Saturday, 30 July 2022 13:34

ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም ዳግም እንዲፈትሹ ያስገደደው የሰርጌይ ላቭሮቭ ጉብኝት

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

   - የአውሮፓ አገራት ህብረቱ ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ እያቀረቡ ነው
     - በኢትዮጵያና በምዕራባውያን መካከል እያሽቆለቆለ የመጣውን ግንኙነት ሩሲያ ትጠቀምበታለች የሚል ስጋት ተፈጥሯል
      - ሁለተኛው የሩሲያ- አፍሪካ ጉባኤ በመጪው ዓመት አዲስ አበባ ላይ ይካሄዳል
                   
           የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ  ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት የአፍሪካ አገራት ያደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት፣ ምዕራባውያን በአፍሪካ  በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም ዳግም እንዲፈትሹ ያስገደደ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የሰሜኑ ጦርነትን ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችንና ጫናዎችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን አሜሪካም  ከጦርነቱ ጋ ተያይዞ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ተጥሰዋል በሚል ለውጭ ንግድ ከፍተኛ ዕድል ይፈጥራል ከሚባለው አጎዋ ኢትዮጵያን ማገዷ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ መንግስት  ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ምዕራባውያን አገራት ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ጉዳዩ ወደ  የተባበሩት መንግስታት  ምክር ቤት እንዲመጣና ድምጽ እንዲሰጥበት ሲደረግም፣ ሩሲያና ቻይና በም/ቤቱ ያላቸውን ድምጽ ተጠቅመው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ወግነዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎች እንዲደረጉ፣አለም አቀፍ የእርዳታና ብድር ተቋማት ለኢትዮጵያ ድጋፍና እርዳታ ከመስጠት እንዲታቀቡ ተደጋጋሚ ጉትጎታና ጫና ሲያደርጉ ነው የከረሙት።
ማዕቀቡና ጫናው የምዕራቡን ፍላጎትና ዓላማ ባያሳካም፣ ኢትዮጵያን ግን አልጎዳትም ማለት አይቻልም። ሌሎች ኢትዮጵያን የሚያሽመደምዱ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችና እገዳዎች በተለይ በአሜሪካ መንግስት መዘጋጀታቸውም ይታወቃል- ተግባራዊ ባይሆኑም። ሩሲያ ፊቷን ወደ አፍሪካ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ማድረጓ ግን ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም እንዲፈትሹ አስገድዷቸዋል ይላል - የአሜሪካው ታዋቂ ጋዜጣ “ፖለቲኮ” ዘገባ።
የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት የአፍሪካ አገራ ሰሞኑን ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቀዋል። በኢትዮጵያ ባደረጉት የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ አለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያለባትን የአንድ መቶ  ስልሳ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ብድር ዕዳም መሰረዙን አስታውቀዋል።
የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላብሮቭ በኢትዮጵያ ባደረጉት የሁለት ቀናት ቆይታም፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው መክረዋል፡፡ በዚሁ ቆይታቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ  የጉብኝታቸው ዓላማ አገራቸው ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደሆነ አመልክተው፤ በኢትዮጵያና በሩሲያ  መካከል ያለው ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር እንዲሻሻል እንሰራለን ብለዋል፡፡ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር  ስለ ሩሲያና ኢትዮጵያ ግንኙነትና ቀጣይ የስራ ትብብር በስፋት የተወያዩት የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣  ኢትዮጵያ ያለባትን ችግር ሊፈታ የሚችልና አገሪቱን ለማረጋጋት የሚያስችል እንዲሁም ቁልፍ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚነጋገር ብሔራዊ ምክክር መጠራቱን በፅኑ እንደግፋለን ብለዋል፡፡ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ሩሲያ እንደምትደግፍም አስታውቀዋል፡፡
ይህ የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉብኝት ግን በምዕራባውያን አገራት ዘንድ ስጋት ያሳደረ ይመስላል። ጉብኝቱ ምዕራባውያኑ በቀጠናው ያላቸውን ተፅዕኖ ለመገዳደር ያለመ ነው በሚል አገራቱ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ  የያዙትን አቋም ዳግም እንዲፈትሹ አስገድዷቸዋል ተብሏል።
 የዓለም አቀፉ ክራይስስ ግሩፕ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ተንታኝ ዊልያም ዴስሊን፤ ሩሲያ በኢትዮጵያና በምዕራባውያን አገራት መካከል እያሽቆለቆለ የመጣውን ግንኙነት እግሯን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ትጠቀምበታለች የሚል ስጋት  መኖሩን ለ”ፖለቲኮ” ጋዜጣ ተናግሯል። ይህንን ስጋት ለማስወገድም ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን አቋም ለማስተካከል አንዳንድ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው፡፡ አንዳንድ የአውሮፓ አገራት አውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ እያደረጉ መሆኑም ተዘግቧል፡፡
የአሜሪካው የፖለቲካና ፖሊሲ ተንታኝ ጋዜጣ “ፖለቲኮ” እንደዘገበው ጣሊያን፣ ጀርመን፣ፈረንሳይና ኔዘርላንድ ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ የአውሮፓ አባል አገራት ህብረቱ ለኢትዮጵያ መንግስት ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጥ ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግም አውሮፓ ኮሚሽን በቅርቡ ለትምህርትና ጤና ፕሮጀክቶች የሚውል የ81.5 ሚሊዮን ዩሮ ሰብአዊ ድጋፍ መፍቀዱም ይታወቃል፡፡ በጦርነቱ ወቅት የተቋረጠው የ1 ቢሊዮን ዩሮ የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ በመጪዎቹ ዓመታት ሊለቀቅ እንደሚችል የህብረቱን ቃል አቀባይ ጠቅሶ የአመሪካው ታዋቂ ጋዜጣ “ፖለቲኮ” ዘግቧል፡፡

Read 19206 times Last modified on Saturday, 30 July 2022 15:20