Saturday, 06 August 2022 11:59

አምስት እና አምስት...ስምንት!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


               እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“እሺ ተወዳዳሪዎቻችን፣ ቀጥለን የእለቱን ከባድ የሚባል ጥያቄ እናቀርባለን፡፡ እንደውም እስከዛሬ ከተጠየቁት ጥያቄዎች ሁሉ ከባዱ ነው ማለት ይቻላል፤ ይህን ጥያቄ የመለሰ ተወዳዳሪ የሚያገኘው አንድ ሳይሆን አስር ነጥብ ነው፡፡ ተዘጋጅታችኋል?”
አዎ፣ ተዘጋጅተዋል፡፡ እነሱ ግራ ተጋብተው ጭጭ ሲሉ እኛ እንመልስላቸው እንጂ! ዘንድሮ እኮ ጠያቂው ሌላ መላሹ ሌላ ሆኖ ነው ግራ የገባን፡፡ ጥያቄው የቀረበለት ገና ምን መልስ እንደሚሰጥ እያሳለሰለ ሳለ ያልተጠየቀው ዘሎ ጥልቅ! የዘሎ ጥልቅ ስልጣኔ! አለ አይደል...ልክ ለምሳሌ እንበልና እሱ ከሚስ እንትናዬ ጋር የሆነ ቦታ ምሳ ላይ ነው፡፡ የሆነ አሰላፊ ይመጣና “ምግቡ ተመችቷችኋል?” ሲል ይጠይቃል። ይሄኔ እሱዬው “አዎ ተመችቶናል፣” ይላል። እሷ መች ተመቸኝ አለች? እስዋ እኮ ከዚህ በፊት ከነበሩት እንትናዎቿ የዚህ አይነት የምግብ ‘አቢዩዝ’ ያደረሳባት ይኖር እንደሁ ለማስታወስ የአእምሮ መዝገብ እያገላበጠች ነው፡፡ ገና ለገና ከፋይ እሱ ነውና ማን ‘ሱፕሪም ኮርት’ ምናምን አደረገው? ለነገሩ በአምስተኛ ወሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጋብዝ  አንድ በየአይነቱ ለሁለት ከሚያዝ ሰው ምን ይጠበቃል! ቂ...ቂ...ቂ...እናላችሁ፣ ወደ ጥያቄና መልስ ውድድሩ...
“እሺ ተወዳዳሪ አንድ፤ ጥያቄውን በሚገባ አዳምጠኝ፡፡ አምስትና አምስት ሲደመር ስንት ነው?” ወላ ተወዳደሪ የለ፣ ወላ ካሜራማን የለ፣ ወላ ቤቱ ዘና ብሎ ቲቪ ሲመለከት ድንገት ጥያቄውን ሲሰማ ጭው ያላለበት የለም...ምን አለፋችሁ፣ ሁሉም ጦጣ ይሆናል፡፡
“ይቅርታ፣ ጥያቄው ይደገምልኝ፡፡”
“አምስትና አምስት ሲደመር ስንት ነው?”
ተወዳዳሪ ሆዬ አስር ነጥብ ሲሰጠው አሸናፊ መሆኑ እየታየው...“አስር፣” ይላል፡፡ አዳራሹ ደግሞ ጭብጨባ በጭብጨባ ይሆናል፡፡ ህዝቤ ያጨበጨው ተወዳዳሪው በትክክል መልሷል ብሎ አድናቆቱን ለመግለጽ ሳይሆን ጠያቂው ላይ ‘ሙድ ሲይዝበት’ ነው፡፡ ጠያቂው የምጸት ፈገግ ነገር ብልጭ ትልበታለች...ምናልባት ለእሱ ያጨበጨቡለት መስሎትም ይሆናል። ልክ ነዋ...ለእኛ ያጨበጨቡልን እየመሰለን ስንቶቻችን በህልም ዓለም ውስጥ እንዳለን አንድዬ ይወቀው፡፡ እነእንትና ኸረ ነቃ፣ ነቃ! ጭብጨባው ለእናንተ አይደለም፡፡ ጨብ ጨብ ያደረግነው ሆዳችን ውስጥ የሚገለባበጠው ነገር ስለባዛብን ነው፡፡ እናማ... ጭብጫቧችን “ወቸ ጉድ!” ምናምን ለማለት ነው እንጂ፣ ምን ይሁን ብለን ነው ለእናንተ የምናጨበጭበው!
ጠያቂ...
“ጥያቄው በትክክል... አልተመለሰም፡፡ ተወዳዳሪ አንድ ለዛሬ አልተሳካልህም፡፡”
እኔ የምለው በቃ “ጥያቄው አልተመለሰም፣” ማለቱ ይበቃ የለ አንዴ! “አልተሳካልህም፣” ምናምን እያሉ የምን ትርፍ ምናምን መለጠፍ ነው!  የምን ‘በቡሃ ላይ ቆረቆር ነው!
አምስትና አምስት...ስምንት!
“እሺ ተወዳዳሪ ሁለት፤ አሁን የአንተ ተራ ነው፡፡ አስታውስ አስር ነጥብ ነው ያለው። እሺ...አምስትና አምስት ስንት ነው?” ይህኛው ተወዳዳሪ ይችን ታክል ሳያመነታ ነው የሚመልሰው፡፡
“አስራ አምስት፡፡” አሥር፣ አስራ አምስት ሰዎች ሌሎቹን ለመቅደምም ሊሆን ይችላል፣ ፈጥነው ጨብ፣ ጨብ ያደርጋሉ፡፡ ሌሎቹ ግን “አይ፣ አሁንስ በዛ! ጭራሽ አራስ ልጅ ይመስል ይጫወቱብናል እንዴ!” በማለት አይነት ጭጭ ብለዋል፡፡ ስሙኛማ.. .አንዳንዴ ምን አለ መሰላችሁ... ምንም አይነት ጭብጨባ በማያስፈልግበት ሰዓት ጭብጫቦውን የሚያቀልጡትን የሆኑ በጭብጫቦ እኛን ‘ክሬዚ‘ የማድረግ ስትራቴጂ ላይ የሚሠሩ አክቲቪስቶች በሏቸውማ!
“እሺ፣ አሁን ወደ መጨረሻ ተወዳዳሪያችን እናልፋለን፡፡ ተወዳደሪ ሦስት... አምስትና አምስት ስንት ነው?” ይህኛው አንገቱን ቀና፣ ደረቱን ነፋ አድርጎ፣ በ‘ኮንፊደንስ’ ነው የሚናገረው፡፡ እኔ ያለው...በሽልማቱ ጉዳይ አስቀድሞ ተደራድሯል እንዴ! ምን ላድርግ...ዘንድሮ በራሱ ‘ኮንፊደንስ’ የሚያሳይ ሰው እኮ “በችሎታው ተማምኖ ነው፤”  “እንደሚያሳካው እርግጠኛ ስለሆነ ነው፤” ከማለት ይልቅ “እባክህ እሱ ጉዳዩን አስቀድሞ ጨርሶት ነው እንዲህ ዘና ያለው፣” ማለቱ ስለሚቀናን ነው፡፡
“እሺ ተወዳዳሪ ሦስት፣ እየጠበቅንህ ነው...”
“ስምንትም ሊሆን ይችላል፣ ሦስትም ሊሆን ይላል፡፡” አዳራሹ ያጉረመርማል፡፡ አንዳንዱም “በቃ፣ ከመጀመሪያው መላሽ በስተቀር አወዳዳሪውን ጨምሮ ሌሎቹ ጭንቅሌያቸው ፉዞ ሆኗል!” ብሎ ይደመድማል፡፡ “ማንምም ከመንገድ እየሰበሰበሱ እንዲህ መጫወቻ ያድርጉን!” እያለ በጥያቄና መልስ ውድድር አስመስሎ ይቦተልካል፡፡
አምስትና አምስት...ስምንት!
“እሺ ተወዳዳሪ ሦስት፣ ሙከራህ ለየት ያለ ስለሆነ ደስ ይላል፡፡” ደስ ይላል! ሰውየው ‘ደስ ይላል፣’ ነው እንዴ ያለው? ባቡሩ ከፉርጎው ተፈናጥሮ ሲወጣ ጥጋጥግ መፈለግ ነው እንጂ ምኑ ደስ ይላል! ደግሞም ለጣቢያውም ሰበብ እንዳይሆንበት ቶሎ ብሎ ወደ ሀኪም መውሰድ ነው እንጂ ‘ደስ ይላል’ ይለዋል! ወይ ሀኪም ቤት መውሰድ፤ ፈረንካው ከሌለ ብርጉድ ምናምን እጠኑት! አይ... ነገርዬው የሆነ የማስታገስ ነገር አለው ስለሚባል ነው፡፡
ጠያቂው...
“ግን ለተመልካቾችም ግልጽ ለማድረግ እንደዛ ማለት ምን ማለትህ እንደሆነ እስቲ አስረዳ፡፡”
“እኔ ጥያቄውን የቁጥርና ሂሳብ ጥያቄ ብቻ አድርጌ አላየውም፡፡ ሰፋ አድርጌ መመርመር ነው የምፈልገው፡፡” (ሰውዬ፣ ያልተከፈለበት ስቴክ ለመንጨት ብቻ ተብሎ እንደሚዘጋጅ ወርክሾፕ አታድርገው! አንተ በቀለበት መነገድ ተሽከርክረህ እስከምትመለስ እኛ ተጎልተን መጠበቅ አለብን እንዴ!) “በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ባይባልም አብዛኛው ነገር ሊሆን በሚገባባት ወይንም ይሆናል ተብሎ በማይጠበቅበት ቦታ ስለሆነ የአምስትና አምስት ድምር እንደ ሁኔታው ተለዋዋጭ ነው፡፡ ግን ደግሞ በምንም አይነት አስርና ከአስር በላይ አይሆንም፡፡” ዘና፣ ፈገግ ብሎ ብሎ ወደ ተመልካቹ ይመለከታል። ተመልካቹም ግራ ግብት ብሎት ወደ እሱ ይመለከታል፡፡
“ተወዳዳሪ ሦስት፣ አንዲት ነገር...እንደው ምናልባት ይበልጡን ግልጽ ለማድረግ ከረዳ  መልሱን በሆነ ቁጥር ክልል ውስጥ አስቀምጠው ብትባል መልስህ ምን ይሆናል?”  
“ከዜሮ እስከ ዘጠኝ ባለው ውስጥ፡፡”
ህዝቤ ሁሉ ጠያቂው፣ የጭንቄው ጤንነት መለስ ብሎለት ከአሁን አሁን አሾፈበት፣ “ለመሆኑ ይህን እውቀት ያገኘኸው ከሀርቫርድ ነው ኦክስፎርድ!” ብሎ በዘመኑ አነጋገር ‘ሙድ ሊይዝበት ነው፣’ ብሎ ሲጠብቅ አወዳዳሪው ምን ቢል ጥሩ ነው...
“በትክክል ተመልሷል፡፡”
በቃ፣ ምን አለፋችሁ የእኛ ሰው በአዳራሽ ውስጥ ወይም ሰው በርከት ባለበት ቦታ ሲበሳጭ  ግፋ ቢል ማጉረምረም ወይንም በሆዱ መራገም እንጂ እንደጠገቡት አንቁላል ወርዋሪ ቢሆን ኖሮ ወላ ጠያቂ፣ ወላ ተወዳዳሪ ቁጥር ሦስት፣ ፊታቸው አስኳል በአስኳል በሆነ ነበር። የፈረንጅ ጋዜጦችም...ያጯጩሁታል፡፡ “ሰበር ዜና...በአፍሪካ ቀንድ በምትገኘው ሀገር ህዝቡ እንቁላል ተመግቦ የተረፈውን የሚያስቀምጥበት ቦታ በማጣቱ እርስ በእርስ እየተወራወረበት እንደሆነ ከታማኝ ምንጮች አረጋግጠናል” ብለው በጻፉብን ነበር፡፡
አምስትና አምስት...ስምንት!
እናላችሁ...ብዙ ነገሮች ላይ አምስትና አምስት አስር መሆኑ እየቀረ፣ መልሱ ባለ አንድ አሀዝ ብቻ እየሆነ ነው፡፡
“ስማ እንዴት ነው የሀገር ነገር..?”
“ሀገር ነው ያልከኝ! ምን ሀገር አለና ነው!” ይላችኋል፡፡ አሀ...በፊት እኮ የፈለገው አይነት የክፉ ክፉ ነገር ይከሰት ከዚህም፣ ከዚያም እያጣቀሰ ሲያስረዳችሁ ምን አለፋችሁ... የምን እከሌ፣ የምን ዩቫል ሀሪሪ ነው፡፡ (ስሙኝማ... የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ...ያ አንድ ሰሞን እንደመሻማት እያልን የገዛነውን ‘ሳፒየንስ’ የሚለውን መጽሐፍ ሙሉውን ይቅርና የመጀመሪያዎቹን ሀያ አምስት ገጾች ያነበበ እጁን ያውጣ! አሀ..እጅ ያላወጣው እኮ በቦታው የሌለ ብቻ ነው፡፡ መቼም እኮ ዘንድሮማ ማስመሰሉንና መመሳሰሉን ስንችልበት!) እናላችሁ...አምስትና አምስት... ስምንት ሲሆን መጨረሻው እኮ ይኸው ነው፡፡
ታዲያላችሁ.... ለአምስትና አምስት ምላሹ አስር መሆኑ ቀርቶ ስምንት ይቀርበዋል ለማለት ያህል ነው፡፡
አምስትና አምስት...ስምንት!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1804 times