Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 06 October 2012 15:20

ታሪካዊው ግቢ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከራስ መኮንን ሰፈር እስከ ዩኒቨርሲቲ
ንጉሡ ከላይ በተጠቀሰው የአውሮፓ ጉብኝታቸው የተመለከቷቸው ውበትና ግርማ ሞገስ ያላቸው ቤተ መንግሥቶች ስላስደመሟቸው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚችል ዘመናዊ ቤተ መንግሥት የመገንባት እቅድ ነበራቸው፡፡ ይህንን የንጉሠ ነገሥቱን ሐሳብ እውን ለማድረግ ካምቴዝ የተባለ አውሮፓዊ መሐንዲስ በሥራ ሚኒስቴር ከነበሩ የውጭ ሐገር መሐንዲሶች ጋር በመሆን፣ የአዲስ ቤተ መንግሥት ንድፍ ሰርቶ አቀረበ፡፡


አዲስ አበባ ከተማ የተመሰረተው ዳግማዊ አጤ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ተራሮች ወደ ደቡብ ወርደው፣ አሁን ታላቁ ቤተ መንግሥት ከሚገኝበት ሥፍራ ላይ መኖሪያቸውን ሲቆረቁሩ ነበር፡፡ በዚሁ ጊዜ ንጉሡ ለጦር አዣዦቻቸው፣ ለአገረ ገዢዎቻቸውና ባለሟሎቻቸው መኖሪያ የሚሆን ሰፋፊ መሬት በመመስረት ላይ ባለው በአዲስ ከተማ ውስጥ እንዲሰጣቸው አደረጉ፡፡ ከአጤ ምኒልክ የጦር አዣዞች ዋንኛው የሆኑት ራስ መኮንንም ዛሬ ስድስት ኪሎ ብለን ከምናውቀው አካባቢ፣ ወደ ሰሜንና ሰሜን ምዕራብ እስከ እንጦጦ ተራሮች ድረስ ያለውን ሰፊ ቦታ በርስትነት ተቀብለው፣ አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በሚገኝበት ሥፍራ ላይ ለራሳቸው እና ለሠራተኞቻቸው የሚሆኑ፣ የሣር ክዳን ያላቸው ቤቶች ሠሩበት፡፡ ከተሰሩትም ቤቶች አንዱ ለአቢሲኒያ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ሆኖ ያገለግል እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሥፍራው መጀመሪያ የራስ መኮንን ሰፈር፣ በኋላ ደግሞ የላይኛው ግቢ በመባል ይታቅ ነበር (የታችኛው ግቢ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ነው)
ራስ መኮንን የሚቀመጡት ግዛታቸው በነበረበት በሐረር ከተማ በመሆኑ፣ በዚህ በአዲሱ ቤታቸው ውስጥ የሚያርፉት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ብቻ ነበር፡፡ ራስ መኮንን በአዲሱ ቤታቸው ብዙም ሳይጠቀሙበት፣ ከዚህ ዓለም ስላለፉ ቦታውና ቤቱ ለትልቁ ልጃቸው ለደጃዝማች ይልማ መኮንን በውርስ ተላለፈ፡፡ ደዳዥማች ይልማም አባታቸውን ወዲያው በሞት በመከተላቸው፣ ቦታው ለሁለተኛ ጊዜ በውርስ ለደጃዝማች ተፈሪ (በኋላ አጼ ኃይለ ሥላሴ) ዞረላቸው፡፡ ከራስ መኮንን እረፍት አራት ህመተ ያህል ቆይቶ አቢሲኒያ ባንክ ግቢውን ለቋል፡፡
ልጅ እያሱ ከሥልጣን ተወግደው ደዳዝማች ተፈሪ በራስነት ማዕረግ አልጋ ወራሽ ሲባሉ ቋሚ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ በማድረጋቸው፣ የላይኛው ግቢ እንደገና ወደ ታሪክ መድረክ ብቅ አለ፡፡ ራስ ተፈሪም በአባታቸው የተሰሩ የሳር ክዳን ቤቶችን በቆርቆሮ ከመቀየራቸውም በላይ የውጭ ተመልካቾች የረቀቀ የእጅ ሥራ ውጤት ታይቶበታል ያሉለትን አምሳለ ገነት የተሰኘ ቤተ መንግሥት አሰሩ፡፡ አምሳለ ገነት በአውሮፓውያንና በኢትዮጵያውያን እንደተገነባ የታወቀ ሲሆን ከተገነባ በኋላ ባሉት ስምንት ዓመታት ያህል በብቸኝነት የውጭ እንግዶችን እና ዲፕሉማቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም የተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት የተባለ ድርጅት በዚሁ ግቢ ተቋቁሞ ብርሃንና ሰላም የተባለውን የዘመኑ ተራማጅ ጋዜጣ እያተመ ያወጣ ጀመር፡፡ ይህ ሥፍራ ከዚህ ጊዜ በኋላ ያልጋ ወራሽ ግቢ በመባል ይታወቅ ጀምር፡፡
ራስ ተፈሪ በ1916 ዓ.ም ግድም አውሮፓን በጎበኙ ጊዜ በፈጠሩት ጠቃሚ ግንኙነት ሳቢያ ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ልዑላንና የመንግሥት ተወካዮች ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ ለነዚህ እንግዶች ክብር አምሳለ ገነት ቤተ መንግሥት አልመጥን እያለ መጣ፡፡ በመሆኑም በ1919 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለሚጎበኘው የኢጣሊያው ንጉሥ አልጋ ወራሽ (የአብሩዚው መሥፍን) ማረፊያ እንዲሆነው ተብሎ ማለፊያ የድንጋይ ቤት በአጭር ጊዜ ተሠርቶ አለቀ፡፡ በአዲሱ ቤት መስፍኑ በእንግድነት ከተስተናገደበት በኋላ፣ ራስ ተፈሪ ለልዩ ልዩ አገልግሎት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ ስሙም የዱክ ቤት እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ ራስ ተፈሪ በ1921 የንጉሥነት ዘውድ ከጫኑና በ1923 ደግሞ ንጉሠ ነገሥት ከተባሉ ወዲህ ግቢው የተፋጠነ እድገት አሳይቷል፡፡
ንጉሡ ከላይ በተጠቀሰው የአውሮፓ ጉብኝታቸው የተመለከቷቸው ውበትና ግርማ ሞገስ ያላቸው ቤተ መንግሥቶች ስላስደመሟቸው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚችል ዘመናዊ ቤተ መንግሥት የመገንባት እቅድ ነበራቸው፡፡ ይህንን የንጉሠ ነገሥቱን ሐሳብ እውን ለማድረግ ካምቴዝ የተባለ አውሮፓዊ መሐንዲስ በሥራ ሚኒስቴር ከነበሩ የውጭ ሐገር መሐንዲሶች ጋር በመሆን፣ የአዲስ ቤተ መንግሥት ንድፍ ሰርቶ አቀረበ፡፡ ንድፉ ተቀባይነት አግኝቶ ተፋጥኖ እንዲገነባ ትዕዛዝ ስለተሰጠ፣ ሥራው ሌትና ቀን ሲጣደፍ ቆይቶ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀቀ፡፡
ገነተ ልዑል ተብሎ የተሰየመው አዲሱ ቤተ መንግሥት ሥራውን የጀመረው በጊዜው በኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ለማድረግ የመጡትን የስዊድን አልጋ ወራሽ ልዑል ጉስታቭ አዶልፍን እንግዳው አድርጎ በመቀበል ነበር፡፡ ይህ ቤተ መንግሥት የአገሪቱ ዋነኛ የአስተዳደር ማዕከል ሆኖ እስከ ኢጣሊያ ወረራ ድረስ ይቀጥላል፡፡
የኢጣሊያ ወረራ ከተጀመረ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱን ተከታዮቻቸው በማይጨው ጦርነት ላይ ተሳትፈው ሲመለሱ፣ ውጊያውን የገመገሙትና ከባለሥልጣኖቻቸው ጋር የወደፊቱን እቅድ የነደፉት ከዚሁ ከገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር፡፡ በተከታታይ በተደረጉ ምክክሮች ንጉሠ ነገሥቱ ጄኔቭ ወደሚገኘው የመንግሥታቱ ማህበር ተጉዘው የኢትዮጵያን አቤቱታ ለዓለም እንዲያሰሙ ስለተወሰነ፣ ሚያዝያ 24 ቀን 1928 ዓ.ም ከጧቱ በ11 ሠዓት ቤተ መንግሥቱን ለቀውና አዲስ አበባን ትተው በባቡር ተሣፈሩ፡፡
ብዙ የተለፋበት አዲሱ ቤተ መንግሥትም ተመርቆ ሥራ ከመጀመሩ ዕጣ ፈንታው ላልታወቀ ግራ የሚያጋባ ጊዜ የተተወ መሰለ፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ መሰደዳቸው እንደታወቀው ሥርዓት አልበኝነት በከተማው በመንገሡ፣ ቤተ መንግሥቲ ከፍተኛ ዘረፋ ተፈጸመበት የቤትና የቢሮ ቁሳቁሶች፣ ጌጦችና ሽልማቶች የዘረፋው ሰለባዎች ሆኑ፡፡ በዚህ ግርግርም አምሳለ ገነት የተባለው ቀደምት የአጤ ኃይለ ሥላሴ መኖሪያ በቃጠሎ ወደመ፡፡
በጀነራል ባዶግሊዮ የተመራው የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ወደ ገነተ ልዑል ሲዘልቅ ያገኘው የተዘረፈ ቤተ መንግሥትና የተቃጠሉ ቤቶችን ነበር፡፡ አዲስ አበባን እንዲያስተዳድር ፋሽስቶች የሾሙት ቦታይ ጽህፈት ቤቱን በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት አድርጎ በዚያ የነበሩትንና የኢትዮጵያ ንጉሣዊ መንግሥት ተምሳሌት የሆኑትን አንበሶች በመግደል ስራውን ጀመረ፡፡
ፋሺስቶች በቤተ መንግሥቱ ሠራዊታቸውን ያሰፈሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ገዢ ሆኖ የተሾመው ባዶግሊዮም መኖሪያውን በኢጣሊያ ኤምባሲ ውስጥ እንጂ በቤተ መንግሥቱ አላደረገም ነበር፡፡
ከባዶግሊዮ በኋላ የኢትዮጵያ ገዢ ሆኖ የተሾመው የኢትዮጵያ ንጉሣዊ መንግሥት ተምሳሌት የሆኑትን አንበሶች በመግደል ስራውን ጀመረ፡፡
ፋሺስቶች በቤተ መንግሥቱ ሠራዊታቸውን ያሰፈሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ገዢ ሆኖ የተሾመው ባዶግሊዮም መኖሪያውን በኢጣሊያ ኤምባሲ ውስጥ እንጂ በቤተ መንግሥቱ አላደረገም ነበር፡፡ ከባዶግሊዮ በኋላ የኢትዮጵያ ገዢ ሆኖ የተሾመው ግራዚየኒ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ የሰፈሩትን ወታደሮች አስወጥቶ ግቢውን የኢጣሊያ ምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት ማዕከላዊ መሥሪያ ቤት አደረገው፡፡
ግራዚያኒ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የኔፕልስን ልዑል መወለድ የደስታ ጊዜ አስመልክቶ ምጽዋት እንዲሰጥ አዝዞ፣ በርካታ ቀሳውስጥ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት እንዲሰበሰቡ አደረገ፡፡ ግራዚያኒ በፋሺስት ጀነራሎች መካከል የቤተ መንግሥቱ ደረጃ ላይ ቆሞ ስለ “ታላቁ የኢጣሊያ መንግሥት” ኃያልነት፣ ቸርነትና ምህረት ዲስኩር ሲያሰማ ሞገስ አስገዶምና አብርሐ ደቦጭ የተባሉ ወጣቶች የእጅ ቦምቦች አከታትለው ወረወሩበት፡፡ ግራዚያኒን እና ጀነራል ሊዮቴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፋሺስት ባለሥልጣኖች በፍንዳታው ቆሰሉ፡፡ ከፍንዳታው በኋላ የኮሎኒያል ፖሊሶች፣ የወታደር ፖሊሶችና ባለ ጥቁር ሸሚዞች ሶስት ቀን የሚቆየውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ እዚያው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ በመጀመር ከተማውን በደም አጠቡት፡፡
ከግራዚያኒ በኋላ የተሾመው የፋሺስት አገረ ገዢ የኦስታው መስፍን (Duke of Aosta) መኖሪያውን በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ያደረገ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም የፋሺስት አስተዳዳሪ ነው፡፡ መስፍኑ የኢትዮጵያ አርበኞችና የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት የፋሺስት ሠራዊትን እየረመረሙ በድል ወደ መሐል አገር ሲገሰግሱ ሸሽቶ መቀመጫውን ደሴ ላይ እስካደረገ ድረስ በዚህ ቤተ መንግሥት ተገልግሎበታል፡፡
1933 ዓ.ም ለፋሺስቶች ሽንፈትን፤ ለኢትዮጵያ ደግሞ ነፃነትን ይዞ መጣ፤ ኢጣሊያኖችም ሽንፈታቸውን ተቀብለው አዲስ አበባን ለእንግሊዞች አስረከቡ፡፡ መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የብሪታንያ ወታደሮች በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት የፋሺስት ኢጣሊያን ባንዲራ አውርደው የእንግሊዝን ሰንደቅ ዓላማ በጊዜያዊነት ያውለበለቡ ሲሆን በግቢው ውስጥ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተከበረው ግን ከአንድ ወር በኋላ፣ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አጼ ኃይለ ሥላሴ በድል ወደ መናገሻ ከተማው ሲመለሱ ነበር፡፡
እውነተኛ ጌታውን ከአምስት ዓመታት በኋላ እንደገና የተቀበለው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሲያገኙት የቀድሞ መልኩ በእጅጉ ተለዋውጦ እና አዳዲስ ግንባታዎች ተጨምረውበት ከፊል ኢትዮጵያዊ ከፊል አውሮፓዊ ሆኖ ነበር፡፡
በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ኢጣሊያኖች በገነቧቸው ሕንጻዎች የጽህፈት ሚኒስቴር፣ የግቢ ሚኒስቴር፣ የዘውድ ምክር ቤት እና የግርማዊነታቸው ልዩ ጽህፈት ቤቶች ተመስርተው የድህረ ነጻነት ሥራ አሀዱ ተብሎ ተጀመረ፡፡ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ በነበሩት ሀያ ዓመታትም ይህ ግቢ የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና ወታደራዊ ማዕከል በመሆን አገልግሏል፡፡ የኤርትራን ጉዳይ የመሳሰሉ የወቅቱ ቁልፍ አገራዊ አጀንዳዎች ተመክረውበታል፡፡ በርካታ ሹመቶችና ሽረቶች፣ ግብር እና ግብዣ ተከናውነውበታል፡፡ የውጭ መልዕክተኞችን፣ ዲፕሎማቶችንና መራሄ መንግሥታትን ተቀብሎም አስተናግዷል፡፡ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የፋሺስት ጭፍጨፋ ወዲህ ይህ ግቢ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረትን እንደገና የሳበው ታህሳስ 5 ቀን 1953 ዓ.ም በጀነራል መንግስቱ ንዋይ እና በወንድማቸው በአቶ ገርማሜ ንዋይ የተመሩ የክብር ዘበኛ ወታደሮች በአጼው መንግሥት ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ባደረጉ ጊዜ ነበር፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱ ለዘውድ ታማኝ በነበረው ጦር ሠራዊት፣ አየር ኃይልና ብሔራዊ ጦር ሲከሽፍ ተስፋ የቆረጡት ጠንሳሾች ቀደም ብለው አግተዋቸው የነበሩትን 19 ከፍተኛ ባለሥልጣናትና አርበኞች በቤተ መንግሥቱ አረንጓዴ ሳሎን ውስጥ ሲጨፈጭፏቸው ከ24 ዓመታት በኋላ ቤተ መንግሥቱ እንደገና በደም ተበከለ፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሰውት አንጋፋ ሰዎች መካከል የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መኮንን ኃብተ ወልድ፣ የጦር ሚኒስትሩ ልዑል ራስ አበበ አረጋይ እንዲሁም የትግራይ ገዢ የነበሩት ልዑል ራስ ስዩም ይገኙበታል፡፡
በዚህ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ልክ ከአንድ ዓመት በኋላ ታህሳስ 9 ቀን 1954 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ ከአባታቸው በውርስ በተቀበሉት ቦታ ለይ የገነቡትን ታሪካዊውን የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት፣ ህንጻዎቹን ከነሙሉ ድርጅታቸውና ቁሳቁሶቻቸው ጋር ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲዞር ለገሱ፡፡ በዚህም ታሪካዊ ድርጊት ይህ ግቢ ከቤተ መንግሥትነት ወደ ቤተ እውቀትንት እስከመጨረሻው ተሸጋግሮ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ተሰይሞ የአገሪቱ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ ሆነ፡፡ ንጉሡ በምረቃው ዕለት ባደረጉት ንግግር “ጥበብ ካልፈለጓት አትፈልግም፤ አልማዝም ባትቀረጽ ድንጋይ ሆና ተቀብራ ትቀራለች፡፡ ዩኒቨርሲቲም የጥበብ ግምጃ ቤት ናት” ያሉ ሲሆን በመቀጠልም “ዩኒቨርሲቲ በመሠረቱ በመንፈስ ኃይል ላይ የሚሰራ ስለሆነ ከሚሰጠው ልዩ ልዩ ዕውቀትና ትምህርት በላይ ተማሪዎቹን ጣዕም ባለው የኑሮ ዘዴና ዋጋ ባለው በህይወት ጎዳና ሊመራቸው ይገባል” ብለው ነበር፡፡
በዚሁ ጊዜ የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥትም የራስ መኮንን ህንጻ ተብሎ ተሰየመና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር መስሪያ ቤት፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋምና ሙዚየም ሆነ፡፡ በግቢው የነበሩ ሌሎች ህንጻዎች የሬጂስትራር እና የፔርሶኔል ቢሮዎች ሆነው ሲዋቀሩ፣ የኪነጥበብ ትምህርት ክፍል እንዲሁም የSchool of Social Work እና የLab School ተመስርተው ሥራ ጀመሩ፡፡ የዱክ ቤት በመባል የሚታወቀው የድንጋይ ህንፃ የሕግ ት/ቤት ሆነ፡፡ በቤተ መንግሥቱ ግብር ይበላበት የነበረው የልደት አዳራሽ ደግሞ ወደ ተማሪዎች ካፍቴሪያነት ተቀይሮ በሥራ ላይ ዋለ፡፡
የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ ተበታትነው የነበሩትን ኮሌጆች በማስተባበርና አዳዲስ የትምህርት ዘርፎችን በመክፈትና በማስፋፋት ለአገሪቱ ሁለንተናዊ የትምህርት ዕድገት ያደረገው አስተዋጽኦ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው የንጉሣዊው ሥርዓት መንግሥት ፍጻሜ ደወልን ያስተጋባው የመሬት ላራሹ የተማሪ ንቅናቄ የፈለቀበት፤ የጎለበተበትና የተስፋፋብት ሥፍራ መሆኑ የማይዘነጋ ነው፡፡
ይህ ታሪካዊ ሥፍራ ከራስ መኮንን ሠፈርነት ተነስቶ እስከ ቤተ መንግሥትነት፤ ከጠላት ማዘዣ ጣቢያነት እንደገና ወደ ቤተ መንግሥትነት በመጨረሻም ወደ ዩኒቨርሲቲነት እየተቀያየረ በተጓዘበት ከአንድ ምዕተ ዓመት በበለጠ የዘመን ጉዞ ወደ ሀዘንና መከራ፣ ሹመትና ሽረት፣ ድልና ሽንፈት፣ ሕይወትና ሞትን፣ ሠርግንና ለቅሶን አስተናግዷል፡፡
ግቢው በፋሺስት ወራሪዎች እጅ ለአምስት ዓመታት፤ በእንግሊዞች ወታደራዊ አስተዳደር ሥር ደግሞ 30 ቀናት እንዲሁም በመፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾች እጅ ደግሞ ለጥቂት ቀናት ተዳድሯል፡፡
ግቢው በሐገሪቱ የዘመናዊ ታሪክ መዝገብ ውስጥ በርካታ ታሪካዊ ክንውኖችን በማስተናገድ ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሕያው ቤተ መዘክር ነው፡፡ በመጨረሻም አጼ ኃይለ ሥላሴ ይህንን ቤተ መንግሥታቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲ መቀየራቸው ለከፍተኛ ትምህርት መስፋፋትና ለእውቀት ልዕልና የነበራቸውን ክብር አጉልቶ የሚያሳይ በመሆኑ ስማቸው ከዘመናዊ ከፍተኛ ትምህርት ጅማሮ ጋር ሲነሳ ይኖራል፡፡

 

Read 4698 times Last modified on Saturday, 06 October 2012 15:39

Latest from