Print this page
Saturday, 02 July 2022 18:06

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  “ነገም ሌላ ቀን ነው” በድጋሚ ታተመ


           ‘’GONE WITH THE WIND’’ በማርጋሬት ሚሼል ተደርሶ በባለቅኔ ነቢይ መኮንን፣ የአሥር ዓመታት የእሥር ቤት ቆይታ ውስጥ በሲጋራ ፖኬት አልሙኒዬሞች ወደ አማርኛ ተተርጉሞ፣ በ1982 ዓ.ም ‘’ነገም ሌላ ቀን ነው’’ በሚል ርዕስ ለኅትመት የበቃ ውድ መጸሐፍ ነው።
ዛሬ በማለዳ የጎበኘን መልካም ዜና ደግሞ ከአሮጌ ተራና ከአንዳንድ መደብሮች ዘንድ ብቻ በጠነነ ዋጋ ይገኝ የነበረው ይኽ ብርቅዬ ሥራ፣ ከሠላሳ ምናምን ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ኅትመት ብርሃን መመለሱን አብስሮናል። ምንም እንኳን የወረቀት ዋጋ ንረት እየተምዘገዘገ ያለበት ፍጥነት ለነዚህ አይነት ዳጎስ ያሉ ሥራዎች መመናመን ዋነኛው ምክኒያት ቢሆንም፣ እንግዲህ ‘’ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርምን’’ ተርተው ይህን ላቀበሉን አሳታሚዎች፣ በተወዳጇ እስካርሌት ስም እጅ ነስተናል።
እነሆ ጥቂት መስመሮች ከመጽሐፉ፦
‘’እናቷ እንዳታያት ፊቷን በታጠፉ እጆቿ እቅፍ ውስጥ ደፍታ ወደ አሽሌይ መሪር ጉዳይ ሀሳቧን አሰማራች። እስከርሌትን ከልቡ እያፈቀረ ሳለ እንዴት ሜላኒን ለማግባት ያቅዳል እሷ እንዴት እንደምታፈቅረው እያወቀ  እንዴት ሆነ ብሎ ቅስሟን ለመስበር ይነሳሳል ከመቅጽበት ሠማያት ሰንጥቆ እንደተወነጨፈ ተወርዋሪ ኮከብ አንድ ሀሳብ በአእምሮዋ ተፈነጠቀ።
“አሃ አሽሌይ እኮ እንደማፈቅረው አያውቅም።” በዚህ ድንገት ደራሽ ሐሳብ ድንጋጤ ገባት። ቁና ቁና ተነፈሰች። አዕምሮዋ ለረዥምና ትንፋሽ አልባ ለሆነ ግዜ ሽባ የሆነ ያህል ጸጥ ዝም ብሎ ቆይቶ ወዲያው ሽምጥ ግልቢያውን ወደ ፊት ቀጠለ። “እውነት እንዴት ያውቃል ሁልጊዜ ሲያገኘኝ አንገቷን የደፋች ጭምት ሴት ሆኜ ነው የሚያየኝ ። የማልደፈርና አትንኩኝ ባይ ሆኜ ሲያገኘኝ እንደው እንደ ማንም ወዳጅ እንጂ ከዚያ ከፍ አድርጌ እንደማላየው አድርጎ ሊገምት ይችላል። አዎ፤ ለዚህ ነው በፍጹም የልቡን ነግሮኝ የማያውቀው ልክ ነው፤ ቢያፈቅረኝ ተስፋ ቢስ አፍቃሪ የሚሆን መስሎት ነው። ለዚህ ነው ሁልግዜ ሁኔታው. . . . .”
አዕምሮዋ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ጥንቶቹ ቀናት ገሰገሰ። እነዚያ ግራጫ አይኖቹ ለውስጣዊ ስሜቱ መጋረጃ ሆነው በሰፊው ይከፈቱና እርቃናቸውን ሲቀሩ እንግዳ በሆነ ስሜት ተሞልተው ሲያስተውሏት ይዛቸዋለች። ከቶውንም በውስጣቸው ስቃይንና ተስፋ መቁረጥን እንዳዘሉ ትዝ ይላታል።
”ተስፋም የለኝ ብሎ ቅስሙ የተሰበረው ወይ ከብሬንት ወይ ከስቱዋርት አሊያም ከካድ ጋር ፍቅር የያዘኝ መስሎት ይሆናል። ምናልባትም እኔን የማያገኝ ከሆነ፥ ሜላኒን አግብቶ ቤተሰቡን ማስደሰት የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ገምቶ ይሆናል። ሆኖም እኔ እንደማፈቅረው አውቆ ቢሆን ኖሮ ግን..“
ያ ቶሎ ግንፍል ፍንድት የሚለው መንፈሷ ከቅስም መሰበር አዘቅት ወጥቶ፤ ሽቅብ ወደተሳከረ ደስታ ተመነጠቀ፤ ተስፈነጠረ። ለአሽሌይ ቸል ማለትና ለእንግዳ ጸባዩ ምክንያት አገኘችለት— የሷን የፍቅር ስሜት ባለማወቁ ነው- ይሄው ነው። ብኩንነቷ ፍላጎቷን ለማገዝ በፍጥነት እየሮጠ ያሰበችውን እንድታምን አደረጋት፤ እምነቷ ደግሞ በፈንታው የገመተችው ነገር ሁሉ እርግጠኛና እውን የሆነ ነገር መሆኑን ማስተማመኛ ሰጣት።
እንደምታፈቅረው አውቆ ቢሆን ኖሮ ወደሷ ይጣደፍ ነበር። አሁን ማድረግ ያለባት...
“ወይኔ!” አለች በከነፈ ሀሳቧ፤ የተከደኑ ቅንድቦቿን በጣቶቿ የመቆፈር ያህል እያሸች። “ይህን ነገር እስከዛሬ አለማሰቤ ምን ጅሏ ነኝ ባካችሁ፤ አሁን እንደምንም እንዲያውቅ ማድረግ አለብኝ።
እኔ እንደማፈቅረው ካወቀ በጭራሽ እሷን አያገባም እንዴት ብሎ ”
ቀና ስትል ጄራልድ እንደጨረሰና የእናቷ አይኖች እሷ ላይ እንዳረፉ ተገነዘበች። በፍጥነት የጸሎት መነባነቧን ጀመረችና መቁጠሪያዋን ስታክቸለችል፤ ድንጋጤ በወጠረው ስሜት የምታወጣው ጉልህ ድምጽ፤ ማሚ አይኖችዋን ገልጣ ወደሷ እንድታነጣጥር አስገደዳት። ጸሎቷን እንደጨረሰች፤ ሱዌለንና ካሪን ግን ገና ጸሎት መጀመራቸው ስለሆነ አዕምሮዋ አዲስ ወደተወለደው ሐሳብ አሁንም ተወረወረ ...

_________________________________________________


          ወደፊት ሊታተም ከተዘጋጀው የነቢይ መኮንን መጽሐፍ


               ያልታተመው መግቢያ (THE UNPUBLISHED PREFACE)  
ማርጋሬት ሚሼል መጽሐፏን ጽፋ ለመጨረስ አስር ዓመት ፈጅቶባታል - ከ1926 – 1936። ይኸውም ታማ የአልጋ ቁራኛ ሆና በነበረበት ጊዜ ነው። እኔም የማርጋሬት ሚሼልን ጐን ዊዝ ዘዊንድ ለመተርጎምና ለማሳተም ከሞላ ጎደል አሥር ዓመት   ፈጅቶብኛል። ከ1971 – 1981 ዓ.ም.  የማርጋሬት ሚሼል ህመምና የኔ ህመም ባይመሳሰልም፣ ሁለታችንም ህመምተኞች መሆናችን ያመሳስለናል። ያቀራርበናል። እሷ በመኪና አደጋ ሳቢያ ቁርጭምጭሚቷን ታማ የአልጋ ቁራኛ፤ እኔ ደሞ የሀገር ህመም ታምሜ የእስር ቁራኛ።
መጽሐፉን እተረጐምኩበት ቦታ ለመድረስ ብዙ ተጉዣለሁ። አራት ዋና ዋና እስር ቤት ውስጥ ታስሬአለሁ። እንደሚከተለው፡-   
1) አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ   
2) ከፍተኛ 15 (ዛሬ ወረዳ 15) ቀበሌ 34   
3) ደርግ ጽሕፈት ቤት (አራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት ቅፅር ግቢ)   
4) ማዕከላዊ ምርመራ ጽ/ቤት ቤተ-መንግሥት። ደርግ ጽ/ቤት እስር ቤት። እስቲ ምን የመሰለ የተንጣለለ ግቢና ያን መሳይ ትልቅ አጥር እንዲሁም ከመሬት ማህፀን የበቀለ የሚመስል ህንፃ አቋርጬ አልፌ ሳበቃ እዚህ ልግባ? ለካ ቤተ-መንግሥት ግቢ ውስጥም እንዲህ ያለ ቦታ ኖሯል? ሲኦል እገነት ማህል ነው እንዴ ያለው?  ይሄ መቸስ በጭራሽ የሰው መኖሪያ አይመስልም። በየክፍሉ የተጠቀጠቀው ሰው ብዛት ራሱ፤ ይሄ ቦታ ከመኖሪያነት ወደመሰቀያነት ለመለወጡ ምስክር ነው። የውጪ በሩም የቆርቆሮ ነው። ውስጡ ሦስት የተለያየ ስፋት ያላቸው በተርታ ተያይዘው የሚታዩ ክፍሎች አሉት። የነዚህ የሁሉም ደጃፍ ያው ግቢ ነው። በአጥር ግቢው አንድ ጥግ ላይ ለሽንት መሽኚያ የሚያገለግል ትልቅ ጉርድ በርሜል አለ። ባንደኛው ጥግ ደግሞ የውሃ ቧንቧ ይታያል። ከቧንቧው አጠገብ በአራት ቋሚዎች የተያዘ የቆርቆሮ ጣራ ያለው የዘብ ቤት አለ። ውስጡ ያለው የመመዝገቢያ ጠረጴዛና አግዳሚ ወንበር እንዲሁም አንድ ባሕረ-መዝገብ፣ ከአንድ ሁለት ዘቦች ጋር ሁልጊዜ የሚታይ ስዕል ነው።



Read 2287 times
Administrator

Latest from Administrator