Saturday, 25 June 2022 20:39

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቴዲ አፍሮ እና “ሐ”
                                 ማዕረግ ጌታቸው


           ቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) ለመጀመሪያ ጊዜ ላገኘው ነው፡፡ የግቢው በር ተከፈተ፡፡ ጥቁር ቲ-ሸርት በቁምጣ ሱሪ ለብሶ አንዲት ክፍል በር ላይ ታየኝ። ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ “ሐ” ትባላለች አለኝ። የምተዋወቀው ነገር ባጣ ዞር አልኩ። የክፍሏ ስም እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ወደ “ሐ” ዘለቅሁ። የቴዎድሮስ ካሳሁን የግል ቤተ-መቅደስ ይች ናት፡፡ ውስጧ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቃላማ ብዛት ተሞሽሯል። በተረፈው ቦታ የነገስታቱ  ምስል አርፏል። የተቀመጠበት ስፍራን ቀና ብዬ ተመለከትኩት፡፡ የእናትና አባቱ ፎቶ፣ ግራና ቀኝ ከእሱ ከፍ ባለ ትይዩ ላይ ተለጥፏል፡፡
“ይች ናት እንግዲህ የስራ ቦታችን” አለኝ፡፡ “ሐ” ለምን ተባለች አልኩት፡፡ ብዙ ትርጉም አለው፡፡ ቀላሉ ግን የአንድነት ምልክት መሆኗ ነው ሲል መለሰልኝ፡፡ “ሐ” በቁሟ “ሐ”ንም “ለ”ንም አቅፋለች፡፡ ስትገለበጥ ደግሞ ሌላ ፊደልን ትሰጣለች፡፡ “ሐ” እንደ ኢትዮጵያ አንድም ብዙም ናት፡፡
ስለ ኤልያስ መልካና እሱ ወዳጅነት ለማውራት ብሄድም፣ በቀጥታ ወደ ጉዳዬ መግባት አልፈለኩም፡፡ አንድ ነገር ገርሞኛል አልኩት፡፡ ጠየቀኝ፡፡ የምታዜማትና የምትኖርባት ኢትዮጵያ ይመሳሰላሉ ስል መለስኩለት፡፡ ግራ ተጋብቶ ይሆን ብዬ ማብራሪያዬን ቀጠልኩ፡፡ ብዙዎች የሚናገሩትን አይኖሩም፡፡ የሚኖሩትን አይናገሩም፡፡ ያንተ ኢትዮጵያ ግን ለማለት ያህል የምትልላት ብቻ ሳትሆን በጥበብ መቅደስህ “ሰዓታት” የምትቆምላት፣ “ወረብ” የምታቀርብላት፣ ዜማ የምታሰማላት ትመስላለች አልኩት፡፡
እውነት ነው፡፡ እኔ የቴዎድሮስ ካሳሁን ሥራዎች ላይ  ሒስ ከሚሰነዝሩ ወገን ነኝ። አገሩን የሚረዳበት መንገድ ላይም ልዩነት አለኝ፡፡ ግን በእሱ ልክ የማምንባትን ኢትዮጵያ የልቤ ሙዳይ አላደረኳትም፡፡ በእሱ መጠን አገሬን ልሰራት አልባተልኩም፡፡ ይህ የእኔ ብቻ ሳይሆን የእኔ ትውልድ መልክ ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንወዳታለን የምንለውን ሩብ ብንኖርላት፣ አሁን የገባንበት የጽልመት መንገድ ውስጥ ባልገባን፡፡  
የቴዎድሮስ ካሳሁንን መንገድ ሳስብ ህንዳዊው ከያኒ ታጎር ትውስ ይለኛል፡፡ ታጎር ሕንድን የሰራ የጥበብ አርበኛ ነው፡፡ ሲያሻው እየፃፈ ሲያሻው እየተቀኘ፣ የህንድን አገራዊ ብሄርተኝነትን መርቷል፡፡ ሕንድን እሱ ባሰበው መንገድ አዋልዷል፡፡ ስለ ታጎር ማንነት ብዙ ቢጻፍም እኔ ግን የሙዚቃ ግጥሞቹ ውስጥ የተደበቀ ሰው አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡
የቴዎድሮስ ካሳሁን መንገድም ከዚህ ብዙ አልራቀም፡፡ የሚመኛትን ኢትዮጵያ ጎጆው ውስጥ ቀልሶ  እሷኑ አገር ሊያደርግ ይባትላል፡፡
ይገባኛል! የቴዎድሮስ ካሳሁንን ኢትዮጵያ ሁሉም ሰው ሊወዳት አይችልም፡፡ ይሁንና ሩብ ምዕተ ዓመት በተጠጋ የሙዚቃ ሕይወቱ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ሆኖ ብዙ ተጉዟል፡፡ አንድም ብዙም ሁኖ ለወደዳት አገር ተፋልሟል፡፡ ብዕር የጨበጠ ጄነራል ሆኖ አዕላፍትን እየመራ ከአደባባይ ተሰይሟል፡፡
ከባድ በሚባሉ ወቅቶች ሳይቀር ነፍሱን አሲይዞ ከአገሬ አልወጣም እንዳለ እኔ ምስክር ነኝ፡፡ በዛ አስጨናቂ ሰዓት በሩ ላይ ያሉትን የግቢውን ጥበቃ እየተመለከትኩ፤ #መንግስት ለአንተ ሳይሆን ለራሱ ሲል ጥበቃ መመደብ እኮ አለበት፤; አልኩት፡፡ ምላሹ ቢያስደነግጠኝም፣ አሁንም ድፍረቱን ሳስብ ያስገርመኛል፡፡....
N.B “ናዕት” የተሰኘ አዲስ ሥራውን ተንተርሶ ለምንድነው ስለ ቴዎድሮስ ካሳሁን ስንኞች ትንታኔ የማትጽፈው? ብላችሁኛል። ጊዜው ሲፈቅድ እንደምመለስባቸው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

____________________________________________________

                    ግልገል ሱሪ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ገባ?
                           አሌክስ አብርሃም


               አውቶሞቢል፣ ስልክ፣ አውሮፕላን፣ ሲኒማ፣ የውሃ ቧንቧ እንዲሁም ሳይክል  ፖስታ ... ወዘተ የመሳሰሉት የስልጣኔና ዘመናዊነት መገለጫዎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት መንገድ ላይ ብዙ አጨቃጫቂ ትርክቶች ይነሳሉ፡፡ የአድዋ በዓል በተቃረበ ቁጥር አንዱ የሚያንገሸግሸንም ይሄው ንትርክ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ሁሉንም ብሔር ሳያስቀይም ወደ ኢትዮጵያ የገባ ነገር ምን ይሆን?  ብሎ የሚጠይቅ ሰው ካለ መልሱ እነሆ፡- ቡታንቲ (ግልገል ሱሪ) ነው!  
እንግዲህ አዶላ የወርቅ ማእድን ማውጫ ሲባል ሰምታችኋል … እና  በጃንሆይ ዘመን (በየትኛው ጃንሆይ እንደሆነ እንጃ) ስራው ዝርክርክ ከማለቱም በላይ  የሚገኘውም ወርቅ ከሰራተኞች ደመወዝ አላልፍ አለ! በዛ ላይ ወርቁ እንደ ጉድ እየተሰረቀ ከተማ ሲቸበቸብ፣ ወደ ጎረቤት አገርም በኮንትሮባንድ ሲሻገር  በግልፅ ይታይ ነበር።  ንጉሱ በዚህ ነገር ተበሳጩና ሰጥ ለጥ አድርጎ ያስተዳድርልኛል ያሉትን   ፊታውራሪ/ቀኛዝማች ወላ በጅሮንድ  ማንትስ አስተዳዳሪ አድርገው ሾሙ፡፡ እውነትም ስራው ተሳለጠ፡፡ አዲሱ አስተዳዳሪ ጥበቃውን አሻሻሉ …ፍተሻውን አዘምነው ዝንብ እንኳን የያዘችውን  ቆሻሻ ሳታራግፍ የማታልፍበት ቦታ አደረጉት፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው …አሁንም የወርቅ ስርቆቱ ሊቆም አልቻለም …አስተዳዳሪው ግራ ገባቸው ….ጥበቃዎቹን ሁሉ ጠሩና፤
‹‹ምንድነው ነገሩ …እንዴት እንዴት ነው ይሄ ወርቅ የሚወጣው? …መንፈስ አለ እንዴ እዚህ ግቢ ሳይታይ የሚያግዝ?… እናንተስ ወርቁ እንዴትና በማን  እንደሚወጣ ማወቅ  የተሳናችሁ ስለምንድነው?..›› ቢሉ በቁጣ  
‹‹አይ ጌታዬ እሱስ በማንም እንዴትም እንደሚወጣ ደርሰንበት ነበር …ግን ….››
‹‹ግን ምን…?›› አሉ አስተዳዳሪው። ጥበቃዎቹ በሃፍረት እየተሽኮረመሙ አቀረቀሩ፡፡
‹‹ምን ያሽኮረምማችኋል? …በሉ እናንተኑ  እግር ከወርች ሳልቀፈድዳችሁና በጅራፍ ጀርባችሁን ሳላስሞሸልቀው  ተናገሩ!…››
‹‹አይ ጌታዬ ወርቁን የሚያወጡት ሴት ሰራተኞች ናቸው … ግን እንዳንፈትሻቸው …አጉል ቦታ ነው የሚደብቁት … እንግዲህ ሴትን  ልጅ እንዳዋላጅ እግሯን  ፈልቅቀን ወርቅ አናዋልድ ነገር ተቸገርነ›› አሉ፡፡ አስተዳዳሪው ገባቸው ….ሴቶቹ ወርቁን የማይፈተሽ ነገራቸው ውስጥ በጨርቅ እየቋጠሩ ይደብቁና ይዘው ይወጣሉ፡፡
ታዲያ አስተዳዳሪው መላ ዘየዱ …ሰራተኛው ስራ እንደገባ ረዥም ቦይ አስቆፈሩና ቦዩን በውሃ አስሞሉ… እንግዲህ ሁሉም ሰራተኛ በቦዩ በኩል እየዘለለ ማለፍ አለበት …በተለይ ሴቶቹ …. ያው የዛን ቀን ብቻ ከመቶ  በላይ ቦጭረቅ የሚሉ ድምፆች ተሰሙ፡፡ ቦዩን ሲዘሉ አጉል ቦታ የደበቁት ወርቅ ውሃው ላይ እየወደቀ፡፡ እንዴት ይሄ ሊሆን ቻለ? ለሚል መልሱ  በዘመኑ ቡታንቲ አልነበረም፤ አይታወቅም ነው!
እንግዲህ አንድ ብልጣብልጥ የየመን ነጋዴ በሚስጥር ቡታንቲ ማቅረብ ሳይጀምር አይቀርም ነው ተረኩ፡፡ በልዋጩ ወርቅ ሳይቀበል አልቀረም፡፡ ዛሬ እንደፈለጋችሁ ስታጠልቁት ቀላል ይመስላችኋል... ቡታንቲ በሃርድ ከረንሲ ያውም በዘመኑ ወርቅ የገባ ቅርስ ነው፡፡
ከወራት በኋላ ቦጭረቅ የሚለው ድምፅ ጠፋ … ወርቁ ግን መሰረቁ አላቆመም … በዚህ ምክንያት አስተዳዳሪው ከቦታቸው ተነሱ። እንደውም ማዕረጋቸውን ተገፈው ግዞት ተላኩ … ታዲያ እኒህ ሚስኪን ሰው እድሜ ልካቸውን አዕምሯቸው ተነክቶ ‹‹ቦጭረቅ›› ሲሉ ኖረው ሞቱ፡፡  ሲሞቱ አስለቃሽ እንዲህ ገጠመች ይባላል፡-
የመን ሴቱን ሁሉ ቡታንቲ አለበሰው
ሁሌ ቦጭረቅ የለም ንገሩት ለዛ ሰው
ቡታንቲ እንዲህ ወደ አገራችን ገባ እላችኋለሁ… ይሄንንም ታሪክ ብላችሁ ብታወሩ የለሁበትም! በትንሽ ወለብታ ታሪክ እንዲሁ ዘና እንልበት ዘንድ የተፃፈ ፈጠራ ነው! እደግመዋለሁ ፈጠራ ነው!

___________________________________________

                       ሰው ሲፈጠር ድሮ ነበረ ዝንጀሮ


            ብለው ሲናገሩ ሰማኋቸው እንጂ አልሰማ አይል ጆሮ
ልመናቸው እንዴ ንገሪኝ እስኪ አንቺ
እንዴት ነበር ያኔ ስትመለከቺ
እንዴት ነበር ሄዋን የአዳም ተፈጥሮ
አዳምን ስታይው ሲነቃ ከእንቅልፉ
ይጫማ ነበረ በሁለት መዳፉ
........
በለመለመው መስክ በገነቱ ስፍራ
ስትንሸራሸሩ ነበረው ወይ ጭራ
አይተሽዋል ሲሄድ እንዳጎነበሰ
የታለ ጎፈሩ ከወዴት ደረሰ
አዳም እንዴት ነበር ስትሰጪው ፍሬ
ልወቅ ማንነቴን በይ ንገሪኝ ዛሬ
ብዬ ብጠይቃት ለማወቅ ጓጉቼ
የሉሲን ቅድመ አያት ሔዋንን አግኝቼ
አሁን ብታረጅም ብትሆንም ጨርጫሳ
እንዲህ ነበር አለች፣ የያኔውን አስታውሳ
.........
ባለቤቴ አዳም በብርሃን ነበር ጸጋ እንደለበሰ
በኋላ ግን እባብ እያለሳለሰ
አራት እግር ያለው ባለ ረጅም ጭራ
ባልሽ ዝንጀሮ ነው በጣም የሚያስፈራ
ብሎ የነገረኝን ለማወቅ ጓጉቼ
ከዛ ያልታዘዝኩትን በለሷን በልቼ
ያኔ አስታውሳለሁ ያየሁትን አዳም
ወዝ ያለው ሰው እንጂ እንስሳ አልነበረም
...........
ዘንድሮ እናንተ በኃጢአት አድፋችሁ
ይገርመኛል እኔ ሰው ነኝ ማለታችሁ
ሰውስ ድሮ ቀረ የሚኖር በጸጋ
ዘንድሮ ነው እንጂ ሁሉ የተቀየረ በዝንጀሮ መንጋ።
(ሜሮን ጌትነት)



____________________________________________


                   በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር


             በ1947 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በአሰላ ከተማ የተወለዱት ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ መኮንንን፣ ታሪክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ  ሴት ፕሮፌሰር አድርጎ መዝግቧቸዋል። በአባታቸው የፖሊስ መኮንነት ሙያ ምክንያት በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ያደጉት ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ እና በጎጃም ፍኖተ ሰላም ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ነበር ያጠናቀቁት።
ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ በተማሪነት ዘመናቸው ለሳይንስ ትምህርት ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው ሲሆን ከክፍላቸው ከፍተኛውን ውጤት የሚያስመዘግቡ ቁንጮ ነበሩ። ሁለት የክፍል ደረጃዎችን ጭምር በአንድ ዓመት በማጠናቀቅ በ16 ዓመታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለመቀላቀል መብቃታቸውን የህይወት  ድርሳናቸው ያሳያል።
የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው በረዳት መምህርነት እዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲያስተምሩ ቆይተው፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በእንስሳት ጥናት/zoology/  በትምህርት ዘርፉ በድህረ ምረቃ ፕሮግራም፣ የመጀመሪያዋ ሴት ተመራቂ በመሆን አጠናቀዋል።
ቀጥሎም ጀርመን ወደ ሚገኘው ሃይደልበርግ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በፊዚዮሎጂ ትምህርት ዘርፍ በተለይም የሆርሞኖች ስነ ህይወት ላይ በማተኮር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ወደ ሀገራቸው  በመመለስም በስነ ህይወት ትምህርት ክፍል ውስጥ በረዳት ፕሮፌሰርነት እና በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ሰርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በነበራቸው  ቆይታ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማጤን፣  በጥር 2001 ዓ.ም የሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው የሥነ ህይወት ተመራማሪ  የሆኑት ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ መኮንን፣ የዛሬ 14 ዓመት በትምህርትና በተመራማሪነት ያገኙት የፕሮፌሰርነት ማዕረግ፣ ከኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ያደርጋቸዋል፡፡
በቤተሰባዊ ህይወታቸው የሁለት ልጆች እናት እና የሁለት ልጆች አያት የሆኑት ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ፤ የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍን ለወንዶች የሚያስቀድመውን ዘልማድ የተሻገሩ ጠንካራ ሴት ናቸው።
ከፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ መኮንን አበርክቶዎች ዋና ዋናዎቹ፡-
*በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በጣም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት፣ ከቀ.ኃ.ስ እጅ የክብር ሽልማት ተቀብለዋል።
*በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሴቶች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማህበረሰብ እንዲጠነሰስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
*ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የወርቅ ሜዳሊያ እና ሰርተፍኬት ተሸላሚ
*በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ ህይወት ትምህርት ክፍል ኃላፊ
*የአክሊሉ ለማ ፓቶባዮሎጂ ተቋም ዳይሬክተር
*በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የስነ-ጾታ ቢሮ ኃላፊ
*በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለ36 ዓመታት በመምህርነት፣ በትምህርት ክፍል ኃላፊነት እና ተመራማሪ
*የ2007 ዓ.ም ምርጥ ሴት ሳይንቲስት፣ የአፍሪካ ህብረት የክዋሜ ንክሩማህ ሳይንሳዊ ሽልማትአሸናፊ
*የተለያዩ ሳይንሳዊ ተቋማት አባል፣ መምህር እና ኃላፊ
*ከዓለም አቀፉ የገጠር መልሶ ግንባታ የላቀ አፈፃፀም ተሸላሚ
*የአሌክሳንደር ቮን ሀምቦልድ ፋውንዴሽን ተሸላሚ
*በእርሻ ሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ልማት ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት አስተባባሪ
*የኢትዮጵያን ሳይንስ አካዳሚ መስራች እና የቦርድ አባል ሆነውም አገልግለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በዓለምአቀፍ ደረጃ ከተለያዩ የሳይንስ ተቋማት ጋር በመተባበር 92 ሳይንሳዊ የምርምር ጹሁፎችን በማበርከት እና መሰል ተመሳሳይ የላቀ አበርክቷቸው ተምሳሌት የሚሆኑ ተመራማሪ ናቸው፡፡







Read 1993 times