Sunday, 07 August 2022 00:00

የዋሽንግተን ውጥን - የዐረብ ሀገራትና የእስራኤል ወታደራዊ ጥምረት ወይስ “የዐረብ ኔቶ?”

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ - ከቤተሳይዳ ሜሪላንድ አሜሪካ
Rate this item
(3 votes)

  የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በቅርቡ በመካከለኛው ምስራቅ የሥራ ጉብኝት አድርገው መመለሳቸው ይታወቃል፡፡  የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ዓላማ፣ በሩስያና ዩክሬይን የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ፣ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ንረት መምጣቱን ለማስታገስና በተለይም በአሜሪካ ውስጥ ያለውን የነዳጅ ውድነት ለማለዘብ እንዲረዳ፣ የዐረብ ሀገራቱን “ምርቱን ጨምሩ - ኮታውን ገፋ አድርጉት“ ለማለት እንደሆነ በዜና አውታሮች ሲዘገብ ተሰምቷል፡፡ በባህረ ሰላጤ ሀገራት የትብብር ምክር ቤት ማለትም GCC  በዚሁ አጋጣሚ ዓመታዊ ስብሰባውን አከናውኖም ነበር፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ ምክንያቱ ይፋ ባይሆንም፣ ግብፅ ኢራቅና ዮርዳኖስ እንዲገኙበት የተደረገ ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ተገኝተው ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከ’እንግዲህ እኛ [አሜሪካ ማለታቸው ነው] የምንተወውና በሩስያ፣ በቻይናና በኢራን የሚሞላ ክፍተት የለም’ በሚል በይፋ ለዐረብ ሀገራቱ ተናግረዋል - በጉባዔው፡፡ በምዕራቡ የዜና  አውታሮች (አሜሪካንን ጨምሮ) - ‘ከነዳጅ ዘይት’ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለመነጋገር ሲባል ከሳውዲት ዐረቢያ  ጋር ዋሽንግተን ግንኙነቷን ለማለሳለስ የምትሞክርበት  ጉዞ ተደርጎም ሲወሳ ሰንብቷል። ይሁንና የአሜሪካ አቢይ ዓላማ ግን ከዚህ በላይ ሰፊና ውስብስብ እንደሆነ መረጃዎች ያወሳሉ። ከአውሮፓው የጦርነት ማዕበል (የሩሲያና ዩክሬይን) ጋር ተያይዞ በዓለማችን እየተስተዋለ የመጣው አዲስ የሀይል አሰላለፍና ለውጥን በማረቅና ከምትሻው አቅጣጫ ጋር ተገናዝቦ እንዲቀረጽ በማድረግ ረገድ ርዕሰ ሀያሏ አሜሪካ ቸል አለማለቷን አመልካችም እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ እና ከወዲሁ የምትወስዳቸው እርምጃዎችና የፖሊሲ አቅጣጫዎች ይህንኑ አመላካችም ይመስላል፡፡
በአንድ ወቅት የማይታሰብ ተደርጎ ይቆጠር የነበረው - የእስራኤልና የዐረብ ሀገራት ትስስር አሁን አሁን እየመጣ ያለ ይመስላል፡፡ ለረዥም ጊዜ አሜሪካ ልትፈጥረው የሻተችው ስትራቴጂያዊው ትብብር፣ በምዕራብ እስያ ሀገራት ዘንድ እውን ሊሆን ዳር፣ ዳር እያለ ነው፡፡ ይህን ደግሞ የአውሮፓው ጦርነት፣ የሩስያና የዩክሬይን ግጭት አፋጥኖታል ማለት ይቻላል፡፡ ርዕሰ ሀያሏ አሜሪካና የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ሀገራቱ በአውሮፓ የማለቂያው ጭላንጭል የማይታይበት የሩስያና የዩክሬይን ግጭት ካልታሰበ ስጋት ውስጥ የጣላቸው ይመስላል፡፡ የኢኮኖሚ ድቀትና የሩስያ ገንዘብ ዋጋ ይወድቃል የሚለው የቀደመው የምዕራባውያኑ ስሌትም ጸሀይ የገላመጠው ቅቤ ሆኗል፡፡ ይሁንና ሩስያ በጦርነት ከዩክሬይን ጋር በተፋጠጠችበት በዚህ ጊዜ፣ አሜሪካ ዙሪያ ገባ ይዞታዋንና ተፅዕኖዋን ለማስፋት ተደጋጋፊ ጥረቶችን ልታደርግ እንደምትችል ይገመታል። በዚህ ረገድም ‘የስትራቴጂያዊ ማጠንጠኛ’ በምትላቸው ሪጅኖች ርዕሰ ሀያሏ አሜሪካ ይፋና ህቡዕ ሥራዎችን ትሠራለች፡፡ እንደ መካከለኛ ምስራቅ አይነት ውል ከውል ለማያያዝ አዳጋች በሆኑባቸው ሪጅኖች፣ ዋነኛ የምትላቸውን ወዳጆቿን በፋና ወጊነት በመጠቀም የተፋጠነ እንቅስቃሴ ይዛለች፡፡
የአሜሪካው የመከላከያ ዘርፍ ማለትም ፔንታገን እስራኤልን ከዩኤስ አውሮፓ የጦር ማዕከላዊ እዝ ማዕከል (ሴንቲኮ - CENTCOM) ጋር በማስተባበር ካለፈው ዓመት ጀምሮ የያዘው እንቅስቃሴ፣ የዐረብ ሀገራቱን የማስተባበርም ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን መረጃዎች ያወሳሉ፡፡ ዋነኛ ማጠንጠኛው በጸረ-ኢራን ላይ ሆኖ የአካባቢውን የሀይል ማስተባበር ሥራው እንዲሳለጥም፣ የአሜሪካ ምክር ቤት አዳዲስ የህግ ረቂቆችን በተከታታይ ያቀረበበት ስለመሆኑ መመልከት ይቻላል፡፡ የ’ዐረብ ኔቶ’ ዝግጅቱን በተመለከተ በሰኔ ወር ላይ የዩኤስ ምክር ቤት የወታደራዊው ዘርፍ ፔንታገን፣ የእስራኤልንና የዐረብ ሀገራትን የአየር መከላከያ አቅምን የሚያስተባብር ሥራ እንዲሠራ የሚያበረታታ የህግ ረቂቅ እንዲቀርብ ያደረገበት ሁኔታም አለ፡፡  
በነገራችን ላይ የዐረብ ሀገራት ተብለው የሚጠቀሱት በቁጥር 22 ሲሆኑ እነዚህም በዐረብ ሊግ አባልነት የሚታወቁ ናቸው፡፡ ከ400 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በእነዚሁ ሀገራት እንዳሉም ይነገራል፡፡ በአቢይነትም የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚገኙባቸው ናቸው። በእነዚህ ሀገራት የእርስ በእርስ ስምምነትና ሰላም ብዙ ጊዜ በቋፍ ያለ ነው፡፡ ሳውዲት ዐረቢያ ከኳታር - ሌባኖስ ከሶርያ - ሞሮኮ ከአልጄሪያ ወዘተ.. ሲጋጩ ይታወቃልም፡፡ የዐረብ ሀገራቱን አንድ ለማድረግና ለማስተባበር ብዙ ጊዜ በተለያዩ መንገዶች ያልተሳኩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በ1960ዎቹ የዐረብ ብሔረተኛነት እንቅስቃሴ ‘ፓን ዐረብ’ በሚል እስከ ውህደት ያለመ እንቅስቃሴም ተከናውኗል፡፡ ከዚያም በለጠቀው ጊዜ በሀይማኖት የማቀናጀትና አንድ የማድረግም ሂደት የተሞከረበት ሁኔታ ነበር፡፡
አሁን በአሜሪካ ፋና ወጊነት የተያዘው የ’ዐረብ የኔቶ ምስረታ’ የሚመስለው እንቅስቃሴ ግን ለየት ያለ ነው፡፡ ስትራቴጂያዊ ትብብርን ያለመና በቅርጽም በይዘትም ‘ከሰሜን አትላንቲክ ወታደራዊ ቃል ኪዳን ትብብር’ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ የዐረቡ ዓለም የሺዓ እስልምና ፊና ተከታይዋንና የዚያ ፊና መሪ የሆነችው ኢራንን በጠላትነት የፈረጀበት እንቅስቃሴ እንዲጠናከር የሚያደርግ ነው፡፡ የሱኒ እስልምና ተከታይና መሪዋ ሳውዲት ዐረቢያ ከኢራን ጋር ያላትን ባላንጣነት የተንተራሰ ወታደራዊ ትብብርም ነው የሚስተዋለው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ባላንጣዎች በሶሪያ፣ በሌባኖስና በየመን በከፉ ወታደራዊ ግጭቶች በእጅ አዙር ተዘፍቀው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡  
አሜሪካ ከኢራን ጋር ያላት መፋጠጥን ተከትሎ ከዐረባውያኑ ሀገራት ጋር ያለው ቅራኔን በመጠቀም የሀይል አሰላለፉን ወደምትሻው የማቀናጀት ሥራው በብርቱ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ የዐረብ ሀገራቱ ‘ኔቶ’ ምስረታን ከዮርዳኖሱ ንጉሥ አንስቶ እስከ እስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ድረስ በድጋፍ የሚገፉት ነው፡፡ በዚህ ውጥን ዙሪያ በአቢይነት ግብፅ ምስጢራዊ ንግግርና ድርድር የሚካሄድባት ስፍራና ዋና አጋፋሪ ናት፡፡ ለዚህ አስረጂ የሚሆነው ከአሜሪካ፣ ከእስራኤል፣ ከሳውዲት ዐረቢያ፣ ከኳታር፣ ከዮርዳኖስ፣ ከተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች፣ ከባህሬንና ከግብጽ የተውጣጡ ወታደራዊ ሹማምንት እዛው ግብጽ በሸርማን ሼክ ምስጢራዊ ወታደራዊ ስብሰባ ማድረጋቸው ነው፡፡  የስብሰባው ሂደትና ውጤት በይፋ ባይነገርም፣ የዚሁ የዐረቡን ዓለም የወታደራዊ ይዞታ ቅንጅት የተመለከተ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የዐረቡ የጦር ቃልኪዳን ትብብር አባላቱ እነማን ሊሆኑ ይችላሉ? ዓላማውስ ምንድን ነው? እንቅፋቶቹ  ምን ሊሆኑ ይችላሉ? የሚሉትን መመለስና ዐረባውያኑ ሀገራትን የማስተባበር ሂደት ግን እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም፡፡ በዙሪያዋ ይህ የሚጠነጠንባት ኢራንም ሆነች በርቀት የሀይል አሰላለፉ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድርባቸው ሩሲያና ቻይናን የመሳሰሉት ሀገራት ምን የአጸፋ ምላሽ  ይሰጡ ይሆን? የሚለውን ታሳቢ ማድረግም ይገባል፡፡
ለነገሩ የዐረብ ሀገራቱን ወታደራዊ ትብብር መፍጠር በቁሙ አዲስ ሀሳብ አይደለም። በ2015 እ.ኤ.አ. የዐረብ ሊግ ወታደራዊ ቅንጅትን ስለመፍጠር የተወያየበት ጊዜ ነበር። ሽብርተኛነትን ከመታገልና ከመቋቋም ጋር፣ የአሜሪካንን አቅጣጫ ያዋሀደ እንደነበረም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በ2017 ደግሞ በአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በሳውዲት ዐረቢያ የጸደቀው ሰነድ፣ ስድስት የዐረብ ሀገራትን ያካተተና የሚያስተባብር የደህንነትና የወታደራዊ ቅንጅትን የሚጠይቅ ነበር፡፡ ይሁንና የሚጠበቀውን ያህል ሳይተገበር ወይም ሕልው ሳይኖረው ቆይቷል።
የዐረብ ሀገራትና የእስራኤል የወታደራዊው ትብብር አቅጣጫ፣ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተራመደው  የ’ዓረብ ኔቶ’ እሳቤ ልዩነቱ እምብዛም  ነው። የሚያስገርመው የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የተሰረዘውንና ከኢራን ጋር በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጊዜ የተጀመረውን የዩኤስና የኢራንን ንግግር ያስቀጥላል የሚል ግምት ነበር፡፡ የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባይደን፣ የያኔው ም/ፕሬዚዳንት፣ ኢራን የኒውክሌር ሀይል ለመሆን የምታደርገውን ግስጋሴ እንድታቆም የሚደረገውን ጥረት ደጋፊ ነበሩ፡፡ እንደውም አሁን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አንቶኒ ብሊንከን፣ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር፣ “የዐረብ ኔቶ” ሀሳብን  ባመነጨ ጊዜ፣ “ዩናይትድ ስቴትስን በሱኒ እና በሺዓ መካከል ወዳለው የእርስ በርስ ቅራኔና መጓተት ሊያስገባት  ይችላል” ሲሉ በይፋ ጽፈው ነበር። ይሁንና ከሦስትና አራት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አሜሪካ፣ በፕሬዚዳንት ባይደን፣ የዐረብ ሀገራቱና እስራኤል፣ ወታደራዊ ቅንጅት የሚፈጥሩበትን መስክ በማመቻቸት ላይ ትገኛለች፡፡  ጥረቱንና እንቅስቃሴውን ለየት ያለ ነው ለማለትም፣ የዐረብ ሀገራቱንና እስራኤልን የጨመረው ወታደራዊ ቅንጅት እንቅስቃሴ - ሴንትኮም (CENTCOM) በሚለው  ስር እንደሚመራ  እየተነገረ ነው፡፡ ለዐረቡ ሀገራትና ለእስራኤል ግንኙነት የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ወሳኝ ሚና መጫወቱን መካድ አይቻልም፡፡ በእርሳቸው ዘመነ ስልጣንም ነው ሳውዲት ዐረቢያና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች ከእስራኤል ጋር ወዳጅነትን በይፋ የተያያዙት። አሁን ወታደራዊው ቅንጅትና ጥምረት ወደ ተግባር የሚለወጡበት ኹነቶች እየተስተዋሉ ናቸው። በዚህ ዓመት የእስራኤል  የባህር ሀይል ዘርፎችንና የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን ታደራዊ ልምምዶች፣ የባህረ ሰላጤው ዐረብ ሹማምንትን ጨምሮ ከቀይ ባህር  ላይ ሆነው ጎብኝተዋል፡፡ እስራኤልን ያከለው የዐረብ ሀገራቱ ወታደራዊ የአየር ላይ የመከላከያ ትብብር፣ በአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር፤ “ኢራንን ለመቋቋም እንደዋነኛ ምዕራፍ እንደሚቆጠር” በይፋ ነው የተገለጸው፡፡ ይህ ወታደራዊ ትብብር፣ አሜሪካ ተፅዕኖዋን ከማሳረፍ በላይ በየአህጉራቱ፣ ወዳጅ በምትላቸው ሀገራት ዙሪያ ወታደሮቿን አሰልፋ - የጦር ጣቢያዎችን ቀልሳ ለማከናወን የምታፈሰውን ሀብትና የሰው ሀይል ውስን እንዲሆንላት ያደርጋል፡፡ የዩኤስ ትኩረትም በየሪጅኑ ባላት የወታደራዊ ቃል ኪዳን ራሱ የሀገራቱን ወታደራዊ አቋም በማጠናከር ማሰለፍ ለሩስያና ቻይና ተጽዕኖ መከላከያም ሆኖ እንደሚያገለግል ታሳቢ ያደርጋል፡፡
ባልተጠበቀ ሁኔታና በተለወጡትም አዳዲስ ምክንያቶች  የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የፕሬዚዳንት ትራምፕን አቅጣጫ በመከተል ያንኑ ፖሊሲ ነው የገፉበት፡፡ የተለወጡት አዳዲስ ምክንያቶች የምንላቸው ደግሞ - ኢራን የኒውክሌር ባለቤት ለመሆን ያላት ርቀት እያነሰ መምጣቱ፣ ብዙዎች የዐረብ ሀገራት ከእስራኤል ጋር ያላቸው የሻከረ ግንኙነት መለሳለሱና ለእስራኤልም እውቅና (ቢያንስ 5 የዐረብ ሀገራት) መስጠታቸውና በአውሮፓ ያልተጠበቀው ጦርነት መከሰት ናቸው፡፡ የሩስያ በዩክሬይን ግጭትና በዩኤስ አሜሪካ መሪነት የተወሰደው አቋም የፈጠራቸው ግፊቶች በዐረቡ አለም ወጥ ምላሽ ያለማግኘቱና ከቶውንም የማንገራገር ስሜቶች መታየታቸው በምዕራቡ ዓለም አለመረጋጋትን ፈጥሯል፡፡ በተለይም አዲሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በሳውዲት ዐረቢያ አልጋ ወራሽ ላይ ከመመረጣቸው በፊትም ሆነ በሁዋላ ያላቸው ተቃውሞ ለግንኙነቱ መሻከር ምክንያት ተደርጎ የሚቆጠር ነው። በሳውዲት ዐረቢያ መሪነት በየመን ላይ የሚፈጸመው የጦር ድብደባ በአሜሪካ ተወካዮች ዘንድ የተቃውሞ ስሜትንም መቀስቀሱ መረሳት የለበትም፡፡ የዚህ አዲሱ የዐረብ ሀገራቱ የጦር ቃል ኪዳን (ዐረብ - ኔቶ) ምስረታ ሀሳብ በዚህ ዙሪያ የነበሩትንና ያሉትን ልዩነቶችን የሚያጠብ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡
በአዲሱ ወታደራዊ የቃል ኪዳን ሳውዲት ዐረቢያ፣ የተባበሩት የዐረብ ኢሚሬቶች፣ ኳታር፣ ኩዌት፣ ባህሪን፣ ኦማን፣ ግብፅ፣ ዮርዳኖስ፣ ሱዳን፣ ሞሮኮና አይሁዳዊቷ እስራኤልን የሚያካትት እንደሚሆን ነው፡፡ በእስራኤል በኩል ይህን ትብብር ለመቀላቀል አዎንታዊ ምላሽ እንዳላት በመከላከያ ሚንስትሯ አማካይነት ይፋ አድርጋለች፡፡ ወታደራዊና መረጃን ያካተተው ትብብር በዐረቡ ዓለም በተለይም እስራኤልን ማካተቱ፣ በአቋሙና በቁመናው ላይ መሰረታዊ የሆነ ለውጥን እንደሚያስከትል ነው ብዙዎች የሚስማሙበት፡፡ እስራኤል በወታደራዊ አቅሟና በጦር መሳሪያ ይዞታዋ ለዚህ ትብብር ያላት አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ ነው። የዚህ ትብብር ዋነኛ ማነጣጠሪያ የሆነውን የኢራንን ወታደራዊ ይዞታ ለመቋቋምም ሆነ ለመመከት የእስራኤል መገኘት ታላቅ ሚና ይጫወታል። በወታደራዊ ሀይል ብዛትና አደረጃጀት በዐረቡ ዓለም የግብፅ በአቢይነት ቢጠቀስም፣ ማንኛቸውም በተናጥል ኢራንን ለመቋቋም የሚያስችል ቁመና እንደሌላቸው ግልጽ ነው፡፡
በዚህ የዐረቡ ትብብር ውስጥ ከእስራኤል መካተት ጋር ተያይዞ እውቅና ያልሰጡ ኩዌት፣ዮርዳኖስና ኦማንን የመሳሰሉት ሀገራት አብረው ለመቀናጀት መቻላቸው ለእስራኤል አይነተኛ ድል ነው፡፡ ከዚህም በላይ እስራኤልን እንቅልፍ የምትነሳት የኢራንን አደጋ ለመግታት የሚያስችላትን ቁመናም ታገኝበታለች። አሜሪካም ይህን ቅንጅት በምዕራብ እስያ ለማዋቀር ለረዥም ጊዜ የወጠነችው፣ በሰላጤ ሀገራት ዙሪያም ለስትራቴጂያዊ ሚዛን የበላይነቷን የሚጠብቅላት ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ በተቃራኒው ከዓለም አቀፉ ግንኙነት ተገልዬ አልኖርም የምትለዋ ሩስያ ፕሬዚዳንት፣ ከኢራን ጋር የግንባር ግንኙነት ለማድረግ እንደወጠኑ ከሰሞኑ  የተሰራጨ መረጃ ያመለክታል፡፡
ይህን የፖሊሲ አቅጣጫና አካሄድ በጥሞና ለተመለከተው የአፍሪቃን በተለይም የአፍሪቃ ቀንድን ሁኔታም ከስሌቱ ውስጥ ማስገባት ይኖርበት ይሆናል፡፡ አቢይ የስትራቴጂያዊ ማጠንጠኚያ የሆነችው የአፍሪቃ ቀንድ - የዐረቡ ሀገራት ተፅዕኗቸውን በማሳደር በኩል ያለውን ሩጫም ማጤን ይገባል፡፡ በዚህ የገበጣ ጨዋታ በሚመስለው የጂኦ ፖለቲካ ስሌት የሀገራችን ቦታ እንዲሁም  ስጋትና ፋይዳውን በቅጡም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡   

Read 2974 times