Saturday, 30 July 2022 14:48

“ቴራኒያ ኮ ኮይሳኒ” የሙርሲ ቴአትር፣ ነገ በብሔራዊ ቴአትር ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 በእንግሊዙ  ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ለንደን ስኩል ኦፍ ኦሪዬንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ እና  በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ትብብር የተሰራው “ቴራኒያ ኮ ኮይሳኒ” (ዳኛው) የተሰኘ የሙርሲ ቴአትር፣ ነገ   በብሔራዊ ቴአትር ይመረቃል፡፡ ቴአትሩ ባለፈው ሳምንት እሁድ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መመረቁ ይታወቃል፡፡  
ቴአትሩ ባለሙያ ባልሆኑ የሙርሲ ተወላጆች፣ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በሙርሲኛ ቋንቋ የተሰራ ነው ተብሏል፡፡
 “ቴራኒያ ኮ ኮይሳኒ”፤  ሙርሲዎች “እኛ እንዲህ ነን” ብለው በቋንቋቸውና በራሳቸው ትወና ማንነታቸውን የሚገልፁበት ቴአትር  ሲሆን ከዚህ ቀደም ስለ ቴአትርም ሆነ ስለ ትወና ሰምተውም ሆነ አይተው የማያውቁ ሰባት የሙርሲ ወጣቶችና ሁለት ሌሎች ተዋንያን የሚተውኑት  የሙሉ ሰዓት ቴአትር መሆኑን የደቡብ ኦሞ ቴአትር ኩባንያ መሥራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስተዋይ መለሰ ተናግረዋል።
  ቴአትሩ ሃምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም ለሙርሲ ማህበረሰብ ፣ለዞኑ ባህልና ቱሪዝም ሃላፊዎችና  ለአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች ቀርቦ ከታየና ከተገመገመ በኋላ ይሁንታን በማግኘቱ  ባለፈው ሳምንት እሁድ  በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ፣ የተመረቀ ሲሆን በነገው ዕለት ደግሞ  የፓርላማ አባላት፣  የህግ ባለሙያዎች፣ አንጋፋ  የቴአትር ባለሙያዎችና ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በሚገኙበት በብሔራዊ ቴአትር እንደሚመረቅ አቶ አስተዋይ ጨምረው ገልፀዋል።
 ቴአትሩ በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚገባ ቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ተደግፎ፣  በፊልም መልክ በአማርኛ እየተተረጎመ እንደሚታይም ታውቋል።
  ቴአትሩ ዓለምአቀፍ ጉዞ የሚያደርግ ሲሆን በእንግሊዝም “ሼክስፒር ግሎብ”በሚባል ቦታ ለእይታ ይቀርባል ተብሏል።

Read 11131 times