Saturday, 16 July 2022 18:24

ሳያጠፉ የሚገረፉ እንስቶች

Written by  በሮቤል ሙላት
Rate this item
(0 votes)

“አሁን እሺ ምን ይዤ ነው ወደ ቤት የምመለሰው?”
            
             በጣም ደስ የሚል ቀን ነበር፡፡ ስሜቱ አሁንም አብሮኝ አለ፡፡ ሀዋሳ ምክኒያት እየፈጠረች በሰበብ ባስባቡ የምትፈነጥዝ ከተማ ብትሆንም፣ የዚያ ቀን ድባብ ግን ልዩ ነው፡፡ ማን የቀረ አለ? የምዕራቡ ዓለም የጨርቃ ጨርቅ ባለ ሀብቶች ውቂያኖስ ቀዝፈው መተዋል፤ የምስራቁ ዓለም የኢንዱስትሪ ፓርክ አልሚዎች አህጉር አቋርጠው ብቅ ብለዋል፤ የኢትዮጵያ ቁንጮ ባለስልጣን አራት ኪሎን ጥለው እኛ ሰፈር ዜሮ አንድ፡ አሮጌ አውሮፕላን ማረፊያ ጋ ተከስተዋል።
ሀዋሳ በሀገሬ ሰንደቅ ዓላማና ጥቅስ ባዘሉ ባነሮች ደምቃለች፡፡ የከተማው ወጣቶች ፓርኩን ከበዋል፤ የአካባቢው ሽማግሌዎች ከፊት ቆመዋል፤ የመስኩ ባለሙያዎች ጥግ ጥጉን ወረዋል፡፡ መኃል ላይ ግዙፉ የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ያብረቀርቃል፡፡ ነጸብራቁ በእንግዶቹ ፊት ላይ ያረፈም ይመስላል፡፡ ሁሉም ይህ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እስኪ ጀምር በጉጉት ሲጠብቅ የከረመ ነው፡፡ ወጣቱ አዲስ የስራ ዕድል፤ ነጋዴው ጸዴ የቢዝነስ አማራጭ፤ መንግስት ነፍ የውጭ ምንዛሬን ሲያሰላስል ሰንብቷል፡፡ ጊዜው 2008 ዓ.ም  (እ.ኤ.አ  ሐምሌ 13. 2016) ነበር፡፡
ባጋጣሚ እኔም እዚያው ነበርኩ። ለግንባታው ብቻ 250 ሚሊዮን ዶላር የወጣበትና ወደፊት 60 ሺ ወጣቶችን ይቀጥራል የተባለለት የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እየተመረቀ ነው። የቀድሞው ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ ሲናገሩም ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ፓርክ ሚናው ዘርፈ ብዙ እንደሆነ፤ ለብዙ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥርና ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀላል ማምረቻ ማዕከል እንደምትሆን አበሰሩ፡፡ ዶ/ር አርከበ ቀጠሉ፡፡ የዚህ ፓርክ ተምሳሌትነት ትልቅ እንደሆነ መሰከሩ፡፡ የ PVH Global Supply ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ማርክ ግሪኒ ቀጠሉ፡፡ ምርጡን የአልባሳት ምርት ከሀዋሳ ጠብቁ ሲሉ አከሉ፡፡ ጭብጨባው ብዙ፤ ፉጨቱ ረጅም፤ እልልታው ከፍ ያለ ነበር፡፡
ከስድስት ዓመት በኋላ፡፡ የአለማችን ሁለተኛው ግዙፉ የአልባሳት ድርጅት በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ያለውን ፋብሪካ መዝጋቱን አስታወቀ፡፡ ባለፉት ሳምንታት ደግሞ የህንዱ ቤስት ጋርመንት፣ ሶስት ሺ የሚሆኑ ሰራተኞቹን ለማሰናበት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ እንደሆነ አስታወቀ። ጉዳዩ በፓርኩ ውስጥ የሚሰሩ ከ35 ሺ በላይ ሰራተኞችን አሳስቧል፡፡ አንዳንዶች የችግሩ ምንጭ፣ ምክኒያቱና የነሱ ተሳትፎ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ አጎዋ (AGOA) ተብሎ ከሚጠራው የአሜሪካ የንግድ እድል መሰረዟ ባለሀብቶቹን እንዲሸሹ፤ ሰራተኞቹ እንዲደነግጡ አድርጓቸዋል፡፡ በእርግጥ መንግስት “ችግሩ እንደሚወራው አይደለም” ብሎ  ቢያስተባብልም፡፡ አጎዋ የተመረጡ ታዳጊ ሀገሮች የጨርቃ ጨርቅ ምርቶቻቸውን ያለ ቀረጥ ወደ አሜሪካ ገበያ የሚያስገቡበት እድል ነበር፡፡
የዋሽንግተን ቁንጥጫ
ያለፉትን ሁለት ዓመታት አሜሪካና ኢትዮጵያ ተዋደዱ ሲባል ሲራራቁ፤ ደግሞ ተኳረፉ ሲባል ሲቀራረቡ ይታያሉ፡፡ ቢሆንም የሰሜኑ ጦርነት ግንኙነታቸው ላይ የእንቅፋት ጠጠር እየጣለ መሄዱ እሙን ነው፡፡ በተለይም በቅርቡ ኢትዮጵያን ከአገዋ ተጠቃሚነት የሚያስወጣው ውሳኔ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሲፈረም ዳፋው  ሀዋሳ እንደሚደርስ ተፈርቶ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት፣ ውሳኔው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስራ እንደሚያሳጣና በተለይም ሴቶችን እንደሚጎዳ አስጠንቅቀዋል (ለምሳሌ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስተር ለገሰ ቱሉ ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንዲሁም  የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ማሞ ምህረቱ ለፎሬይን ፖሊሲ መጽሄት)፡፡ ምን ዋጋ አለው? ረፈደ፡፡
ይሁን እንጂ የዋሽንግተን ቅጣት፤ ምክኒያቱና ዳፋው ግራ የሚያጋባ፣ ግዜውን ያልጠበቀና መከራከሪያቸውም ሚዛን የሚደፋ አይደለም። ኢትዮጵያ ከአገዋ የተሰረዘችበት ምክኒያት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውን ሰብዓዊ መብቶች በመጣሷ ነው ትላለች አሜሪካ (for gross violations of internationally recognized human rights)፡፡ ይህ ጉዳይ በዋናነት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተካሄደውን አሳዛኝ ደግሞም አሳፋሪ ጦርነት ይመለከታል። ይህ ጉዳይ ራሱ ውስብስብ፣ የብዙ ሀይሎች ፍላጎትና እጅ ያለበት በመሆኑ የኔ ጽሁፍ እሱን አይመለከትም፡፡ የኔ ሀሳብ ማዕከል ለፍቶ አዳሪዎቹ የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሰራተኞች ናቸው፡፡
የአሜሪካ ውሳኔ በጦርነቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሌላቸው፤ ጉልበታቸውን ገብረው የሚያድሩ፤ በገጠር የሚገኙ ዘመዶቻቸውን የሚጦሩ እንስት የፋብሪካ ሰራተኞች ለምን የቅጣቱ በትር ያርፍባቸዋል? የኔ መከራከሪያ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ቋሚ ሰራተኞችን ከስራ ገበታቸው ማፈናቀል ሰብዓዊ መብት መጣስ አይደለምን? ወደ ልመና ተንደርድረው  እንዲገቡ ማድረግስ ሰብዓዊ መብት መጣስ አይደለምን? ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቀጥተኛ ያልሆነ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተጠቃሚ ማህበረሰብ ገቢ እንዲያጣ ማድረግስ ሰብዓዊ መብት መጣስ አይደለምን? ሁለቱም ተፋላሚ ሀይሎች የሴቶች ሰብዓዊ መብት ጥሰዋል ብለው እየከሰሱ እዚህ ያለ ጦርነት ሰላማዊ የፓርክ ሰራተኞችን በግዳጅ ወደ ትውልድ መንደራቸው መመለስ ሰብዓዊ መብት መጣስ አይሆንምን?
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከውጭ ምንዛሬ ማምጣት እና ከቴክኖሎጂ ሽግግር በፊት የሚፈጥሩት ሰፊ የስራ እድል ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ የስራ አጋጣሚ ሲቀንስ ወይም ሲጠፋ መጀመርያ ኢኮኖሚያዊ ችግር፣ ከዚያም ማህበራዊ ቀውስ፤ በኋላም ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ  አስከትሎ አካባቢውን የድህነት አዙሪት ውስጥ ያሽከረክረዋል፡፡ ስለዚህም ነው ሴቶችን በመቅጣት ዘላቂ ሰላም አይመጣም የምለው፡፡ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ አበው፣ በትሩ ያለፈው ምስኪኖቹ ላይ ነው፡፡
የሀዋሳ ኩርፊያ
ከመዝናኛ፣ ከኮንፈረንስ ከተማነት ወደ ኢንዱስትሪ ማዕከልነት እየተሸጋገረች ያለችው ሀዋሳ በፓርኩ ብዙ አትርፋለች፡፡ ቀጥተኛ ያልሆኑ የስራ እድሎችን  ፈጥራለች፣ መሰረት ልማቷን አስፋፍታለች፣ የገቢ ግብሯን አሳድጋለች፤ እምቅ የመልማት አቅሟን በብዙ አቅጣጫ አስተዋውቃለች፡፡ ከዚህ ባሻገር ካንዴም ሁለት ግዜ ከተማዋ የተጋፈጠችውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር የፓርኩ መኪኖችና ባለሙያዎች በእጅጉ አስፈላጊ ነበሩ፡፡ ከአካባቢ ጥበቃና ከጉልበት ብዝበዛ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች  እንዳሉ ቢታመንም፣ በፓርኩ የሀዋሳ ተጠቃሚነት ግን ገሀድ ነው፡፡
ከሰሞኑ ግን ከስራ የለቀቁ፣ ወደ ገጠር በመመለስና በመቅረት መካካል የሚዋልሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞችን ተመልክቻለሁ። አዲስ ስራ ተይዞ፣ የከተማ ኑሮ ተለምዶ እና ብዙ ተስፋ ተሰጥቶ ሲያበቃ እንዲሁ በድንገት ወደ መጡበት መሄድ ከብዷቸዋል (መቋቋሚያ የ3 ወር ደመወዝ የሚሰጣቸው አሉ)፡፡ የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቶ፣ የገጠር ህይወት ከእጅ ወደ አፍ ብቻ ሆኖ ቀርቶ፤ ከፓርክ ውጭ የለመዱት ሌላ ስራ በሌለበት ሁኔታ ወደ ቤት መሄድ ጭንቅ ብሏቸዋል፡፡ ስለ አጎዋ በደንብ ሳይሰሙ፤ ስለ ሀገራቸው ከእድሉ መባረር ምንነት ሳይረዱ፤ በሰሜኑ ጦርነት የነሱ አስተዋጽኦ ምን እንደነበረ ምክኒያቱ ሳይነገራቸው ግራ እንደገባቸው አሉ፡፡
እናም መንግስት ይህን ቢያደርግ እላለሁ፡፡ አንደኛ፡ አማራጭ ገበያዎችን ማፈላለግ (ኤሽያና አውሮፓ)፡፡ ሁለተኛ፡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ማድረግ (የውጭ ባለሀብቶች ጥገኝነትን መቀነስ)፡፡
ሶስተኛ፡ ወደ አጎዋ ለመመለስ እልህ አስጨራሽ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት፡፡ አራተኛ፡ የሚቀነሱ ሰራተኞችን ማደራጀት፣ ማቋቋምና በህብረት የሚሰሩበትን ዘዴዎች በመቀየስ ወደ ተግባር መግባት፡፡
ሁሌም አንዲት የፓርኩ ሰራተኛ የነገረችኝን አስታውሳለሁ፤ “አሁን እሺ ምን ይዤ ነው ወደ ቤት የምመለሰው?”
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡




Read 11362 times