Saturday, 13 October 2012 10:37

ለ40/60 ቤቶች ምዝገባ የወረዳ ማስረጃ አያስፈልግም ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(10 votes)
የምዝገባው ጊዜ በቅርቡ ይፋ ይደረጋልየስምምነት ሰነዱ ከትናንት በስቲያ ተፈርሟል

የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ ይረዳል በሚል በአዲስ አበባ ከተማ በአስር ሺህ ቤቶች ይጀመራል ለተባለው የ40/60 ቤቶች ምዝገባ፣ ቤት እንደሌለም ሆነ የጋብቻ ሁኔታን የሚገልፅ ማስረጃ እንደማያስፈልግ፣ ንግድ ባንክም ይህንን ማስረጃ የመጠየቅ ሥልጣን እንደሌለው ተገለፀ፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ መሀሪ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የቁጠባ ምዝገባውን ለማድረግ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን እያሟላን ባለንበት ወቅት ምዝገባ ሊጀመር ነው በሚል የተሳሳተ መረጃ አማካኝነት በርካታ ሰዎች ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውን ሰምተናል፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩ ለቁጠባ  ምዝገባው ያወጣው የተለየ መስፈርት የሌለ ከመሆኑም ባሻገር ባንኩ እነዚህን ደንበኞች እንዲያቀርቡ ይገደዳሉ ተብሎ የተገለፁትን እንደጋብቻ ማስረጃና ቤት የሌለው መሆኑን የሚገልፁ መረጃዎች የመጠየቅ ሥልጣን የለውም ብለዋል፡፡

ባንኩ ደንበኞቹን እንደማንኛውም የቁጠባ ሂሣብ ተጠቃሚ የሚቀበልና የሚመዘግብ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ለ40/60 ቤቶች ልማት ፕሮግራም የተለየ የቁጠባ መስፈርት ያልወጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የምዝገባ ጊዜው መራዘሙን አስመልክተው ሲናገሩም “እኛ ምዝገባ የምንጀምረው የቁጠባ ልማት ቤቶች ኢንተርፕራይዝ” ምዝገባ እንድንጀምር ትዕዛዝ ሲሰጠን ነው፡፡ በዚህ ወቅትም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን  ይፋ በማድረግ ምዝገባ እንጀምራለን፡፡ ምዝገባው ለሁለት ቀናት ተካሂዶ ይጠናቀቃል የተባለው ጉዳይም ከእኛ እውቅና ውጪ የሆነና ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የኮሚኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ  አቶ ተስፋ አለማየሁ፤ የምዝገባ ጊዜ መራዘሙን አስመልክተው ሲናገሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዙ ከትናንት በስቲያ የስምምነት ሰነዱን የፈረሙ ሲሆን ከዚህ በማስከተል በሚወጡ የምዝገባ ጊዜያትና የአሠራር ሂደቶች መመሪያዎች አማካኝነት በቅርቡ ምዝገባው ይጀመራል ብለዋል፡፡ ከወረዳ ይፈለጋሉ ስለሚባሉ መረጃዎችና የምዝገባ መስፈርቱን በተመለከተም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ንግድ ባንክን በመሆኑ እሱ በሚያወጣው መመሪያና መስፈርት መሰረት ለቁጠባ ደንበኝነት ምዝገባውን ያካሂዳል፡፡ እስከአሁን ባለው አካሄድ ግን የቀበሌ (የወረዳ) ማስረጃዎች አያስፈልገውም ብለዋል፡፡ የአንዳንድ ወረዳዎች ነዋሪዎች የጋብቻ ማስረጃዎችና ቤት የሌላቸው መሆኑን የሚገልፅ ማስረጃ ለማግኘት ገንዘብ እየከፈሉ እንደሚወስዱ መስማታቸውንና ይህም አግባብነት የሌለው አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለ40/60 ቤቶች ምዝገባ ዋንኛ መስፈርት ነው የተባለውን ቤት የሌለው መሆኑን የሚገልፅና የጋብቻ ሁኔታን የሚያስረዳ መረጃ ለማግኘት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለሰዓታት ሠልፍ በመጠበቅ መጉላላታቸውን የጠቆሙት የከተማዋ ነዋሪዎች፤ በሥፍራው ለዚሁ ተግባር ለተሰማሩ ደላሎች እስከ ብር 500 በመክፈል ወረፋ ለማግኘትና መረጃውን ለመውሰድ ጥረት ሲያደርጉ መሰንበታቸውን ገልፀዋል፡፡ የ40/60 ቤቶች ልማት ምዝገባ በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን እንደሚገለፅና ምዝገባው የሚካሄደው በይፋ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪውም ሁኔታውን በትዕግስት እንዲጠባበቅ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ አባይነህ መሀሪ አስገንዝበዋል፡፡

 

Read 4055 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 10:50