Saturday, 25 June 2022 18:07

ከወለጋው ጥቃት የተረፉ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብተዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 “ተመልሰን ስንመጣ ካገኘናችሁ እንጨርሳችኋለን ብለውናል”

   •በጥቃቱ ከ350 በላይ ንፁሃን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ተነግሯል
   •ቁጥራቸው ያልታወቀ ነዋሪዎች በታጣቂዎቹ ታግተው ተወስደዋል
   •በጥቃቱ ከ3 ቀን ህፃን እስከ 82 ዓመት አዛውንት ድረስ ተገድለዋል
   • የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መንግስት በጅምላ ጭፍጨፋው ዙሪያ ፈጣንና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግ አሳስቧል
   • ኢሰመኮ መንግስት ለዜጎቹ ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቋል
   • “አገራችንን ለቃችሁ ካልወጣችሁ ተመልሰን መጥተን እንጨርሳችኋለን ብለውናል”
   • “ከአሰቃቂው ጥቃት ብንተርፍም በረሃብ ማለቃችን ነውና ድረሱልን”
- ከጥቃቱ የተረፉ  
        
           በምዕራብ ወለጋ ዞን በጊምቢ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የቶሌ ቀበሌ ጉቱ ጨቆርሳ፣ ሣልሳው፣በገኔ፣ጫካ ሰፈርና ሃያው መንደሮች ውስጥ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በታጣቂዎች በተፈፀመ የጅምላ  ጭፍጨፋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ350 በላይ እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡
ቢቢሲና ሮይተርስን ጨምሮ የተለያዩ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን የአይን እማኞችን ጠቅሰው የሟቾቹ ቁጥር ከ300- 350 ሊደርስ እንደሚችል ሲገልፁ፤ በአሜሪካ የአማራ ማህበር  አድቮኬሲ የሟቾችን ቁጥር 378 ይደርሳል ብሏል፡፡ በመንግስት በኩል የሟቾቹን ቁጥር የሚገልፅ ይፋዊ መረጃ  እስካሁን አልተነገረም፡፡
ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡20 ጀምሮ እስከ ቀኑ 7 ሰዓት በዘለቀው በዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ፤ ከተወለደ ገና 3 ቀናትን ብቻ ካስቆጠረ አራስ ልጅ አንስቶ እስከ 82 ዓመት አዛውንት ድረስ በግፍ መጨፍጨፋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡
ጥቃቱ የተፈፀመው መንግስት በአሸባሪነት በፈረጀው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፤ ታጣቂው ቡድን የአማራ ተወላጆች በሚኖሩባቸው አምስት መንደሮች ውስጥ በመግባት የመንደሮቹን ነዋሪዎች እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ጨፍጭፋቸዋል፤ ነዋሪዎቹ በቤታቸው  እያሉ ቤቱን ቢንዚን አርከፍክፈው  አቃጥለዋቸዋል፤ ጉቱ በተባለው መንደር ውስጥ በቤታቸው ውስጥ የነበሩ 8 የአንድ ቤተሰብ አባላት ቤቱን በላያቸው ላይ ዘግቶ በማቃጠል ሁሉም በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሞቱ የተደረገ ሲሆን በዚህ መንደር ውስጥ ብቻ የአማራ ብሔር ተወላጆች የሆኑ 35 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
በጨቆርሳ መንደር 102 ሰዎች በግፍ የተጨፈጨፉ ሲሆን ሣልሳው በሚባለው መንደር ነዋሪ የሆኑ 102 ንፁሃንም ተገድለዋል፡፡ በገኔ-ከአንድ መቶ በላይ አስክሬን መነሳቱንም የአይን እማኞች ይገልፃሉ፡፡
ጥቃቱ የተፈፀመው የአካባቢው አርሶ አደር ለእርሻ ስራ ወደ ማሳ በተንቀሳቀሰበት ወቅት በመሆኑ በአብዛኛው በመንደር ውስጥ የነበሩት ህጻናት፣ሴቶችና አቅመ ደካሞች  ብቻ እንደነበሩ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፤ ታጣቂዎቹ ወደ መንደር ውስጥ ዘልቀው ያገኟቸውን ህጻናት ሴቶችንና አቅመ ደካሞችን በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፍጭፈው መሄዳቸውን  ተናግረዋል፡፡
በጨቆርሳ መንድር ውስጥ ነዋሪ የሆነና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ነዋሪ፣ ለአዲስ አድማስ እንደተናገረው፤ የተፈፀመው አሰቃቂና ዘግናኝ ጥቃት እንኳንስ በወንድምና በአገር ልጅ በጠላት እንኳን ሊፈፀም የማይችል  ዘግናኝ ጥቃት ነው” ብሏል፡፡ በዕለቱ በመንደሩ ባለመኖሩ ህይወቱ መትረፉን የሚናገረው ወጣቱ በጥቃቱ አሳዳጊ አያቴንና ታናሽ ወንድሜን አጥቻለሁ ብሏል፡፡
“ታጣቂዎቹ ወደ መንደሮቹ ዘልቀው ከገቡ በኋላ፤ አስቀድመው ጤና ጣቢያዎችን እየከፈቱ መድሃኒቶችን በመኪኖቻቸው እየጫኑ ወሰዱ፡፡
ሱቆችን ዘረፉ፤ ከዚያ  በኋላ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚኖሩባቸው መንደሮች እየገቡ በቤቱ ውስጥ ያገኙትን ሁሉ ይገድሉ ጀመር፡፡ ከ3 ሠዓት እስከ 7 ሰዓት ድረስ በዘለቀው በዚሁ ጥቃትም በየቤታቸው ውስጥ እንዳሉ በእሳት እየተቃጠሉ፣በጥይት እንደተደበደቡና በዘግናኝ ሁኔታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተገድለዋል፡፡ ታጣቂዎች የሚገድሉትን ገለው የሚዘርፉትን ዘርፈው 7ሰዓት ላይ መንደሮቹን ለቀው የወጡ ሲሆን መከላከያ ግን የደረሰው  ከወጡ በኋላ ለ4 ሰዓት ያህል ዘግይቶ ነው” ብሏል፡፡
ጫካ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው መንደር ውስጥ ነዋሪ የሆኑትና ከባለቤታቸውና ሁለት ልጆቻቸው ጋር ለእርሻ ስራ ወደ ማሳ ሄደው ከጥቃቱ ማምለጣቸውን የሚናገሩት ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉት ነዋሪ እንዳሉት ከጥቃቱ በሕይወት ቢተርፉም፣ቤት ንብረታቸውና ለዘር ያስቀመጡት እህል ሳይቀር መዘረፋቸውንና ለዓመታት አብረዋቸው የኖሩት ጎረቤቶቻቸውን ማጣታቸውን ነግረውናል፡፡
“ይሄ አገራችሁ አይደለም፣አገራችንን ለቃችሁ ውጡ ተመልሰን ስንመጣ ካገኘናችሁ ግን አንድም ሰው አይተርፈንም” ብለው አስጠንቅቀው ነው የሄዱት ያሉት ነዋሪው ይሄን እየሰማን እንዴት ዝም  ብለን እንቀመጣለን? እኛ ላለፉት 30 እና 40 ዓመታት የኖርነው እዚሁ ነው- የት ነው የምንሄደውስ? ግራ ገብቶናል፤ ልጆቼ እኛ አገራችን ግን የት ነው? እያሉ ይጠይቁኛል፤ የት ልበላቸው? ልጆቼ ተወልደው ያደጉት፤ እዚሁ ነው አፋቸውን የፈቱት በኦሮምኛ ቋንቋ ነው፡፡
ምንድን ነው የምላቸው? የትስ ነው የምወስዳቸው መንግስት የሚባለው ነገር ካለ መፍትሔውን ይሰጠን-አሁን ልጆቼን ይዤ ከዘመድ ቤት ተጠግቼ ነው ያለሁት፤ በክረምት ሰማይ ተደፍቶበናል፤ ወገን ይድረስልን” ሲሉ ተማፅዋል፡፡
ካለፈው እሁድ ጀምሮ በጥቃቱ የተገደሉት ወገኖችን አስክሬን የማንሳትና የመቅበር ስራ እስከ ማክሰኞ ድረስ መቀጠሉን የሚገልፁ ምንጮች፤ የአስክሬኖቹ ሽታ አካባቢውን እያዳረሰ በመሄዱና ስፍራው በአሞራ በመወረሩ ሣቢያ አስክሬኖችን በጅምላ ለመቅበር መገዳዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ሃብትና ንብረታቸውን አጥተው በቤተእምነቶችና በየዘመዶቻቸው ቤቶች ተጠልለው የሚገኙ ነዋሪዎች “ከጥቃቱ ብንተርፍም በረሃብ ልናልቅ ነው፡፡ ልጆቻችንን የምናበላውና  በዚህ ክረምትና ብርድ የምናለብሳቸው  ቸግሮናል፤ መንግስትና  ወገኖቻችን ይድረሱልን” ሲሉ ተማፅነዋል፡፡
“ከዛ ሁሉ መከራ ተርፈን፣ያንን ሁሉ አስክሬን ተመልክተን ቆመን መሄዳችን ተአምር ነው፡፡ በተለይ ህፃናት ልጆቻችን ከሬሳ መካከል ተርፈው አዕምሮአቸው ጤናማ መሆን ስለማይችል የህክምና እገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንኳንስ እነሱ እኛ ያንን  ሰቆቃና መከራ ስናይ ቆይተን ቀና ማለት አቅቶናል፡፡ አሁን ዝም ብለን ሃዘናችንን እየተካፈልን ነው ያለነው፤ ቤተሰቦቻቸው አልቀው ሜዳ የቀሩ ከ30 በላይ ህጻናት አሉ- እነዚህን ህጻናትስ ማነው የሚረከባቸው? መንግስትም ሆነ ወገን ሁሉ ይድረስልን” ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የመከላከያ ሃይል እንዳለና ስፍራው አንጻራዊ ሰላም እንደሚታይበት የሚገልጹት ነዋሪዎቹ፤ ተመልሰን እንመጣለን ያሉት ታጣቂዎች መቼ እንደሚመጡ ባለማወቃችን ተጨንቀናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቃቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ በንጹሃን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋውን የፈፀሙት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች እንደሆኑ ጠቁሞ፤ የጥቃቱ ኢላማዎች በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መሆናቸውን ከአይን እማኞች አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ከግድያው በኋላ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን የጠቆመው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ መንግስት ንፁሃን ዜጎች ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስባቸው እርምጃዎችን እንዲወስድና ሲቪሎች የጥቃት ኢላማ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ በማድረግ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በምዕራብ ወለጋ ጊንቢ ወረዳ በ5ቱ መንደሮች ውስጥ የተፈፀመውን ጥቃት አውግዞ የወንጀሉ ፈጻሚዎችጠይቋል፡፡
አሜሪካ፣ቻይና እና ኢራን፣ በጅምላ ለተጨፈጨፉት ዜጎች አሰቃቂውን የጅምላ ጥቃት በጥብቅ አወግዘዋል የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል፡፡

Read 23640 times