Saturday, 16 July 2022 18:05

ኢትዮጵያ በኦሬጎን ላይ 5 የወርቅ፤ 2 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች ትወስዳለች- Athletics Weekly

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከኬንያ ቀጥሎ በአፍሪካ ሁለተኛውን ትልቅ ውጤት ያስመዘገበች ናት

          18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሜሪካዋ ኦሬጎን ከተማ ትናንት ተጀምሯል። ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው ታሪክ  በመካከለኛና ረጅም ርቀት የሩጫ ውድድሮች የላቀ ውጤት ከሚያስመዘግቡ አገራት ተርታ እንደምትሰለፍ ይታወቃል፡፡ ኦሬጎን ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ድረስ በሁለቱም ፆታዎች 40 አትሌቶችን  (21 ወንድና 19 ሴት) የሚያሳትፍ ይሆናል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው ትናንት ሲጀመር በ1500ሜ የማጣርያ ውድድሮች እንዲሁም በ3ሺሜ መሰናክል የፍፃሜ ውድድሮች ተደርገዋል፡፡
ታዋቂው የእንግሊዝ የአትሌቲክስ ዘጋቢ መፅሄት አትሌቲክስ ዊክሊ ዓለም ሻምፒዮናው ከመጀመሩ በፊት የአትሌቲክስ ባለሙያዎችና እውቅ ጋዜጠኞችን በማሳተፍ በሰራው ትንበያ ኢትዮጵያ ኦሬጎን ላይ 5 የወርቅ፤ 2 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች እንደምትወስድ ገምቷል። በአትሌቲክስ ዊክሊ ላይ በዝርዝር በቀረበው የትንበያ ሪፖርት በወንዶች ምድብ ሰለሞን ባረጋ በ10ሺ ሜትር የወርቅ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ እንደሚወስድና ለሜቻ ግርማ በ3ሺሜ መሰናክል የወርቅ ሜዳልያ እንደሚያገኝ ተጠብቋል፡፡ በ1500 ሜትር እና በማራቶን በወንዶች  ለኢትዮጵያ ምንም አይነት የሜዳልያ ግምት አልተሰጠም፡፡  በሌላ በኩል በሴቶች በ1500ሜ ሂሩት መሸሻ የብር ሜዳልያ፤ በ5ሺ ሜትር ጉዳፍ ፀጋዬ የወርቅና እጅጋየሁ ታዬ የነሐስ፤ በ10ሺ ሜትር ለተሰንበት ግደይ የወርቅና ቦሰና ሙላትዬ የነሐስ እንዲሁም በማራቶን ጎይቶም ገብረስላሴ የወርቅ ሜዳልያዎችን ሊያገኙ እንደሚችሉ የአትሌቲክስ ዊክሊ ባለሙያዎች ተንብየዋል፡፡
ከ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊት በ15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ተካፍላለች፡፡ በወንዶች ከ1983 እኤአ ጀምሮ በሴቶች ደግሞ ከ1991 እኤአ ጀምሮ ነው ተሳታፊ የሆነችው፡፡ ከኦሬጎን በፊት ኢትዮጵያ  በሁለቱም ፆታዎች የሰበሰበቻቸው ሜዳልያዎች ብዛት   85  ሲሆን 29 የወርቅ፤ 30 የብርና 26 የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው። ይህም በሻምፒዮናው አንድና ከዚያም በላይ ሜዳልያዎችን ከሰበሰቡ 102 አገራት መካከል 7ኛ ደረጃ  ላይ ሲያስቀምጣት በአፍሪካ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ውጤት ነው። በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለአፍሪካ ትልቁን ውጤት ያስመዘገበችው አገር ኬንያ ናት፡፡ ኬንያ ከ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊት በ17 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች  በመሳተፍ  በሁለቱም ፆታዎች ያስመዘገበቻቸው ሜዳልያዎች ብዛት   151  ሲሆን 60 የወርቅ፤ 50 የብርና 41 የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡ ይህም በዓለም ሻምፒዮናው ታሪክ ሜዳልያዎችን ከሰበሰቡ 102 የዓለም አገራት መካከል 2ኛ ደረጃ  ሲያሰጣት አፍሪካን ደግሞ በአንደኛ ደረጃ ትመራለች፡፡ በአፍሪካ ከሚኘጉ 54 አገራት መካከል በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አንድና ከዚያም በላይ ሜዳልያዎችን የሰበሰቡ አገራት 23 ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ (12 የወርቅ፤ 7 የብርና 8 የነሐስ)፤ ሞሮኮ (10 የወርቅ፤ 12 የብርና 8 የነሐስ) እንዲሁም አልጄርያ (6 የወርቅ፤ 1 የብርና 3 የነሐስ) ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ተከታታይ ደረጃ ይወስዳሉ። 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን የምታካሄደው አሜሪካ ከኦሬጎን መስተንግዶዋ በፊት  በ17 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ተሳትፋ ዓለምን የምትመራበት ከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ አስመዝግባለች፡፡  አሜሪካ በ17 የዓለም ሻምፒዮናዎች የሰበሰበቻቸው ሜዳልያዎች ብዛት   381  ሲሆን 170 የወርቅ፤ 117 የብርና 94 የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከኢትዮጵያና አፍሪካ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን  በ10ሺና በ5ሺ ሜትር 7 ሜዳልያዎችን(4 የወርቅ ፤ 2 የብርና 1 የነሐስ)   በማግኘት ነው፡፡  ኃይሌ በ10,000ሜ 4 የወርቅ ሜዳልያዎች በ1993, 1995, 1997, 1999 እኤአ ላይ ሲጎናፀፍ፤ የብር ሜዳልያ 2003 እንዲሁም  የነሐስ ሜዳልያ 2001 እኤአ ላይ ወስዷል፡፡ በ5000ሜ ደግሞ የብር ሜዳልያ ያስመዘገበው በ1993  እኤአ ነው።   
ቀነኒሳ በቀለ በዓለም ሻምፒዮናው የተሳትፎ ታሪኩ  በ10ሺና በ5ሺ ሜትር 6 ሜዳልያዎችን (5 የወርቅና 1 የነሐስ) በመውሰድ  ለኢትዮጵያና አፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ የሚያስቀምጠውን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ቀነኒሳ በዓለም ሻምፒዮናው የሰበሰባቸው ሜዳልያዎች በ10000ሜ 4 የወርቅ ሜዳልያዎች በ2003 ,በ2005 ,በ2007ና በ2009 እኤአ እንዲሁም በ5000 ሜ የወርቅ ሜዳልያ በ2009ና የነሐስ ሜዳልያ በ2003 እኤአ ነው፡፡
 ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር 6 ሜዳልያዎችን (5 የወርቅና 1 የብር) በመጎናፀፍ ከሴቶች ከፍተኛውን ውጤት ለኢትዮጵያና አፍሪካ አስመዝግባለች፡፡ ጥሩነሽ በአፍሪካ አትሌቲክስ በሴቶች ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው በ10,000 ሜትር 3 የወርቅ ሜዳልያዎች 2005, 2007, 2013ና የብር ሜዳልያ 2017 እኤአ ላይ እንዲሁም በ5000ሜ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች 2003ና 2005 እኤአ ላይ በመውሰድ ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከተመዘገቡ ክብረወሰኖች ሁለቱ በኢትዮጲያ አትሌቶች እንደተያዙ ናቸው፡፡ በ10ሺ ሜትር ወንዶች ቀነኒሳ በቀለ በ2009 እኤአ በርሊን ላይ 26፡46.31 እንዲሁም በሴቶች 10ሺ ሜትር በ2003 እኤአ ፓሪስ ላይ ብርሃኔ አደሬ 30፡04.18 በሆነ ጊዜ ያስመዘገቧቸው ናቸው፡፡


Read 1395 times