Saturday, 02 July 2022 17:52

ከሕልም ርቀናል። ቅዠት አዘውትረናል።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን የሚያስወግድና የሚተካ ትክክለኛ ሃሳብ ካልጨበጥን፣…
የእያንዳንዱን ሰው ሕልውና ካላከበርንና እንደየስራው ዳኝነት መስጠት ካልቻልን፣…
 ለዛሬ ባይሆን እንኳ ለነገ ብሩህ ሕልም ካልያዝን ሰላም አይኖረንም።
ከምር፣ ለነገ የሚዘልቅ መፍትሄ እንዲኖረን ከፈለግን፣ ብሩህ ህልም ያስፈልገናል።
በትክክለኛ ሃሳብ የተቃኘ…
የተቃና መንገድን የተከተለ፣ …
“ብሩህ የሩቅ ሕልም” መያዝ ይኖርብናል። ከዚህ የሚመጣ “አገራዊ መግባባት” አይኖርምና። ቢኖርም እንደገለባ በነፋስ ሽውታ በአንድ አዳር የሚጠፋ ነው።
“ብሩህ ሕልም” ማየት ብንችል፤ ነገ ወይም ከነገወዲያ፣ ተዓምረኛ ለውጥ ይመጣል ማለት አይደለም። አይመጣም። ከመነሻው፣ “ብሩህ የሩቅ ሕልም” አስፈላጊ የሚሆነውኮ፣ በአንድ ጀምበር፣ እንደ ትንግርት የምናወራለት ለውጥ ተዓምረኛ ስለማይመጣ ነው።
አሜሪካ፣ እንደ አዲስ የተወለደች ጊዜ፣ የያኔዎቹ ፈርቀዳጅ ሰዎች ምን አይነት ሕልም እንደነበራቸው አስታውሱ።
“ሁሉም ሰዎች፣ በተፈጥሮ እኩል ናቸው።
እያንዳንዱ ሰው፣ የገዛ ራሱ ሕይወት ብቸኛ ባለቤት ነው።
አእምሮውንና አካሉን የመጠቀም፣ የማሰብና የመስራት ነፃነት አለው።
እያንዳንዱ ሰው፣ በጥረቱ ኑሮውን የማሻሻል፣ ከቻለም ሃብት የማፍራትና የንብረት ባለቤት የመሆን መብት አለው። …
እነዚህ ሃሳቦችን በይፋ የሚያውጅ ነበር- የያኔው ብሩህ ሕልም።
ጊዜው፣ የዛሬ 246 ዓመት፣ በዚህ ሳምንት ነው። ከተለያዩ የአሜሪካ ክልሎች የተውጣጡ የያኔው ታዋቂ ፖለቲከኞችና ምሁራን፣ በፍላደልፊያ የተሰበሰቡት፣ በእንግሊዝ መንግስት ላይ በማመጽ ነው። ከእንግሊዝ አገዛዝ ለመለየት የወሰኑበትን ምክንያት ለማስረዳትም፣ የነጻነት አዋጅ አዘጋጅተዋል።
ታዲያ የአመጽ ፍቅር ኖሯቸው አይደለም። ለጥቃቅንና ለጊዜያዊ አላማዎች ተብሎ፣ ነባር የመንግሥት ስርዓትን ለመለወጥ የሚካሄድ አብዮት ተገቢ እንዳልሆነ ያምናሉ። ሌሎች አማራጮች ሁሉ ካተዘጋጉ በስተቀር ነባር ስርዓትን ለመቀየር አመፅ ማስነሳት እንደማይገባ ይጠቁማል አዋጁ።
Prudence, indeed, will dictate that Governments long established should not be changed for light and transient Causes…
በደል ሲበዛና አማራጭ ሲጠፋ ግን፣ ነባሩን ሥርዓት መለወጥ ወይም ማሻሻል የግድ አስፈላጊ እንደሚሆን ይገልፃል - ሰነዱ።
ተሰብሳቢዎቹ የአሜሪካ ፖለቲከኞችና ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ፣… የእንግሊዝ መንግሥት፣ ግፍ አብዝቷል። የሰዎችን ሕይወት ማበላሸት፣ ጎተራቸውንና ኪሳቸውን ማራቆት ለምዷል። ለሰዎች አቤቱታ ጆሮ አይሰጥም። በተቃራኒው፣ በበደል ላይ በደል እየጫነብን ነው በማለት ምሬታቸውን ዘርዝረዋል።
እናም፤ ሌላ መፍትሔ ስለጠፋ፣  “በቃ” ለማለት ወስነዋል። ውሳኔያቸውም፣ የእንግሊዝን የቅኝ ግዛት ለማስወገድና የአሜሪካ ነጻነትን ለማወጅ ነው።
ታዲያ፣ “በደል ወይም ግፍ በዛ”፣ በሚል ምክንያት ብቻ፣ እንዲሁ በዘፈቀደ ነባር ሥርዓትን ማፍረስና በሌላ በማንኛውም ሥርዓት መለወጥ ጥሩ ነው ማለታቸው አይደለም።
ነባር ሥርዓት፣ ሊለወጥ ወይም ሊሻሻል የሚገባው ምን ዓይነት ችግር ሲኖረው ነው?  ለውጥ ተገቢ የሚሆነውስ፣ ወደ ምን ዓይነት አዲስ ሥርዓት ነው? ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች፣ ሰነዱ መልስ ይሰጣል። በቅድሚያ ግን፣ መሰረታዊ መርሆችን ያቀርባል።
We hold these Truths to be self-evident,
that all Men are created equal,
that they are endowed by their Creator with certain unalienable Rights,
that among these are Life, Liberty, and the Pursuit of Happiness—
That to secure these Rights, Governments are instituted among Men,…
that whenever any Form of Government becomes destructive of these Ends, it is the Right of the People to alter or to abolish it, and to institute new Government,…
የአሜሪካ መሥራቾች፣ በዚሁ የነፃነት አዋጅ፣ ብሩህ ሕልማቸውንና ትክክለኛ ሃሳባቸውን በይፋ ገለፁ። ለምን?
“በማግስቱ፣ የግለሰብ ነፃነትና መብት ሙሉ ለሙሉ የተከበረባት እንከን አልባ አገር ትፈጠራለች” በሚል ተስፋ አይደለም።
የመንግስት ትክክለኛ ስራ፣ የእያንዳንዱን ሰው የግል መብት ማስከበር ነው ብለው በአዋጅ ስለተናገሩ፣ በማግስቱ እፁብ ድንቅ መንግስት ይፈጠራል ማለት አይደለም።
አይፈጠርም። ነገር ግን፣ እፁብ ድንቅ ሕልም ተፈጥሯል። ቀስ በቀስም፣ እውን ይሆናል።
አስቀያሚና ክፉ የባርነት ልማድ፣ በዓመት በሁለት ዓመት እንደማይወገድ ያውቁ ነበር። ነገር ግን፣ ዘንድሮና በሚቀጥለው ዓመት፣ የተሟላ ለውጥ ስለማይመጣ፣ “ሁሉም ነገር ከንቱ ነው” ብለው አልተቀመጡም።
“ብሩህ የሩቅ ሕልም” በመያዝ ነው፣ ዋና ዋና ችግሮችን መመከት፣ ማሸነፍና ማስወገድ የሚቻለው።
በተፈጥሮው፣ እያንዳንዱ ሰው፣ “የሕይወት፣ የነፃነትና የንብረት መብቶች አሉት”፣ “በዚህም፣ ሁሉም ሰው እኩል ነው” የሚለው ሃሳብ ነው፣ “የአሜሪካ ሕልም” የሚባለው።  ሕልም ብቻ ሆኖ አልቀረም።
በእርግጥም፣ የባርነት ልማድ፣ ከጊዜ በኋላ ተሸንፎ ተወግዷል። የዘረኝነት አስተሳሰብና ዝንባሌም፣ ተዋርዷል። ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል ማለት ግን አይደለም።
ለዚያም ነው፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ “የአሜሪካ ሕልም” ሙሉ ለሙሉ እውን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል ብሎ የራሱን ሕልም የተናገረው። ዛሬና ነገ ባይሳካም፣ ነገና ከነገወዲያ በእንቅፋቶች የታጠረ ቢሆንም፣… ትክክለኛ ሃሳብ የሚነግስበት ዘመን ላይ እንደርሳለን። ካሁን ቀደም ከቀረበው  ፅሁፍ፣ ትንሽ ልጥቀስ።
በፅናት የተያዘ ሕልም፣ እውን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል የሚል ነው - የኪንግ ሕልም። ተዘውትሮ መጠቀስ የሚገባው ነው-ንግግሩና ሕልሙ።
Even though we face the difficulties of today and tomorrow, I still have a dream. It is a dream deeply rooted in the American dream.
I have a dream that my four little children will one day live in a nation where they will not be judged by the color of their skin but by the content of their character.
ሁሉንም ሰው፣ ነጭ ይሁን ጥቁር፣ በግል ተግባሩ፣ እንደየስራው፣ በትክክል የምንመዝንበትና የምንዳኝበት የሥልጣኔ ዘመን ይመጣል።
የወደፊት የሥልጣኔ ዘመንን፣ መጪውን ትውልድ፣ ዛሬ ከወዲሁ፣ በዓይነ ህሊና አማትሮ የሚያይ ነው፤ የአሜሪካ መስራቾች ሕልም። ነፃነትና ፍትህ በሕብር የተጣመሩበት የፍቅር ዘመንን የሚጣራ ነው - በማርቲን ሉተር ኪንግ ንግግር ውስጥ የተገለጠው ሕልም።
እንዲህ አይነት ብሩህ ሕልም፣ ዛሬ ዛሬ ደብዝዟል። በኛ አገርማ፣ ጭላንጭሉ  እንኳ አልደረሰንም። ቢደርሰንም እየተስለመለመ በእጅጉ ጨልሟል። አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ፣ ምናምን የሚል ሆኗል - ቅዠታችን።
ብሩህና መልካም ሕልም ጨልሞብን፣ ጭላንጭሉ ሁሉ ከመጥፋቱ በፊት፣
ያጠላብን ቅዠትም ፈፅሞ ሳይውጠን በፊት፣…
በጥበብና በትጋት ወደ ብሩህ ሕልም ለመጓዝ፣…
 መልካምም ሕልም ለመጨበጥ ካልፈጠንን፣ ነገሩ ሁሉ መላ ያጣል።
እንኳን እንደ ኢትዮጵያ በከባድ ፈተና ውስጥ የሚገኝ አገር ይቅርና፣ በሥልጣኔ የገነኑና ወደ ከፍታ የገሰገሱ አገራትም፣ ሕልም ከጠፋባቸው፣ ወደ ውድቀት መጓዛቸው አይቀርም።
ጥበበኛው ዳንኤል፣ ይህን እውነት ነው፣ ለንጉሥ ናቡከደነፆር የገለጠለት - በትንቢተ ዳንኤል ትረካ ላይ።
የናቡከደነፆር ዘመን፣ ምንም እንኳ በብሩህ ሕልም ወደ አስደናቂ ከፍታ የደረሰ ዘመን ቢሆንም፣… እንደ አጀማመሩ መቀጠል አቅቶት፣ ሕልሙ ጠፍቶበታል።
በረዥምና በፈጣን የሥልጣኔ ግስጋሴ፣ የዓለም ሁሉ አርአያ፣ የታሪክ ሁሉ ቀዳሚ፣… ነበር አገሩና አካባቢው። በያኔው ዘመን፣ “ሱመር”፣ “አካድ” እና “አሶር” የተሰኙት የኢራቅ አካባቢዎች፣ በሁሉም የስልጣኔ እርምጃዎች፣ የታሪክ በኩር በኩር በየመስኩ የወለዱ ያፈለቁ አካባቢዎች ናቸው። መጀመሪያዎቹ ከተሞች፣ ቀዳሚዎቹ ሰማይ ጠቀስ ግንባታዎች፣ ግድብና የመስኖ እርሻዎች፣ ጥንታዊ ትረካዎችና ግጥሞች፣ ጋሪ እና ኪነጥበባዊ ፈጠራዎች፣… በዚያ ምድር አብበዋል።
በዋና ዋናዎቹ የስልጣኔ እርምጃዎች፣ የዛሬው ኢራቅ፣ የታሪክ አንደኛ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜም፣  ወደ ላቀ ከፍታ እየመጠቀ፣  ውጣ ውረድና ወድቆ መነሳት ባያጣውም፣ ለ2500 ዓመታት በስልጣኔ ጎዳና ዓለምን ሁሉ መርቷል።
ክፋቱ፣ የስልጣኔ ብሩህ ሕልም ከጠፋበት በኋላ ግን ቀስ በቀስ ተፍረክርኳል። ሰማይ ጠቀሶቹ ሕንፃዎች በአሸዋ ተቀብረዋል። ከተሞቹ የአፈር ክምር ሆነዋል። ከናቡከደነፆር ዘመን በኋላ፣ የኢራቅ ምድር፣ ለ2500 ዓመታት የውጭ ወራሪዎች የሚፈራረቁባት በረሃ ከመሆኗ የተነሳ፣ ታሪከኞቹ ጥንታዊ ከተሞች ተረስተዋል።
ተረት አለመሆናው የተረጋገጠው፣ ባለፉት 150 ዓመታት ውስጥ፣ በቁፋሮ በተካሄዱ ጥናቶች ነው።
ሕልም ማየት ያነሳል፤  ሕልም ማጣት ይጥላል ይሉሃል እንዲህ ነው።
ደግነቱ፣ እንደ ኢትዮጵያ ሕልም ጠፍቶበት በቅዠት የተረበሸ አገር፣ እንደ አዲስ ባለ ሕልም መሆን ይችላል። ክፋቱ ደግሞ፣ ባለሕልም ነበረ ገናና አገርና ዘመን በአሳዛኝ ሁኔታ ሕልሙ ሊጠፋበት ይችላል።
ለዚህም ነው፣ ንጉሡ፣ “ሕልሜን ሰምታችሁ፣ ትርጉሙን ፍቱልኝ” ብሎ ጠቢባንን ያልጠየቃቸው።
የንጉሡ ትዕዛዝ፣ “ሕልሜን ንገሩኝ፣ ትርጉሙን ፍቱልኝ” የሚል ነበር። ሕልም የጠፋበት ዘመን ነውና። ለዚህ ጥያቄ፣ ትክክለኛ መልስ መስጠት የቻለው፣ ጥበበኛው ዳንኤል ብቻ ነበር።
ሕልሙን ያጣ ዘመን፣ ቅዠት ውስጥ የገባ አገር፣ “መላም የለው”!
“ንጉሥ ሆይ፣ ተኝተህ ሳለ፣ አእምሮህ፣ ወደፊት ሊሆን ስላለው ነገር ያሰላስል ነበር።”… በማለት ይጀምራል- ዳንኤል።
በእርግጥም ናቡከደነፆር፣ አስተዋይ ንጉሥ ነው። አልጨበጥ እያለ አስቸግሮት እንጂ፣ ለማሰብና ለማሰላሰል የሚሰንፍ ሰው አይደለም። ደግሞም፣ የዘመኑ አዝማሚያ ግራ ቢያጋባው አይገርምም። ሕልም የጠፋበት ቅይጥ ዘመን፣ ያምታታል። መያዣ መጨበጫ ያሳጣል። የዘመኑ ዳርዳርታ ባይጠፋውም፣ ሕልሙና መንፈሱ ሁሉ፣ ቅርፁን የሚለዋውጥ ጉም ሆኖበታል። ሕልም የጠፋበት ዘመን፣… የተቀየጠ የደፈረሰ ዘመን ነውና።
ጥበበኛው ዳንኤል፣ የዘመኑን ቅይጥ ሕልም በምናብ ለንጉሡ ሊያሳየው ይሞክራል። ይተርክለታል።
ንጉሥ ሆይ፣… በፊት ለፊትህ፣ ግዙፍ የሆነ፣ አብረቅራቂና ግርማዊ ታላቅ ምስል ቆሞ አየህ።
የምስሉ ራስ፣ ከንጹሕ ወርቅ፣
ደረቱና ክንዶቹ፣ ከብር፣
ሆዱና ጭኖቹ፣ ከነሀስ፣ የተሠሩ ነበሩ።
ቅልጥሞቹ ከብረት፣ እግሮቹም፣ ከፊሉ ከብረት፣ ከፊሉ ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ።
ይህን በመመልከት ላይ ሳለህ፣ አንድ ድንጋይ፣ የሰው እጅ ሳይነካው፣ ተፈንቅሎ ወረደ። ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው። አደቀቃቸውም።
ወዲያውኑም፣ ብረቱ፣ ሸክላው፣ ነሀሱ፣ ብሩና ወርቁ፣ ተሰባበሩ። በበጋ ወራት፣ በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ ገለባም ሆኑ። ነፋስም፣ አንዳች ሳያስቀር፣ ጠራረጋቸው። ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን፣ ታላቅ ተራራ ሆነ። ምድርንም ሞላ።
ሕልሙ ይህ ነበር።
ዳንኤል፣ ሕልም ለጠፋበት ለንጉሥ ናቡከደነፆር፣ “ሕልሙን” ነገረው።
በእርግጥ፣ የዘመኑ ችግር፣ የንጉሡ የግል ጥፋት፣ የግል ድክመት  አይደለም። የዘመኑ አስተሳሰብ ደፍርሷል። አገር ምድሩ ተቀዣብሯል። እናም ፣ ጥበበኛው ዳንኤል፣ “ሕልም ለጠፋበት ዘመን፣ ሕልሙን ነገረው” ብንል ያስኬዳል።
የዘመኑ ቅይጥ ሕልም፣ ምን እንደሚመስል፣ ከላይ እስከ ታች ነገረው።
“ሕልሙ ይህ ነው” ብሎም ደመደመ። ከዚያስ?
“አሁን፣ ትርጉሙን ለንጉሥ እንናገራለን” በማለት የሕልሙን ምስጢር ይገልፅለታል።
ንጉሥ ሆይ፣ አንተ፣ የነገሥታት ንጉሥ ነህ። የሰማይ አምላክ፣ መንግሥትንና ሥልጣንን፣ ኀይልንና ክብርን ሰጥቶሃል። የሰው ልጆችን፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል። በየትም ቦታ ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል። እንግዲህ፣ የወርቁ ራስ አንተ ነህ።
ከአንተም በኋላ፣ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል።
ቀጥሎም፣ በነሀስ የተመሰለው፣ ሦስተኛ መንግሥት ይነሣል። …
በመጨረሻም፣ … ብረት የሆነ አራተኛ መንግሥት ይነሣል።… እግሮቹና ጣቶቹ፣ በከፊል ብረት፣ በከፊል ሸክላ ሆነው እንዳየህ፣ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል።… ከፊሉ ብርቱ፣ ከፊሉ ደካማ ይሆናል።… ብረትና ሸክላ እንደማይዋሐዱ ሁሉ፣ ሕዝቡም በአንድነት አይኖሩም።
በዚያ ዘመን፣… የሰማይ አምላክ፣… እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል።… ያጠፋቸዋል። የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ የወረደውና፣ ብረቱን፣ ነሀሱን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ያደቀቀው ድንጋይ … ትርጓሜ ይህ ነው።
ሕልሙ እውነት ነው።
ትርጓሜው የታመነ ነው።
ጥበበኛው ዳንኤል፣ ለናቡከደነፆር፣ “ሕልሙን ከነትርጉሙ” ገለፀለት።
ባለ ሕልም የነበረ የሥልጣኔ ዘመን፣ ሕልሙ ሲጠፋበት፣… በአንድ ጀምበር፣ እንክትክቱ አይወጣም። ከጊዜ በኋላ ግን አይቀርለትም። ቀስ በቀስ፣ ደረጃ በደረጃ፣… ከወርቅ ወደ ብር ዝቅ ይላል። ከዚያም ወደ ቅይጥ ነሀስ ያሽቆለቁላል።
ይባስ ብሎም፣ በቅጡ ሊዋሐድ የማይችል፣ ከሸክላና ከብረት የተለጣጠፈ ይሆናል። አብሮ መቆየትና ቆሞ መራመድ ያቅተዋል። በተነቃነቀ ቁጥር እየተሰነጣጠቀ፣… ከዛሬ-ነገ ለመፍረስ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅ ይመስላል።
“ብሩህ የሥልጣኔ ሕልም”፣ ከአፈር ተነስቶ፣ ከዓመት ዓመት ይለመልማል፣ ፍሬውም ይበረክታል። ከአፈር ውስጥም፣ ብረትንና መዳብን አንጥሮ ያወጣል። ነሀስን ይፈጥራል። በተጣራ ብርና በንፁሕ ወርቅ ይንቆጠቆጣል። ከአፈር ውስጥ አልማዝና እንቁ እየፈለቀቀ፤ ውበትን ይጎናፀፋል። ከእለት ወደ እለት ጨለማው እየተገፈፈ፣ ከቅይጥና ከድንግዝግዝ ማጥ ውስጥ ወጥቶ እየተሻገረ፣ እየፀዳ፣ እየፈካ፣ እየከበረ ይጓዛል።
ሕልም ሲርቀው ደግሞ፣ ያ ሁሉ ብርሃን እየደበዘዘ፣ ያ ሁሉ ክብር እየቀለለ፣… መጨረሻው ገለባ ይሆናል። ከአፈር ተነስቶ ወደ ሸክላና ወደ ወርቅ እንዳልደረሰ፣ ወደ አፈር ይመለሳል።
በእርግጥ፣ የእለት እለት ውድቀቱ፣ የቀን ከቀን ለውጡ፣ በግልፅ አይታይም። አገር ምድሩ እስኪፈራርስ ድረስ፣ የዓመት ዓመት ልዩነቱን፣ ብዙ ሰዎች ልብ አይሉትም። ልዩነቱ አይታወቃቸውም - ከዳንኤል ጥበብ ካልተማሩ በቀር። ጥበበኞች ግን ያውቁታል - ያስተውላሉና።
ባለ ሕልም የነበረ የስልጣኔ ጅምር፣… ሕልሙ ሲጠፋበት፣ እንደቀድሞው መቀጠል አይችልም።
ያለ ሕልም፣ ለትንሽ ጊዜ ቢጓዝም፣… ቀስ በቀስ፣ ሳይታወቀው፣…
በትንሽ በትንሹ እየተበረዘ፣ ስንዝር በስንዝር እየተንሸራተተ፣
ከስር ከስሩ እየተሸረሸረ፣ ውስጥ ለውጥ እየተቦረቦረ፣…
ለተወሰነ ጊዜ ቢቀጥልም፣… ወርዶ ወርዶ የሆነ ደረጃ ላይ ሲደርስ ግን፣…
ይንኮታኮታል። ትንሽ እንቅፋት ይበቃዋል።
የሰው እጅ ያልነካው ድንጋይ ድንገት ሲመታው፣ እንክትክቱ ይወጣል።
ይሄ፣ አይቀሬና ዘላለማዊ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ከመጽሐፈ ሄኖክ ጋር የተቀራረበ አገላለፅን ከተጠቀምን ደግሞ፣ ዘላለማዊውን የተፈጥሮ ሕግ፣ “ለዘላለም ፀንቶ የሚኖርና የማይዛነፍ የአምላክ ሥርዓት” እንለዋለን።
ከእውቀት የፈለቀ፣ ከመልካምና ከብሩህ ሕልም የተፀነሰ፣…
ከዚያም በጥበብ፣ በትጋትና በፅናት የተወለደ የሥልጣኔ ቡቃያ፣…
ያለ ሕልም፣ ብዙ አይቆይም።
ሕልሙ ሲጨልም፣ የሥልጣኔ ጅምር ይጠወልጋል፣ ይደርቃል፣ ይረግፋል። ተመልሶ አመድ ይሆናል።
ይሄ፣… ጨርሶ የማይናወጥ የተፈጥሮ ሕግ ነው - ዓለምን ሁሉ እንደሚሞላ ግዙፍ አለት።
አሳዛኙ ነገር፣ አገራዊ ሥርዓትና ባሕል፣ ዓለማቀፋዊ አስተሳሰብና ቅኝት፣… አንድ ሁለት ሰዎች በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሚገነቡት ነገር አይደለም። ተበላሽቶ ሲፈራርስም፣ በአንድ ንጉሥና በአንድ ጥበበኛ ጥረት ብቻ፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ተጠግኖ አይድንም። ከአጭር ጊዜ አንፃር ሲታይ፣ “በሰው ሥልጣን ስር አይደለም” ያስብላል።
በረዥም ጊዜ ግን፣ “ይቻላል”።
 ከአፈር ተነስቶ፣ እንደገና፣ የሥልጣኔ ቡቃያን መትከልና ማፅደቅ፣…
ቀስ በቀስም ማሳደግና በሰፊው ማልማት፣ በዓመታት ጥረትም፣ ዓለምን እንዲያሳምር፣ ሕይወትን እንዲያለመልም ማድረግ ይቻላል።
 “መልካም ብሩህ ሕልም” ማለትም ይሄው ነው።
“ብሩህ ሕልም”፣ ከአፈር ውስጥ ወርቅን ፈልቅቆ ያወጣል።
የሥልጣኔ ሕልሞችና የጥበብ እጆች፣ “አፈርን ወደ ወርቅ ይቀይራሉ” ብንል፣ ቅንጣት አልተጋነነም። በረዥም ጊዜ አሻግረው ሲመለከቷቸው፣ ሥልጣኔና ብልፅግና፣ አገራዊ ሥርዓትና ባሕል፣… “በሰው ሥልጣን ስር ናቸው”።
ሕልም የጨለመ ጊዜ ግን፣… አገራዊ ባሕልና መንግሥታዊ መዋቅር፣ ሕግና ሥርዓት፣ ሥልጣኔና ብልፅግና፣… ቀስ በቀስ ይመነምናሉ፣ ይንኮታኮታሉ - “ለጊዜው፣ ከሰው ሥልጣን ውጭ ይሆናሉ” (ከኀያሉ ንጉሥ ከናቡከደነፆርና ከጥበበኛው ከዳንኤል ቁጥጥር ውጭ ሆነዋል´ኮ- ለጊዜው)።
አገራዊ ባሕልና ሥርዓት፣ ዓለማቀፋዊ አስተሳሰብና ቅኝት ሲበላሹ፣… “ሕልም በጠፋበት ዘመን”፣ ለጊዜው መላ አይገኝላቸውም።
ንጉሡ፣ ይህን ዘላለማዊ እውነት ለማወቅ፣ ዳንኤል ስለረዳው፣ ያመሰግነዋል። ጥበበኛውን ያከብረዋል።
…”ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ በግንባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት። አከበረውም” ይላል - ትረካው።
ናቡከደነፆርና ዳንኤል፣ ይህን እውነታ ተገንዝበዋል። የማኅበረሰብን ሥርዓትና የታሪክን ሂደት፣ በቅጡ ተረድተዋል። ለጊዜው፣ ምንም መፍትሔ እንደማይገኝለት ገብቷቸዋል። ሕልም ለጠፋበት ዘመን፣ መልካምና ብሩህ ሕልም ለመያዝ መፍጠን፣ ሕልሙን እውን ለማድረግ በፅናት መትጋት እንጂ፣ ከዚህ ውጭ፣ ዘላቂ መፍትሔ የለውም።
የዘመናችን እና የአገራችን መንፈስም፣ ከብሩህ ሕልም በስተቀር፣ ከጨለማ የሚያወጣ መፍትሔ አይገኝለትም። ለጊዜው፤ ሕልም ጠፍቶብናል። ቅዠት አብዝተናል። ራሳችንን እየጠየቅን ማረጋገጥ እንችላለን።
“የእውነት ብርሃንን፣ የትጋት መንገድን፣ የክብር ሕይወትን አሟልተን”፣ ብሩህ አላማዎችን ይዘናል?
የእያንዳንዱን ሰው ሃሳብና ንግግር፣ እቅድና ተግባር፣ ብቃትና ባሕርይ፣… በቅንነት መርምረን እንፈርዳለን?
እውነትንና ውሸትን፣ ጠቃሚንና ጎጂን፣ መልካምነትንና ክፋትን በጥንቃቄ እየለየን፣ በሃቅ እንመዝናለን?
እያንዳንዱን ሰው በግል ተግባሩና በግል ብቃቱ በትክክል እንዳኛለን?
ወይስ በምቀኝነትና በቲፎዞ ጩኸት፣ በዘረኝነትና በጅምላ፣ በጭፍን ስሜትና በሃይማኖት ተከታይነት?
ምንም አያጠራጥርም። ከሕልም ርቀናል። ቅዠት አዘውትረናል።
መልካም ብሩህ ሕልም ብንይዝ ነው የሚበጀን።
ደግሞስ፣ ከዚህ ውጭ፣ የትኛው አይነት “አገራዊ መግባባት”፣ እውነተኛ እና ጤናማ መግባባት ሊሆን ይችላል? ሊሆን አይችልም።


Read 10603 times