Saturday, 16 July 2022 18:01

ባለፈው ሰኔ ወር በስድስት ክልሎች አስከፊ ግጭቶች ተከስተዋል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ባለፈው ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስድስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ብሔርንና ጎሳን መሰረት ያደረጉ  አስከፊ ግጭቶችና  ጥቃቶች መከሰታቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ሪፖርት ያመለክታል፡፡
በመገናኛ ብዙኃን በስፋት የሚነገረው በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ የተከሰቱ  ብሔር ተኮተር ጥቃቶች ቢሆኑም፣ በተለያዩ  የሃገሪቱ አካባቢዎችም ከመገናኛ ብዙኃን የተሰወሩ አስከፊ ጥቃቶችና ኢ-ሠብአዊ ድርጊቶች በሠላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈፀሙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በተከሰቱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ህይወት ከመጥፋቱም ባሻገር በ10ሺ የሚገመቱ ከሞት የተረፉ ዜጎች ሃብት ንብረታቸውን ማጣታቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የወለጋውን ጥቃት ተከትሎ 20 ሺህ 5 መቶ ያህል ዜጎች አካባቢውን ጥለው ወደ አማራ ክልል እንደገቡ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በተጠናቀቀው የሰኔ ወር ከኦሮሚያ ውጪ ግጭቶች አይለው ከታዩባቸው አካባቢዎች፡- በአፋር ክልል አውሲ፣ ገቢ፣ ሃሪ ዞኖች፣በሶማሊ ክልል ሊበን ዞን፣በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ካማሺ እና አሶሳ አካባቢ፣ በደቡብ ክልል ደራሼ እና አሌ ወረዳዎች፣የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የደቡብ ወረዳዎች (ጌዲኦ ዞን፣ አማሮ፣ ቡርጂ) ይጠቀሳሉ፡፡
በአንጻሩ ለበርካታ ጊዜያት በግጭትና ጥቃት ቀጠናነቱ የሚታወቀው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ባለፈው ሰኔ ወር አንጻራዊ መረጋጋት እንደታየበት እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞንም በአንጻራዊ መረጋጋት ውስጥ ማሳለፉን የተመድ የሠብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሪፖርት ያመለክታል፡፡

Read 11598 times