልጅ ቱሪስትና ፒስኮር ከለየ የቆየ፣ “ጨውና አሞሌ፣ ወመቴና አለሌ ገና ዱሮ አንጥሮ ያየ”፣ የዕውቀት  ሰው ነው እያሉ፣ በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡
የመርካቶ ልጅ፤ ንግድን ከህይወቱ ጋር ያዋሃደና ልምዱን ለነገ ማዋል የሚችል፣ አዎንታዊ ልዕልና ያለው  የተግባር ሰው ነው፤ ብለው የሚናገሩ አያሌ ናቸው፡፡
የመርካቶ ልጅን የወለደው የመርካቶ ከባቤ -አየር ነው፡፡ ጠበብት በፈላስፋ አነጋገር፤
“Environment is the architect of man” የሚሉን ከዚሁ ምክንያት በመነሳት ነው። (የሰው ፈጣሪ መሐንዲስ አካባቢው ነው እንደማለት፡፡)

ፖስት ራንዴቩ /post rendez- vous/
ዱሮ ዱሮ ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ ሲመጣ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ፖስት ራንዴቩ የሚባል ከሆቴል ዝቅ፣ ከሻይ ቤት ከፍ፣ያለ ሬስቶራንት ነበር፡፡ ራንዴ ቩ- መገናኛ መሰብሰቢያ ቦታ ማለት ነው፡፡ ቃለ - አመጣጡ ከፈረንሳይኛ ነው፡፡ ስለ መርካቶ ስናወራ “ያገር መናኸሪያ- መርካቶ” ብለን ርዕስ ብናወጣ፣ የመርካቶን ባህሪ ይገልጥልናል፡፡ “መርካቶ መነሻ፤ያገር መብቃያ ነው” - ጋሽ ፀጋዬ ገ/መድህን (ሎሬት)
ጣሊያን “መርካቶ እንዲጂኖ” የሚለን፤ ሠፊውን የምስራቅ አፍሪቃ ገበያ የራሱ የሆነ ልዩ ባህሪ ያለው ነው ሲለን ነው፡፡ ሌሎች ፈረንጆች “The indigenous Merkato”  እንደሚሉት መሆኑ ነው፡፡
“ግጥም በስድ-ንባብ ለመባል የማይችል ጥበብ ነው፡፡” ቢባልም፣የፀጋዬ ገ/መድህንን “አይ መርካቶ” ከመጥቀስ አይገታኝም፡፡ አበው የግጥም ሰዎች፤በዝርው (prose) ሲገልጡት፤ “ግጥም ወደ ሕይወት መግቢያም፣ ከህይወት መውጪያም ነው” ይሏልና፣ እኔ በከፊል ቆንፅዬ ስንኙን አጋራችኋለሁ፤ ዓላማችን መርካቶን እንደ ፅላት ገልጦ ማየት ነውና፡፡
አይ መርካቶ
አገር ከየጎራው ወጥቶ
አንቺን ብሎ ነቅሎ መጥቶ
ግሳንግሱን ጓዙን ሞልቶ
ህልቆ መሳፍርትሽ ፈልቶ
ባንቺ ባዝኖ ተንከራትቶ
እንደባዘቶ ተባዝቶ
ተንጠራውዞ ዋትቶ ዋትቶ
አይ መርካቶ!
የምድር ዓለም የእንጀራ እናት
ላንዱ ርካሽ ለሌላ እሳት
ላንዱ ፍርሃት ላንዱ ምትሃት
ላንዱ ሲሳይ ላንዱ ፍርሃት
ላንዱ ተስፋ ላንዱ ሥጋት
የግርግር የሆይታ ቋት
አይ መርካቶ!
መርካቶ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ሰፊ ገበያ ነው፡፡ የመርካቶ ትልቁ አዳራሽ፤ በበላይ ተክሉ ኬክ ቤት፣ በዋንዛ ካፍቴሪያ፣ በዋርካ ካፍቴሪያና በሰሜን ሻይ ቤት፣እንዲሁም ወደ አራተኛ ሲል ባለው በምስራች ሆቴል እና በበርካታ ልብስ ሱቆች የተከበበና የታጀበ ነው፡፡
ማህል አዳራሽን የመርካቶ ዕምብርት አድርገን አራቱንም ማዕዘናት በምናብ ለማየት ብንሞክር፣ በዙሪያውና በአካባቢው ማን ማን እንዳለ ጠቅላላ ስዕል እናገኝ ይሆናል፡፡
በምስራቅ፣ ወደ ናዝሬትና ሐረር መውጫ አለ
በምዕራብ፤ ወደ ጅማና ወለጋ መውጫ አለ፡፡
በሰሜን፤ ደሴ- አሥመራ መንገድ አለ
በደቡብ፣ አርሲና ባሌ መውጫ ይገኛል
ያም ሆኖ መውጫዎቹ በጣም ሰፋፊ በመሆናቸው ዕቅጩን መናገር አይቻልም። ምናልባት ወደ ፊት ሶፎራቶ ፕላን (ጠቅላይ ካርታ ከአውሮፕላን ዕይታ) ከማዘጋጃ ቤት ካገኘሁ መረጃውን አሟላው ይሆናል፡፡

Read 9725 times