Saturday, 25 June 2022 18:32

ዳሽን ባንክ “ቲር ስሪ” የተሰኘ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል አስመረቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ማዕከሉን ለማደራጀት 230 ሚ. ብር ፈጅቷል
                                  
            ዳሽን ባንክ በአይነቱ የተለየና በግል ባንኮች ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነውን “Tier lll” የተሰኘ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል ሐሙስ ረፋድ ላይ በዋና መስሪያ ቤቱ አስመርቆ ስራ ጀመረ። ይህን የመረጃ ማዕከል ለማደራጀት ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉም ተገልጿል።
መረጃ ማዕከሉ “ህዋዌ ፊውዥን 2000” በተሰኘ ቴክኖሎጂ የተዋቀረ ሲሆን ከፍተኛ ሀይል ያላቸውን ከ1 ሺህ ያላነሱ ሰርቨሮችንና ሌሎች ተያያዥ የኔትወርክ መሳሪያዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው መሆኑን የዳሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ተናግረዋል።
የመረጃ ማዕከሉ በአካባቢው የሚስተዋሉ የተለያዩ ክስተቶችን በመለየት ለማዕከሉ ዋና መቆጣጠሪያ ክፍል መረጃ ማስተላለፍ የሚችል ከመሆኑም በላይ፣ ችግር ሲከሰትም ችግሩን በመለየት ስጋቶችን እስከማስቀረት የሚደርስ ዓለማቀፋዊ ደረጃውን በጠበቀ ቴክኖሎጂ የተዋቀረ ነው ተብሏል።
ቴክሎጂው በዓለም ላይ ከታች ወደላይ እያደገ ቲር 1 “፣ ቲር 2፣ ቲር 3 እና ቲር 4 ላይ የደረሰ ሲሆን ዳሽን ያስገነባው ሶስተኛ ደረጃውንና በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ሊገነባ የሚችለውን መሆኑም ተነግሯል።
ዓመቱን ሙሉ 99.98 በመቶ ባንኩ ከአገልግሎት ሳይቋረጥ መቀጠል የሚያስችለውን አሰራር የሚያሳልጥ ሲሆን በዓመት ውስጥ ባንኩ ለ95 ደቂቃ ብቻ ከአገልግሎት ውጭ እንደሚሆን ተገልጿል። መረጃ ማዕከሉ ሲገነባ ከዳሽን ባንክ ባሻገር ለሌሎች ባንኮችና ለፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ይሰጣል የተባለ ሲሆን ይህም ማለት ሌሎች ባንኮችና የፋይንስ ተቋማት ሰርቨሮቻቸውን አምጥተው በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስቀምጡበትንና የሚጠቀሙበትን መሰረተ ልማት (ቦታ) ማዘጋጀቱንም ነው ባንኩ ያስታወቀው።
ይህ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል በውስጡ የማቀዝቀዣ ኤነርጂ (Power and Cool)፣ የዳታ ሴንተር የኔትወርክ ኦፕሬሽን (ወደ ማእከሉ ሳንሄድ ካለንበት ሆነን ማኔጅ የምናደርግበት)፣ የሴኩሪቲ ኦፕሬሽን ዘርፍ (ችግር ሲከሰት ችግሩን ከመጠቆምና ከመለየት ባለፈ ችግሩን እስከ መከላከል የሚያደርስ አሰራር) እንዲሁም ሶፍትዌር ዲፋይኒንግ  ሴንተርና ከ500 ሜትር ጀምሮ ወደ ማዕከሉ የሚሄዱትን ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች የሚቆጣጠር CCTV ካሜራዎችም የተገጠሙለት በመሆኑ ሁሉም ነገር ከአደጋና ከስጋት የፀዳ አሰራርን እንዲከተል ያደርጋል ተብሏል።
በመረጃ ማዕከሉ ምርቃ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የብሄራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር 3ኛ ደረጃ የመረጃ ማዕከል በመገንባታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላ፣ የምታስተዳድሩትን የህዝብ  ሀብት ከአደጋ መጠበቅ ዋንኛ ስራችሁ በመሆኑ ይህንን ለማድረግ ቀዳሚ መሆናችሁ ያስመሰግናችኋል ብለዋል” ዶክተሩ አክለውም ከዳሽን ባንክ  ባለፈ ሁሉም ባንኮች ይህን ቴክሎጂ ገንብተው ማየት እንደሚፈልጉ ገልፀው፣ ቀደም ያሉት፣ መካከለኛ ዕድሜ ያላቸውም ሆነ አዳዲሶቹ ባንኮች ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ መታጠቅ ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
የዳሽን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው “ብሄራዊ ባንክ በየጊዜው የሚያወጣቸው ህጎችና መመሪያዎች አንቂና ከዘመኑ ጋር እንድንራመድ የሚያደርጉን በመሆኑ እናመሰግናለን ብለዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የዘመን ባንክን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነን ጨምሮ የበርካታ ባንኮች ስራ አስፈጻሚዎችና የቦርድ አመራሮች የተገኙ ሲሆን በመረጃ ማዕከሉ ግንባታ የተሳተፉ ተቋማትም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዳሽን ባንክም በመረጃ ማዕከሉ ግንባታ ከአለም አቀፍ የጥራት ሸላሚ ድርጅት የዕውቅና ሰርተፍኬት አግኝቷል።


Read 573 times