Saturday, 02 July 2022 17:09

የጋዜጣ የህትመት ዋጋ ከእጥፍ በላይ ሆኗል- ዓመት ባልሞላ ጊዜ፡፡

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 • መንግስት፣ ለጋዜጦች ሕትመት፣ የታክስ እና የታሪፍ ጫናዎችን ለመቀነስ ቃል ገብቶ ነበር (2012 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው                  የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ)፡፡
          • የጋዜጦች ሕትመት ሳይቋረጥ በፊት፣ መንግስት ካቻምና የገባውን ቃል ዛሬ ተግባራዊ ካላደረገ፣ለመቼ ነው?


             በጥቂት ወራት ውስጥ፣ የሕትመት ዋጋ ከአጥፍ በላይ አሻቅቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት ብቻ፣ የጋዜጦች የህትመት ዋጋ ከ60 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡ ከዚያ በፊትም  በየወሩ በተከታታይ የሕትመት ወጪያቸው አሻቅቧል፡፡
ከ10 እስከ 12 ብር በሆነ ሂሳብ ሲታተም የነበረ ጋዜጣ፣ አሁን ከ24 እስከ 28 ብር የሕትመት ዋጋ ተጭኖበታል፡፡ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ከእጥፍ በላይ የሕትመት ዋጋ የከበደባቸው ጋዜጦች፣ ከሳምንት ሳምንት የመሻገር አቅም አጥተዋል።
የአከፋፋይና የአዟሪ ወጪዎች ሲጨመሩበት፣ አንድ ጋዜጣ ለማሳተምና ለአንባቢ ለማቅረብ፣ ከ30 እስከ 35 ብር ወጪ  ይጠይቃል፡፡ የባለሙያ ደሞዝ፣ የቢሮ ኪራይ፣ የስራ ማስኬጃ ወጪዎች ሁሉ ሳይታሰቡ ነው።
ታዲያ በዚህ አይነት ሁኔታ፣ የጋዜጦች ሕትመት እንዴት ሊቀጥል ይችላል? ሊቀጥል እንደማይችል በመገንዘብ ነው፣ መንግስት በሕትመት ዙሪያ ያሉ የታክስ እና የታሪፍ ጫናዎችን ለመቀነስ ቃል የገባው፡፡ ይህም፣ ከሁለት ዓመት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት  የፀደቀው  የመንግስት ፖሊሲ ውስጥ፣ ቃል በቃል ሰፍሯል፡፡
እስካሁን ግን ተግባራዊ አልሆነም። በጣም ዘገየ፡፡ የጋዜጦች የህትመት ወጪና ሸክም፣ አሁን የመጨረሻ ጫፍ ላይ ደርሷል። ጥናት፣ ውይይት፣ ደብዳቤ መላላክ በሚል፣ ጉዳዩ ይዋል ይደር ከተባለ፣ “የዘገየ እንደተነፈገ ይቆጠራል” እንዲሉ፣ ያኔ ጋዜጦች አይኖሩም፡፡ እና ምን ይሻላል?
ለጊዜው፣ ሳይውል ሳያድር መንግስት ሊያደርጋቸው በሚችላቸው ነገሮች ላይ፣ በፍጥነት ውሳኔ መስጠት ይችላል፡፡ ሌሎች አማራጭ መንገዶች ላይ ውይይትና ጥናት ማካሄድ ጠቃሚ ቢሆንም፣ እስከዚያው ድረስ፣ ጊዜያዊ መፍትሔዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፤ ተገቢም ነው፡፡
 ቋሚ ውሳኔ  እስኪመጣ ድረስ፣ ለጊዜው የጋዜጣ ሕትመት ቁሳቁስና ስራዎች ላይ፣ የጉሙሩክ ታሪፎችን ማንሳት፣ የቫት ታክሶች ላይ እፎይታ መስጥት፣ እንዲሁም ተዛማጅ መፍትሔዎችን ሳይውል ሳያድር መተግበር ይችላል፡፡ ካስፈለገም፣ ውሳኔው የጊዜ ገደብ ቢኖረው፤ ለዓመት ተኩል ወይም ለሁለት ዓመት ብቻ የሚገለግል ቢሆን፣ ጉዳት አያመጣም፡፡
በዚሁ ጊዜ ውስጥ፣ በጥናቶችና በውይይቶች፣ አማራጭ መፍትሔዎችን የማበጀት እድል ይፈጠራል፡፡ ጋዜጦችም፣ ችግሮችን የመቋቋም አቅም ለማደራጀትና የሚያዘልቁ የአሰራር መንገዶችን ለመክፈት የሚረዳ ጊዜ ያገኛሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ በተለያየ ሚዲያ ማስታወቂያዎችን የሚያሰራጩ የመንግስት ተቋማት፣ ቋሚ አሰራ እስኪፈጠር ድረስ፣ ለጊዜው የግል ጋዜጦችን ያላገለለና በተወሰነ መቶኛ በትንሹ ያካተተ አሰራር እንዲጀምሩ ማድረግ ይቻላል፡፡

Read 13506 times