Saturday, 06 August 2022 11:41

“ሳያስቡ የጀመሩት ቀረርቶ ለመመለስ ያስቸግራል”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ደራሲ ከበደ ሚካኤል “ታሪክና ምሳሌ” በሚል መጽሐፋቸው ስለ አውራ ዶሮ፣ ድመትና የአይጥ ግልገል ሲተርኩ የሚከተለውን ይሉናል፡-
  ከሰፈሯ ውጪ የትም ሔዳ የማታውቅ አንዲት የአይጥ ግልግል ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን  እናቷ ሳታውቅባት ለዙረት ወጣች። ስትመለስም ለእናቷ ይህን ነገረቻት፡-  “አንድ ያየሁት እንስሳ የዋህ ነው፤ አይኖቹ ያምራሉ፤ ረጅም የከንፈር ፂም አለው፤ ገላው ለስላሳ ነው፤ ድምጹ ደርባባና-የተዋበ ስለሆነ- ላጫውተው ጠጋ አልኩኝ፡፡ ሌላኛውና ቀዥቃዣው ፍጡር ግን የቀይ ስጋ ቁንጮ ራሱ ላይ ያለው ነው፤ ሲራመድ ጎብላላ ነው - ያስፈራል፤ በዚያ አሸባሪ ድምፁ ጮኸ፤ ከጉያውም ሁለቱን እጆቹን አወጣና ዘረጋ፤ አንድ ጊዜ እንደ ቁርበት  አራግፎ  ሲያጓራብኝ ምን ይዋጠኝ፤ የት ልግባ፡፡ ያንን መልከ መልካሙን ግን በወጉ እንኳን ሳልተዋወቀው ቀረሁ፤ ስለዚህ ፈጥኜ ወደ ቤቴ መጣሁ እልሻለሁ፡፡” አለቻት፡፡
እዛ ምን ወሰደሽ አንቺ ክልብልብ
አይጦች ስትባሉ የላችሁም ቀልብ
አይጥ ሞቷን ስትሻ ስታበዛ ሩጫ
ሄዳ ታሸታለች የድመት አፍንጫ
ሲባል የነበረው እስከነ ተረቱ
ባንቺ ሳይ ደረሰ በክልፍልፊቱ፡፡
ያ መልከመልካም ፊቱ የሚታይ
ድመት የሚባለው አውሬ አይደለም ወይ
መልኩ ቅልስልስ ነው ያ ክፉ አታላይ
ዋ የሰራው ስራ እሱ በኛ ላይ
ባታውቂው ነው እንጂ ጥንቱንም ሲፈጠር
አጥፊያችን እሱ ነው የትውልዳችን ጠር
እልቅስ ቀብራራው የደነገጥሽለት
 እኛን የሚጎዳ ክፋትም የለበት
ስሙም አውራ ዶሮ
እንደውም አንዳንዴ ሰው ሊበላ ሲያርደው
ለእኛም አንዳንድ ጊዜ ያገለግለናል
አጥንትና ስጋው ሲጣል ይተርፈናል፡፡
 ብላ እናቲቱ እየዘረዘረች ሁሉን አስረድታ
ለልጇ መከረች፡፡
---------
ሰው ጠባዩ ታውቆ ፊት ሳይመረመር
መልኩን አይቶ ብቻ ይረባል አይረባም
 ክፉ ነው  ደግ ነው ማለት አይገባም፡፡
***
የአውራ ዶሮ የድመትና አይጥ ግልገል ታሪክ፣ ከልጅነት እስከ እውቀት ስናነበው ስንተርከውና ስንጽፈው፤ ሲወርድ ሲዋረድ  የመጣ ተረት ነው። ትምህርትነቱ ግን ምንጊዜም ለማህበረሰባችን ጠቃሚ ስለሆነ ይኸው ስንጠቅሰው እንኖራለን። ፋይዳው የሚመነጨው ዛሬም መልከ መልካም ጢማም --- የሚያምሩ፣ ገላቸው ልስልስ፣ ብዙ ጅራታም ሰዎች ስላሉ ነው። የልባቸውን ሳናውቅ በአንደበታቸው  እየተማረክን  እንታዘዛለን፡፡ የከረባታቸው ማማር ይገዛናል። ተክለ ሰውነታቸው ያማልለናል። አንዳንዴም የአብዮታዊ እንቅስቃሴ ፍልሚያ ብዙ ነገሮችን እንድናስተውል ጊዜ ስለማይሰጠን ካለፈ በኋላ ለቁጭትና ለፀፀት  ይዳርገናል፡፡
በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት እንቅስቃሴዎች ሁሉ ለቁጭትና ፀፀት ምንግዜም ሰፊ ቦታ አላቸው። ችግሩ የቁጭቶቹና ፀፀቶቹ አይነትና መጠን በጣም በርካታ በመሆኑ ለመያዝ ለመጨበጥ  አለመቻሉ ነው። አይያዝ አይጨበጤነታቸው የሚመጣው ደግሞ አንዱን ፈር ሳናሲዝ  ሌላው ወዲያው ወዲያው ስለሚከታተልብን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በየጊዜው ዝግጁ የሆነ አእምሮ ያስፈልጋል። አለበለዚያ እንደ 1966 አብዮት - ቤት ለቃቂው እቃውን ሳያወጣ፣ ገቢው እቃውን አምጥቶ ሳያስገባ  ፍጥጫ ይከፈታል፡፡
 በተደጋጋሚ በሀገራችን  ያጋጠመን  ነገር፣ በቶሎ የመፎከር - በቶሎ ለሬዲዮ ዲስኩር የመጣደፍ   አባዜ ነው፡፡ ለህዝባችን የምንሰጠውን መረጃ ብንሳሳት -- ስነ አዕምሯዊ መዛባት ሊያስከትል እንደሚችል አለማሰብ እጅግ  ጎጂ ነው፡፡  “ሳያስቡት የጀመሩት ቀረርቶ  ለመመለስ ያስቸግራል” ለሚለው ተረት ያጋልጠናል፡፡  እንጠንቀቅ!!

Read 13747 times