Saturday, 30 July 2022 13:28

ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት… (አናት ይጠብቃል) ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት….(አንገት ይጠብቃል) አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ! - ከበደ ሚካኤል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

        ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ እስር ቤት ውስጥ በሚካሄድ አንድ የትግል ውድድር ላይ እጅግ ግዙፍና ለዐይን የከበደው መንዲስ የሚያክለው እስረኛ ተነስቶ፤
“ወንድ የሆነ ይምጣና ይግጠመኝ!” እያለ ይፎክራል።
ቀጥሎ የመጨረሻው ቀጫጫ ሰው ተነሳና፤  “እኔ እገጥምሃለሁ!” አለው።
ሰው ሁሉ ሳቀ። መቼም ጨዋታ ነው ተብሎ ይገመታል።
ግጥሚያው ተጀመረ። ግዙፉ ሰው በንቀት የቀጫጫውን ሰው አንገት በጣቱ ሊይዘው ይሞክራል። አንገቱን እንደማነቅ ብሎ። ቀጫጫው ሰው ግን ፍንክች አላለም!! አንዳንድ ለቋሳ የሚመስሉ ሰዎች እጅግ በርትተው ሲገኙ በጣም ይገርማሉ። ያስደነግጣሉም።
ግዙፉ ሰው፤ “አሃ እቺ ቀጫጫ የዋዛ አይደለችም!” ብሎ ያለ የሌለ ሃይሉን ሊጠቀም ቢሞክርም ፈጽሞ አልነቀነቅ አለችው። ቀጥሎ የሆነው ደግሞ ፈጽሞ  የማይታመን ነገር ነው። ትንሿ ሚጢጢ ሰው ጭራሽ በቀጫጫ እጇ ብብቱ ስር ገብታ በጠንካራ ጣቶቿ ስርንቅ አድርጋ ይዛ፤ ትንፋሽ አሳጠረችው። ያሁኑ ይባስ! እጅጉን ጨከነችበትና ያን አንዳች የሚያክል ግንዲላ ወለሉ ላይ አነጠፈችው።
ግንዲላው እልህ ይዞት ተነስቶ ዳግመኛ ካልገጠምኩ በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ አለ።
ዳግመኛ አንከባለለችው። የዕለቱ የትግል ፍጻሜ ሆነ።
አገር ሳቀ፡፡ ጉድ ተባለ! የሰውነት ግዝፈት ብቻውን የአቅም መለኪያ አይሆንም። በአገርም በመንግስትም፣ በአለቃም በምንዝርም ላይ ሲከሰት የምናየው ነው።
***
አንዳንዴ ከጉልበት ይልቅ ጥበብና ብልሃት ያለው ሰው ሊያሸንፈን እንደሚችል እንመን። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ጊዜ እንግዛ እንጂ “ዘራፍ! አጉራኝ ጠራኝ”  ማለት ሁልጊዜ አያዋጣም!
እንዲያው በነገረ -ቀደም ሬዲዮውና ቴሌቪዥኑ በጄ በደጄ ነው ብለን ብዙ ባወራን ቁጥር  ብዙ ልንሳሳት እችላለን። ብዙ ቀዳዳም እንፈጥራለን። አመራር ላይ ባለን ሰዓት በክፉ ጊዜ ከምንፈጥረው ስህተት ይልቅ በደጉ ጊዜ የምንፈጥረው ይብሳል- ብዙ የመዘናጋት ዕድል አለና!
ሁልጊዜ ትልቅ ስንሆን ትንሿ ድንቢጥ ወፍ ለተራራው ያለችውን አንርሳ። If I am not big as you are not are you as small as I am (እኔ ያንተን ያህል ትልቅ  ባልሆንም አንተም የእኔን ያህል ትንሽ እንዳልሆንክ ልብ በል፣ እንደ ማለት ነው)
በመንግስትና በተቃዋሚ ሃይሎች መካከል በሚካሄደው ጦርነት ይህ እውነት ደጋግሞ ተከስቷል። እንዲያውም ስብሐት ገ/እግዚያብሄር ገና ኢህአዴግ ስልጣን ሳይይዝ በጻፈው ጽሁፍ፤ “አገርን በሴት መመሰል የተለመደ ነው። የአገሪቱ መሪ ባል ነው ብንል አማጺው ሽፍታ ደግሞ ውሽማ ይሆናል። ሽፍታው መሪውን ጥሎ መንግስት የመሆን እድል ከገጠመው፣ ውሽማ  ባል ሆነ ማለት ነው”  ብሎ ነበር። በነሐሴ 1984 የካቲት መጽሔት ላይ “ሽፍቶችና መሪዎች” በሚል ርዕስ እንደሚከተለው አስነብቦናል፡-
“መሪዎቹ ወይ በድንቁርና ወይም በራስ ወዳድነት ወይም በሌላ ምክንያት የተነሳ ወደ ነጂዎች ሲለወጡ፣ ህዝቡ መነዳት ስለሚከፋው ከውስጡ ከአንጀቱ ሽፍቶችን ያፈልቃል። እነዚህ ሽፍቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ በግልጽም ሆነ በስውር ከሕዝቡ ሙሉ ድጋፍ ያገኛሉ። ሕዝቡ “አቀፋቸው” ይባላል። ስለዚህም ሰነባብተው- ሰውተውና ተሰውተው ያሸንፋሉ። ሽፍቶቹ ነጂዎቹን ያስወግዳሉ። እፎይ ግልግል!... ከዚያስ?...
ከዚያማ ሽፍቶች የነበሩት መሪዎች ይሆናሉ- እነሱም ሰነባብተው በየምክንያታቸው ወደ ነጂዎች እስኪለወጡ ድረስ።  በራሺያ ሰፊ አገር እነ ሌኒን- እነ ትሮትስኪ ድንቅ ሽፍቶች ነበሩ። የዓለም አንድ ስድስተኛ ሕዝብ በሚኖርባት በቻይና አገር የተነሱት እነ ማኦ -እና ጁ..ኤን ላይ ተወዳጅ ሽፍቶች ነበሩ። በቪዬትናም እነ ሆ ቺ-ሚን የሚያስገርሙ ሽፍቶች ነበሩ። በኩባ እነ ፊደል ካስትሮና  ቼ-ጉቬራ ታይተው ተሰምተው የማይታወቁ ዓለምን የነሸጡ ሽፍቶች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ቆንጅዬ ሽፍቶች የህዝቡን ብሶት ይዘው ስለተነሱ ድል አደረጉ። በሽፍትነታቸው ዘመን “ተአምር ነው” ወይም “ምትሀት ነው” የሚያሰኝ ብዙ ጀብዱ ፈጸሙ። የሽፍትነታቸው ዘመን ሲተረት ሲተረክና ሲጻፍ ገድል ይመስላል። ገድል ነው፡፡ ደግሞ-ምድራዊ ሆነ እንጂ።
እንደተለመደው  አገርን በሴት ብንመስላት፣ ሽፍቶች የነበሩት ተለውጠው መሪዎች ሲሆኑ “ውሽማ የነበረው ሰውዬ ባል ሆነ” እንደማለት ነው። ሰውየው ያው ሆኖም በውሽምነቱ ሌላ፣ በባልነቱ ሌላ፡፡ ኧረ የትና የት!
ባጠቃላይ እንደው በጭፍን ያህል ስንናገር፣ በአንድ ልብ በአንድ ወኔ፣ ለአንድ ዓላማ ሲዋጉ የነበሩት ሽፍቶች፣ መሪዎች በሆኑ በማግስቱ ዓላማቸውም ልባቸውም መለያየት የጀመሩት ልዩነቶቻቸው እየበዙ እየከረሩ ሲሄዱ፣ ጠላትነት እየተንፏቀቀ መሃላቸው ይገባል። በራሽያ ስታሊን ትሮትስኪን ከአገር ያባርረዋል፡ ሽፍቶች የነበሩት የትሮትስኪ ወገኖች፣ ሽፍቶች በነበሩት በስታሊን  ወገኖች ይጨፈጨፋሉ።
በቻይና ሽፍታ የነበረው ሊዮ-ሻዎ-ቺ፣ ሽፍቶች ወደ መሪዎች ሲለወጡ መከላከያ ሚኒስትር ሆኖ ቆየ፤ ያውም አሪፍ!
ተዘርዝሮ የማያልቅ አደጋ አብረው ያሳለፉና ስንትና ስንት ድል አብረው የተቀዳጁ ነበሩ- ማኦ እና ሊዮ። በሽፍትነት ዘመን በደጉ-ዘመን። አለፈቻ!  የሽፍትነት ዘመን።
አይ ደግ ዘመን/ ለስንትና ስንት ዓመት የመሞት የመቁሰል አደጋ እያለበትም፣  ራብና ውሃ ጥም እየተጠናወተውም  አብረን ነበር እምንቆስለው፣ እምንሞተው ባንድ ላይ ነበር፣ እምንራበው፣ እምንጠማው፣ ስናገኝም አብረን ነበረ እምንደሰተው፤ ያውም አንተ ቅደም አንተ ቅደም እየተባባልን፤ አይ ውቢቱ የሽፍትነት ዘመን! ሁላችንም የሕዝባችን ኡኡታ ጠርቶን ወጣን -ከየቤታችን። ተዋጋነው  ያንን “ኡኡ” ያሰኘው፤ የነበረውን (እኛ ህዝብ ነንና፣ የህዝባችን ያካሉ ቁራጭ ነንና፣ የህዝባችንም “ኡኡታ” ውስጣችንም ነበር) እና ባንድነት ተዋጋነው - ያኔ ቢያስፈልግ አንተ ለእኔ ትሞትልኝ ነበር- እኔም ላንተ።
ዛሬ ግን ዞረን እኔና አንተ እርስ በእርሳችን ልንጋደል ሆነ? ግን  ምን መጣና እንዲህ ለወጠን? እኔም አንተም እያወቅነው? ተጋግዘን ጭራቁን  ማባረር ሌላ፤ ተጋግዘን ቻይናን መምራት ሌላ፡፡
የት ነው የተጠፋፋነው መሰለህ? ሁላችንም ለቻይና ሕዝብ ለመሞት ወይም ለማሸነፍ ወጣን። በለስ ቀናንና አሸነፍን። ቀጥሎ ምን መጣ? ያቺን ከህይወታችን አብልጠን እየወደድናት እኩል ልንሞትላት ተስማምተን የተዋጋንላትን ቻይና…
“አሁን ተራችን መጣ፤ እንምራት- እናታችንን” ስንል
 እኔ”በዚህ በኩል ይሻላል” ስል፣ አንተ “በዚያ በኩል ይሻላል” ስትል - መንገዳችን ተቃራኒ ሆነ። አንተም ከልብህ ካንጀትህ “ለቻይናችን ይበጃታል” ያልከው  ወደዚያ አመራ። እኔም ከልቤ ካንጀቴ “ለሕዝባችን ይሻለዋል” የምለው  ወደዚህ አመራ። የኔና የአንተ አብሮ መጓዝ አበቃ። እየወደድኩህ፣ እያከበርኩህም “ያንተ መንገድ ቻይናን ይጎዳል እንጂ አይበጃትም” ብዬ ስላመንኩ እቃወምሃለሁ።
አንተም እንደዚሁ ነው… ስለኔና ስለቻይናችን የምታስበው። ምነው ያንተ መንገድ ትክክል በመሰለኝና አብሬህ በተጓዝኩ! ባይሆንልኝም ያንተንና የቻይናችንን መንገድ ለመጥረግ በሞከርኩ!
ግን ባንተ ቤት የኔ መንገድ የቻይና ጥፋት፤ በኔ ቤት ያንተ መንገድ የቻይና ጥፋት።
ቻይና ከመጥፋቷ በፊት ማንም ግለሰብ መጥፋት አለበት- አንተም ሆንክ እኔ። አያሳዝንም፤ ወይ እኔ ወይ አንተ መጥፋት ሲኖርብን?  እኔና አንተ ልንቻቻል አልቻልንማ! ምናልባት ላንጠፋፋ እንችል ነበር ይሆን? ከኛ በኋላ የሚመጡ አብዮታውያን ያስቡበት። የት እንደተጠፋፋን መርምረው ይድረሱበት፡፡ እዚያ ሲደርሱ እንደኛ እንዳይጠፉ።
ወደ ዛሬይቱ ኢትዮጵያ መለስ ስንል ሂደቱ ያው ነው። አብሮ ጉዞ መጀመር፤ መፈራረጅ፣ መቧደን፣ መፋለም፤ አሸናፊው ወንበር መያዝ ፣ ሰነባብቶ ለተረኛው አስረክቦ ተዋርዶ ወህኒ መውደቅ፣  ወህኒ ማደር! አንድ ባለስልጣን ወህኒ ቤት  ሲጎበኙ፤ “ይህ ወህኒ ቤት በደንብ ይታደስ፤ የወደፊት ቤታችን ሊሆን ይችላል!” አሉ፣ አሉ።
 ከዚህ ይሰውረን!


Read 11809 times