Print this page
Saturday, 25 June 2022 18:04

የሙስና ክስ የቀረበባቸው ከ300 በላይ ዳኞች ህግ ፊት አልቀረቡም

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 ጉቦ መጠየቅ፣ ስልጣንን አላግባብ መጠቀምና የገለልተኝነት ችግር ከቀረቡባቸው ክሶች ይጠቀሳሉ፡፡
በፍርድ ቤት ሂደት ውስጥ ከሙስናና ስልጣንን ያለአግባብ ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ክስ የቀረበባቸው ከ300 በላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ህግ ፊት እንዳልቀረቡና አሁንም ድረስ በስራቸው ላይ እንደሚገኙ  ደርሼበታለሁ ሲል የፌደራል የፍትህና ህግ ኢንስቲቲዩት አስታወቀ፡፡ ተቋሙ ለአምስት ወራት ሲያካሂድ የቆየውን ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡
የፌደራል የፍትህና ህግ ኢንስቲቲዩት የፌደራል የፍትህ ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳደርና የተገልጋዩ ህዝብ እርካታን በተመለከተ ጥናት እንዲያካሂድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ላለፉት አምስት ወራት ሲያካሂድ የቆየውን ጥናት አጠናቅቆ የጥናቱን ውጤት ከትናንት በስቲያ ለምክር ቤቱ ይፋ አድርጓል፡፡
ኢንስቲቲዩቱ በጥናቱ አገኘሁት ባለው ውጤት መሰረት፤ ቁጥራቸው ከ300 በላይ  የሆኑ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች፣ ጉቦና ጥቅማጥቅሞችን መጠየቅ፣ አላግባብ በስልጣን መጠቀም፣ የመዝገብ መጥፋት፣ደንበኞች ላይ በደል ማድረስ፣ የገለልተኝነት ችግር፣ማስረጃን በአግባቡ አለመመርመርና በራስ አስተያየት ውሳኔን መስጠት የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸዋል።
እነዚህ በተገልጋዮች የቀረቡት ክሶች በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ታይተው ውሳኔ ሊሰጥበትና ክስ የቀረበባቸው ዳኞች በተከሰሱበት ጉዳይ ህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ ሲገባ ዳኞቹ ያለምንም ተጠያቂነት ስራቸውን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ በጥናቱ ማረጋገጥ መቻሉ ተገልጿል፡፡
ዳኞች ተጠያቂ እንዲሆኑ ያልተደረጉበት ምክንያት የፍርድ ቤቶች የውስጥ ምርመራ ቡድኖች ጠንካራ አደረጃጀት ስለሌላቸውና የዳኞች አስተዳደር ጉባኤም  ጉዳዩን ተከታትሎ ማስፈፀም ባለመቻሉ እንደሆነም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡
መሰረታዊ አገር አቀፍና አለም አቀፍ የፍርድ ቤት አገልግሎቶች መለኪያዎችን መሰረት በማድረግ ለአምስት ወራት ተደረገ የተባለው ይኸው ጥናት፤ በአጠቃላይ በፍርድ ቤቶች ውስጥ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶች ዝቅተኛ መሆናቸውን አመልክቷል
የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በዳኞች ላይ የሚቀርቡ ክሶችን በማየት ጥፋት መፈፀሙን ሲያረጋግጥ የዳኛው የይግባኝ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ወዲያውኑ ዳኛው ከዳኝነት ኃላፊነቱ እንዲሰናበት ጉባኤው ለተወካዮች ምክር  ቤት የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ በ2013 ዓ.ም የወጣው የፌደራል ዳኞች የስነ ምግባር፣ የዲሲፕሊን ክስ ስነስርዓት ደንብ ያመለክታል፡፡



Read 11639 times