Saturday, 23 July 2022 14:17

ከሰው ቆፈን ይጠብቀን

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ! ውይ ብርድ! ውይ ብርድ! የዘንድሮ ብርድ አይደለም እንደተረቱ፣ ምንስ ቢያሳቅፍ ምን ይገርማል! በዚህ ላይ የነገር ቆፈኑ አልለቀን ብሎ እንዲህ አይነት ክረምት ይጨመርበት፡፡ እኔ የምለው ይቺን ጊዜ እንኳን ብንደጋገፍ ምን ክፋት አለው! የቀድሞ ወይ ከዓመታት በፊት የነበረ ክረምት የሚባል ነገር አለ፡፡ ዝናቡም፣ ብርዱም እንደ ጉድ የሚሆንበት...ልክ የአሁኑ አይነት ክረምት ማለት ነው፡፡ እነ እንትና ትዝ ይላችኋል... ሲኒማ ኢትዮጵያ ፎቅ ላይ... (ዓረፍተ ነገሩን ጨርሱልኝማ! ቂ...ቂ...ቂ...) አንድ ሬስቱራንት ቢጤ ነው አሉ፤ ሰፋ ያለ ጣራና በረንዳ ያለው ቤት፡፡ እናላችሁ... ከሰሞኑ በአንደኛው ቀን ከበድ ያለ ዝናብ ሲጥል የተወሰኑ ሰዎች ተሯሩጠው ወደ በረንዳው ይሄዳሉ። ትንሽ ቆ ይቶም ሙ ልት ይ ላል አ ሉ፡፡ መ ቼም እንደዛ ወለል ያለ በረንዳ አፍጥጦ እያለ ህሊና ያለው ሰው ዝናብ ይውረድባችሁ አይልም፡፡ (ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... “ዝናብ ይውረድባችሁ!” ማለት እኮ...አለ አይደል... እንደ እርግማን ሊሆን ይችላል! አሀ... የተለያየ አይነት ‘ዝናብ’ ሊኖር የሚችልበት ዘመን ነዋ! አይ... ጥቆማ ለመስጠት ሳይሆን እዚህ ሀገር ለትልቀኛውም፣ ለትንሽዬዋም ነገር አራምባና ቆቦ የሚሉት አይነት ‘ትርጉም’ መስጠት ስለተለመደ የተናገርነውም ሆ ነ የ ሠራነው ማ ንኛውም ነ ገር ባላሰብነው መንገድ ቢተረጎም መገረም አይገባን ለማለት ነው፡፡) እንደዛ እየዘነበ፣ በዛ ሰዓት የሚሸቀብ ገበያ በሌለበት፣ ሴትየዋ ያንን ሁሉ ሰው እንደዛ ከፍ ዝቅ ስታደርግ እንዴት ነው ትንሽ የማይሰማት! ትንሽ ሰብአዊነት ቢሰማት ኖሮ፣ ከእነኛ ሰዎች መካከል ምናልባት የእሷ ደንበኞች
ሊኖሩ ይችላሉ..እንደዛ ለይቶ ማሰብ ትክክል ባይሆንም፡፡ ታዲያላችሁ...ዝናብ የሸሸው ህዝብ እንደተጨናነቀ እስኪያባራ እየጠበቀ ሳለ፣ የሆነች ሴትዮ ከውስጥ ብቅ ትላለች፡፡ በቃ፣ አለች አይደል ‘ሞደርን’ የምትባል አይነት፡፡ (ለአንዳንድ ቃላት ትርጉም በመስጠት ለመተባበር ያህል ‘ሞደርን’ ማለት ወደዚች ዓለም ከመጣች ከሀያ ሰባት እስከ ሀምሳ ስድስት ዓመት ሊሆናት ይችላል ለማለት ያህል ነው! ቂ...ቂ...ቂ...) እናማ፣ ሰዉ ላይ ተለቀቀችበት አሉ፡፡
“ይሄ እኮ ንግድ ቤት ነው! እኛ ሥራችንን አንዴት እንሥራ!” በዛ ሰዓት አንኩዋን እሷ ቤት የሚገለገል ሰው ሊመጣ መንገዱ ላይ ዝር የሚል አንድም ሰው አልነበረም እኮ! እንደውም ሌላ ትርፍ፣ ትርፍ ነገር ተናግራለች አሉ፡፡ የምር እኮ እዚህ ሀገር እውነተኛ የባህሪያችን ምንነት ቁልጭ የሚለው እንዲህ አይነት
አስቸጋሪ ነገሮች ሲፈጠሩ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ሴትየዋ እኮ ምኑም ነገሯ አልተነካም! ይልቅ ሠራተኞቿን “ልጆች፣ እስቲ እዛ ጥግ፣ ጥግ የተወሸቁትን ወንበሮች አነሳሱላቸው!” ብትል አይደለም እሷ፣ ወደ ኋላ እስከ አምስተኛ ትወልድ ብትቆጥር ሁሉም በድምር ያላገኙትን ምርቃት ባገኘች ነበር! በዚህ ላይ አሪፍ የፕሮሞሽን ሥራ በሆነላት! ግን ምን ያደርጋል... የክፋትና የእብሪት ዘመን ሆነና፣ እንጀራዋ ላይ ሳይታወቃት ውሀ ደፋችበት፡፡ በሌላ ቀን...
“የዚህ ሬስቱራንት ባለቤት ሰው መሰለችህ!   መልኳን አሳምራ የሆነች ሰይጣን ነገር!”
“ምነው ምን አደረገችህ?”
“በቀደም ያ ሁሉ ዶፍ ሲወርድ በረንዳው ላይ ተጠልለን፣ ያንን ሁሉ ሰው ሙልጭ አድርጋ አትሰድብ መሰለህ!”
“አትለኝም!!“ ሀሳብ አለን...የዘንድሮ ክረምት ያልበረዳቸው ሰዎች ካሉ ዲ.ኤን.ኤ. ይመርመርልን፤ ካሉ ማለት ነው፡፡ (በ‘እኛ ሊግ’ እንደዛ አይነት ወዳጆች
ስላልገጠሙን ነው) አሀ ልክ ነዋ...እሺ የእኛ አይነቱን በምሳሌነት ማቅረቡ ሰዉ ሁለተኛ “ምሳሌ...” የሚባል ነገር ሊያስጠላው ይችላል።
ግን የእኛን ሁለትና ከዛ በላይ የሚያካክሉ ሰዎች ይኸው ከእኛ እኩል ሲንሰፈሰፉ ስናይ በሆዳችን “ቢያንስ፣ ቢያንስ እኩል የሚያደርገን ነገር አገኘን!” ማለታችን እንደተጠበቀ ሆኖ
(“ኦፊሻል” አማርኛ ሊባል ይችላል እንጂ “እንደተጠበቀ...” የምትለዋ ድራፍት ወይም ጀበና ቡና ቦታ የምናነሳት አይደለችም፡፡...ልክ ሚጢጢዬ ወፍ እንኳን ጭር በማትልበት
“አጠናክሮ ቀጥሏል...” እንደምትባለው አማርኛ ማለት ነው!) ክረምትዬው ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡ እንደ እውነቱ ዝናቡን አንጠላውም፣ እንደውም የክረምት አየር ለምን እንደሁ ገና ባልተደረሰበት ምክንያት ይስማማናል የምንል አለን፡፡ የዘንድሮውን ክረምት ብርዱ ባያከፋው ኖሮ!
  እኔ የምለው...የክረምት ነገር ካነሳን አይቀር እነኚህ የአዲስ አባባ መንገዶች እንደው መቼ ነው ለመቦርቦር ‘ዓመታዊ እቅድ’ በሚመስል አይነት፣ ክረምቱ እስኪጋመስ እንኳን መጠበቅ የሚያቅታቸው! አሀ... ገና ክረምቱ በጀመረ በሳምንቱ ብቅ ሲል የሆነ ነገር እኮ በአሳቻ ሰዓት እየመጣ ሲቦረቡራቸው የሚያድርነው የሚመስለው፡፡ እናላችሁ...መአት ስፍራዎች “አዲስ አበባ የምናምን መቶ ጊዜያዊ ሀይቆች ከተማ” አይነት ነገር ሳያስመስሏት አልቀረም፡፡
እሺ የመንገዶቹ ነገር የለመድነው ነው እንበል...አለ አይደል...“ወሬ አጣህና ስለእሱ ታወራለህ! ምን እንዲሆን ነበር የፈለግኸው?” አይነት ነገር የሚያሰኝ!
ደግሞላችሁ...ዘንድሮ ትልቁ መከራ ምን መሰላችሁ... ለሌላው ሰው ማለትመ ለእግረኞች ይችን ታክል የማያስቡ አሽከርካሪዎች መብዛት፡፡ ከርቀት መንገዱ ላይ ውሀ የቋጠሩ ስፍራዎች እንዳሉ እየታያቸው፣ መንገድ ላይ የሚርመሰመሱትን ምስኪን እግረኞች እያዩዋቸው (ይቅርታ...“እያዩን” ለማለት ነው!)
ዝግ ሳይሉ በመጡበት ፍጥነት ማለፍ የክፋት ጥግ ነው፡፡ የምር! ትንሽ እንኩዋን ፍጥነት ቢቀንሱ የትኛው ክብራቸው እንዳይዋረድ ነው! የትኛው ኒሻናቸው እንዳይረግፍ ነው!! የትኛው የምናምን ሀገር አውሮፕላን እንዳያመልጣቸው ነው! እንደው ‘ፖለቲካል ኮሬክትነስ’ የሚሉት ነገር ይዞን ነው እንጂ (ቂ...ቂ...ቂ...) እኛ እግረኞቹ
በዛ ሰዓት የምንላቸውንና የምንረግማቸውን ለሳምፕል ያህል ‘እንደወረደ’ ብናሰፍረው እኛን የማያዩበት በሚመስላቸው በቀለበት መንገድ ብቻ በሄዱ ነበር፡፡
ስሙኝማ... የሆነ ከዚህ በፊት ያወራነው ነገር ትዝ አለኝማ! ከአስርት ዓመታት በፊት አንድ የከተማ ባለስልጣን ምን አሉ መሰላችሁ... “የዛሬ ሁለት ዓመት አዲስ አበባ መንገዶች ላይ አንድ ቀዳዳ የሚያገኝ ማንኛውም ሰው ይሸለማል፣” አሉ፡፡ በኋላ አለቆቻቸው እሳቸው ራሳቸውን ሸለሟቸው...በስንብት ደብዳቤ፡፡ ዘንድሮ በአደባባይ “በእንዲህ አይነት ጊዜ ውስጥ እንዲህ እናደርጋለን...” ብለው ከ‘ሪሊያሊቲ’ ይልቅ በ‘ፋንታሲ’ ለሚጠቀጥቁን ሰዎች የስንብት
ደብዳቤ የሚሸለም ቢሆን፣ ባዶ የሚሆነውን ቢሮ ብዛት ለመቁጠር የሆነ ታስክ ፎርስ ምናምን ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ በነገራችን ላይ...አንዳንድ ወዳጆች “አጅሬ፣ ክረምቱን እንዴት እያሳለፍከው ነው?” የሚል ሆድ የሚያባባ ጥያቄ ተዉንማ! ልጄ ስንትና ስንት ‘ማሳለፊያ መንገድ አለ! በዚህ ላይ በ‘ሀይ ኮፒ’ አባብለን እንዳናሳልፍ ጋቢውም ተወደደ፡፡ (እኔ የምለው... የሴቶች የሀበሻ ልብስ የሚባለውን ዋጋ ስትሰሙ...አለ አይደል... ለድሀ ሀገራት አቅም ታስባ የተሠራች አዲስ መኪና ዋጋ ነው የሚመስላችሁ፡፡) “ስማ ክረምቱ እንዴት እያደረገህ ነው?” በቃ ከተጠየቀ እንዲህ መጠየቅ ነው፡፡ አሀ... ፈጻሚና
የሚፈጸምበት ይለያ! ስሙኝማ... የአሽከርካሪዎች ነገር ከተናሳ... ምንም ቢባል፣ ቢባል እንኳን ሊቀንስ እየባሰበት የመጣ ነገር አለ፡፡ ይሄ እጅን በመስኮት ብቅ እያደረጉ በሰላም የተቀመጠችውን ጣት ከሰው ጋር ማጋጨት! (ቂ...ቂ...ቂ...) እናላችሁ...መኪኖቹ ከእኛ የመኪና አይነት ከመለየት አቅም እየባሱ
ስለሄዱ “ምናምን የምትባል መኪና” ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ እናላችሁ ሴትየዋ በቃ፣ ምን አለፋችሁ “ሰው እንዲህ የተወለወለ ማሰሮ የሚመስለው ምን ቢመገብ ነው!” ታስብላለች። ታዲያላችሁ... የትኛው አሽከርካሪ ጥፋት ይፈጽምባት እሷው ትወቀው፡፡ መሪ በያዘው እጇ ጥሩምባውን እንደ ጉድ እያጮኸችው፣ ሌላኛዋን እጅዋን በመስኮት አውጥታ ላበሳጫት ሰው ብቻ ሳይሆን ለሌሎቻችንም ተርፎ በሚዳረስ አይነት ‘ፊንገርዬዋን’ ለቀቀችዋ! በቀደም በከተማው የትኛው ክፍል እንደሆነ እንጃ እንጂ እንደሰማነው ሁለት አሽከርካሪዎች ይጋጩና አንደኛው ተሽከርካሪ ውስጥ የነበረ ተሳፋሪ በዛኛው መኪና አሽከርካሪ ላይ እንደመትፋት ይልበታል፡፡ በቃ አካባቢዋ ቀውጢ ሆነች አሉ፡፡ በዛኛው መኪና ውስጥ የነበረው ሰው ተሳፋሪው ያልነበረበት መኪና
አልፎት ሄዶ ሊዘጋበት፣ ያኛው ደግሞ ሾልኮ ለማለፍ ሲሞካከሩ የአካባቢውን ትራፊክ ፍሰት አምሰውት ነበር አሉ፤ በመጨረሻ ያኛው እንደምንም ሾልኮ አለፈ አሉ፡፡ ይታያችሁ... ሾፌሩ ሳይሆን ያሳፈረው ሰው ነው እኮ ነገሩን ያከረረው! ይቺ የሦስተኛ ወገን ትንኮሳና ነገር ማባበስ ነች እኮ፣ በትንሹም በትልቁም
እያስቸገረችን ያለችው፡፡ አንድዬ ከዚህም፣ ከዚያም ካሉ ሦስተኛ ወገን ነገር አባባሾች ይጠብቀንማ! የጎን ውጋት ሆኑብን እኮ! ብቻ... የተፈጥሮውንስ ቆፈን በጋቢውም፣ በምናምኑም ልንከላከለው እንሞክራለን፡፡ ከሰው ቆፈን ይጠብቀንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1321 times