Saturday, 23 July 2022 13:19

አብረው የሳቡ ጣቶች ቀርክሃ ያጎብጣሉ! (United we stand, divided we fall)

Written by 
Rate this item
(2 votes)


        ከዕለታት አንድ ቀን አንድ መልካም ድምጽ ያለውና ጫማ ሲሰፋ መደብሩ ውስጥ ሆኖ ማንጓራጎር የሚወድ አንድ ሰው ነበር፡፡ ጎረቤቱ ደግሞ ገንዘብ የተረፈው ባለጸጋ ነበር። ይህ ሀብታም፣ ጫማ ሰፊው በመዝፈኑ ሁሌም ይደነቅ ነበር፡፡ ባለጸጋው አንድ ቀን ጫማ ሰፊውን ወደ ቤቱ አስጠርቶ፤
“መቼም እንዲህ የምትዘፍነው ቢደላህ ነው። ብዙ ብር ሳታገኝ አትቀርም። በዓመት ምን ያህል ታተርፋለህ?” አለው፡፡
ያም ጫማ ሰፊ፤ “ኧረ ምንም አላተርፍም፤ ትርፌ ድካሜ ብቻ ነው” አለና መለሰ። ሀብታሙም፤ “በቀንስ ስንት ታገኛለህ?” አለው።
ጫማ ሰፊውም፤ “ቀለቤን ከቻልኩ በቂዬ ነው። የችግሬን ቀዳዳ ከሸፈንኩ ተመስገን ብዬ እተኛለሁ።” ሲል መለሰለት።
ሀብታሙ ሰው ከት ብሎ ስቆ፤ ወደ ጓዳው ገብቶ፣ አንድ ከረጢት ወርቅ አምጥቶ “እንካ ለቤትህና ለትዳርህ የሚሆንህ ሀብት ነው፡፡ ተጠቀምበት፡፡” አለው።
ያ ጫማ ሰፊ እንዴት እንደሚያመሰግነው ግራ እየተጋባ፣ የተሰጠውን ይዞ ወደ ቤቱ ሮጠ፡፡ ቤት ገብቶም ጓዳውን ቆፍሮ ወርቁን ቀበረው፡፡ ባልጠበቀው የወርቅ ስጦታ እጅግ ተደሰተ፡፡ ውሎ ሲያድር ግን ጫማ ሰፊውን አንዳንድ አጓጉል ሀሳብ ያስጨንቀው ጀመር፡-
“አሁን ከረጢት ሙሉ ወርቅ መቀበሌን ድንገት የሰማና ያወቀ ሌባ ቢመጣና ገድሎ ቢቀማኝ ምን እሆናለሁ?” ይህ ሀሳብ እጅጉን እረፍት ነሳው፡፡
አይጦችና ድመቶች ኮሽ ባደረጉ ቁጥር ይባንናል፡፡ ይሸበራል፡፡ ጭራሹኑ ሌሊት መተኛትም ሆነ ማለዳ ተነስቶ መዝፈኑ ቀረ፡፡ ጤንነት አጣ፡፡ ሀሳብ ብቻ፡፡ ጭንቀት ብቻ፡፡ ስጋት ብቻ። ከዚያ ወርቅ ያገኘውን ጥቅም ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ቢያወጣ ቢያወርደው ምንም ጥቅም አላገኘበትም - ከእንቅልፍ ማጣቱ በስተቀር፡፡ በመጨረሻም ወደ ባለጸጋው ጎረቤቱ ሄደና፤
“ጌታዬ፤ ይኸውልህ ወርቅህን ውሰድልኝ” አለው፡፡
“ምነው?” ሲል ሀብታሙ ጠየቀው፤ ሁኔታው ግራ እያጋባው፡፡
“የለም፤ የጥንት የጠዋቱ ዘፈኔና ድምፄ ይሻለኛል፡፡ ያንን የሚያክል አንዳችም ደስታ በምንም ዋጋ አላገኝም፡፡ እንቅልፌን መልስልኝ!” በማለት ሥጋቱንና ወርቁን መልሶ አስረከበው፡፡
ከዚህ በኋላ ያ ድሀ ጫማ ሰፊ፣ እጅግ ፍንድቅድቅ እያለ ሀሳቡን ሁሉ ጥሎ፤ ወደ ማለዳ ደስታው፣ ወደ ድህነቱና ወደ ሥራው እንዲሁም ወደ ዘፈኑ ተመለሰ፤ ይባላል፡፡
     ***
     ገንዘብን የጨበጠ ሁሉ፣ ሃብትን ያከማቸ ሁሉ ደስተኛ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ያለ ሥራ የሚገኝ ሀብት፣ ከፍስሐው ይልቅ የነብስ ውጪ ነብስ -ግቢ ሰቀቀኑ የበለጠ አሳሳቢ ነው፡፡ ነገን የሚፈጥረው የዛሬ ጥንካሬያችን ነው፡፡ ጥንካሬ በፖለቲካ፣ ጥንካሬ በኢኮኖሚ፤ ጥንካሬ በማህበረ- ሱታፌ፣ ጥንካሬ በራዕይ፣ ጥንካሬ በሽንፈት ባለመሰበር፣ ጥንካሬ በዕውቀት፣ ጥንካሬ ወድቆ በመነሳት ወዘተ ሊተረጎም ይችላል፡፡ በሰላም ጊዜ የምናሳየው ጥንካሬና በጦርነት ጊዜ የምናሳየው ጥንካሬ ከቶም አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ለሁሉም ወሳኙ የትግል መንፈስ ጥንካሬ በአንድ ወገን፤ ቅራኔን የመፍታትና የመቻቻል ጥንካሬ በሌላ ወገን መኖር ነው፡፡ ለሁሉም ጥንቃቄ አስፈላጊ ነው፡፡ ከጥንቃቄ ሁሉ ዋናው ደግሞ፤
“ወፍ ነሽ ሲሉ እዩት ጥርሴን፣ አይጥ ነሽ ሲሉ እዩት ክንፌን” ከሚሉ አድር-ባዮች የምናደርገው ጥንቃቄ ነው፡፡
ቀጣዩ ጥንቃቄ፤
“ማገርና ግድግዳ የማይረዳ፣ ሰፋ አድርገህ ሥራ” እንደሚል ነው፡፡ የሚያወራ አገር ሙሉ መሆኑን አለመርሳት ነው፡፡ “በቅሎ ግዙ ግዙ፤ አንድ አሞሌ ላያግዙ” የሚለውንም ልብ ማለት ያባት ነው። ሌላው ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ፤
“ውሻን በእግር መምታት፣ እንካ ስጋ ማለት መሆኑን” መርሳት አደገኛ መሆኑን መዘንጋት ነው፡፡ በመጨረሻም፤
“አብረው የሳቡ ጣቶች ቀርክሃ ያጎብጣሉ!” የሚለውን የአንድነት ዋንኛ መርህ ከልብ ማሰብ
ያሻል፡፡ ፈረንጅ፤ “United we stand, divided we fall” እንዲል።


Read 11959 times